እነ በረከት ስሞኦን ሰልፈኛውን እና አስተባባሪዎቹን ማስፈራራት መርጠዋል
የአዲስ አበባ ወጣት ወያኔዎች የለቀቁበትን ፍረሀት መስበሩ የወያኔን ቁንጮዎች እጅግ አስፈርቷቸዋል። እንዲህ ነው እንጂ ፍርሀት ጓዙን ጠቅልሎ ከህዝቡ ላይ ተነስቶ ወያኔዎች ላይ ሲሰፍር!
ወያኔ የገነባው የፍርሀት ድባብ መናድ የጀመረው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላለፉት 14 ወራቶች ሳያቋርጡ መንግስት ከሀይማኖታችን ላይ እጁን ያንሳ እያሉ ተቀውሞ ማሰማት ከጀመሩ ጊዜ ወዲህ ይመስላል። በወቅቱ ሁኔታው ያሳሰባቸው ሟች አመባገነን መለስ ዜናዊ ካቢኔያቸውን በውድቅት ሰብስበው ሌሊቱን ሁሉ ሲመክሩ አድረዋል። እርግጥ ነው የህዝቡ ከፍርሀት አረንቋ መውጣት ወያኔዎችን ያስፈራቸዋል (ያርበደብዳቸዋል)።
ሙስሊሞች ከአንድ አመት በላይ ጥያቄዎቻችንን መልሱ፣ መሪዎቻችንን ፍቱ እያሉ ሲጮሁ ወያኔዎቹ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለትና ይልቁኑም በሞኖፖል የያዙትን ሚድያ ተጠቅመው ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ለማጋጨት ሲሰሩ ከረሙ (“ጅሀዳዊ ሀረካት” የተሰኘውን የወያኔ ድራማ-ነክ ዶክመንተሪ ፕሮፓጋንዳ ያስታውሳሉ?)። የወያኔን ቀትረ-ቀላልልነትና “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” የረከሰ አካሄድ የተገነዘቡት ሙስሊሞች ግን “ለጅሀዳዊ ሀረካት ዶክመንተሪ” የሚሆን ተዋጽኦ አላበረከቱም ነበር፣ ስለዚህም ወያኔዎቹ የኢትዮጵያን ክርስቲያን ማህበረሰብ ለማስበርገግና ለእኩይ አላማቸው ከጎናቸው ለማሰለፍ ወደ አፍጋኒስታን ተጉዘው ከአልቃይዳ እና ታሊባኖች ላይ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ምስሎች ተበድረው “ጅሀዳዊ ሀረካት” ላይ ሞሉበት። (ወሬ ለማሳመር ያህል እንጂ ወደ አፍጋኒስታን አልተጓዙም እዚሁ ከዩቲዩብ ላይ ነው ዳውንሎድ ያደረጉት)።
ይሁንና ከአንድ ሺህ አመታት በላይ “ሀይማኖት የግል፣ ሀገር የጋራ ነው” በሚል ብሄል ተዋዶና ተከባብሮ የኖረን የኢትዮጵያ እስላምና ክርስቲያን የበረከት ስሞኦን ረጋ ሰራሽ “ጅሀዳዊ ሀረካት” ሊፈትነው አልቻለም። እንደውም የሆነው ሌላ ነው፣ የወያኔን ተንኮል የተረዱ ኢትዮጵያውያን እስላምና ክርስቲያኖች፣ በስደት ከሚኖሩባቸው ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መልዕክቶች አስተላለፉ፣ ሼካውና ቄሱ ተቃቀፉ፣ የወያኔን “ጅሀዳዊ ሀረካት” የሚያመክን መልዕክትም አስተላለፉ።
ግንቦት 25፣ 2005 የሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ ታድያ ድንቅ ትዕይንት ታየ! ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተለመዱ መፈክሮቻቸውን አንግበው ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር ለተቃውሞ ተሰለፉ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው ስለነጻነት ዘመሩ። ይሄኔ ነው የወያኔ ቁንጮዎች “ጅሀዳዊ ሀረካታቸው” እንዳልሰራ የገባቸውና ፍርሀት የወረራቸው።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ነዋሪ (በአብዛኛው ወጣቱ) እሁድ ግንቦት 25 ፍርሀቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ወደ “ኩባ አደባባይ” ሲያመራ መሸሸጊያ ያጣው ፍርሀት ደግሞ በረከት ስሞኦን እና የወያኔ ቁንጮዎች ላይ ሰፈረ። ቢዘላብዱ፣ “አሸባሪ” እያሉ ቢያላዝኑ አያስደንቅም ይልቁኑ ከተሰጣችሁ 90 ቀናት ውስጥ 1 ቀን ተቀንሶ 89 ቀናቶች ናቸው የቀሯችሁና አስቡበት።
No comments:
Post a Comment