የራስን እድል በራስ መወሰን፣ እርስ በርስ እስከ ማጣላት…
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ተከበረ የተባለውን የብሄሮች ቀን ምን ያህሎቻችሁ እንደተከታተላቹህ አላቅም። ላላያችሁት ግንዛቤ ለመፍጠር ያህል… ዘንድሮ በአሉ የተከበረው ሱማሌ ክልል፣ በኦጋዴን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን በመንገር ወጋችንን እንጀምራለን። ይህ ዝግጅት እስከዛሬ በትግራይም፣ በአማራውም ክልል ተደርጓል… ሆኖም በአሉ ላይ ሁሉም የየብሄሩን ባህል ለማሳየት ሲጥር እንጂ፤ አንደኛው ብሄር ሌላውን ሲሰድብ ያየንበት አጋጣሚ አልነበረም። የዚህ አመቱ የብሄር ብሄረሰቦች ወይም የብሄረተኞች ቀን ሌላውን ኢትዮጵያዊ በመውቀስ ላይ የተመሰረተ ነበር።
“አማራው፣ ደገኛው፣ የመሃል አገር ሰው…” እያሉ ቀጠሉ አስተያየት ሰጪዎቹ። በአሉን ምክንያት በማድረግ በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች ወቀሳቸውን ቀጠሉ፤ “የመሃል አገር ሰዎች ‘ሽርጣም ሱማሌ’ እያሉ ይጠሩን ነበር” አለ። እኛንም በሃሳብ ወደኋላ መለሰን። የመሃል አገር ሰው ይህንን ቃል አይጠቀምበትም ለማለት አይደለም። ነገር ግን “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውን ቃል መስማት የጀመርነው፤ በኢትዮጵያ እና ሱማሌ ጦርነት ወቅት ነው። “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውን አባባል ሁሉም የመሃል አገር ሰው እንደማይጠቀምበት ሁሉ፤ በቴሌቭዥን መስኮት ላይ ብቅ ብለው ሌላውን ኢትዮጵያ የሰደቡት እና ያሰደቡትም መላውን የኢትዮጵያ ሱማሌ እንደማይወክሉ እናውቃልን። በመሆኑም ይህ ጽሁፍ በሁሉም የኢትዮጵያ ሱማሌዎች ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ የማያውቁትን ታሪክ ለማሳወቅ ያህል የተዘጋጀ መሆኑን ልብ ይበሉ።
(በዳዊት ከበደ ወየሳ)
በ1969 ዓ.ም. ሱማሌ ኢትዮጵያን ስትወር፤ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አፈናቅለዋል፤ ገድለዋል፤ በሺህ የሚቆጠሩትን ማርከው ወስደው አገራቸው ውስጥ አስረዋል። ሱማሌዎች ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ታዲያ ሽርጥ እንጂ ሱሪ ታጥቀው አይደለም። በዚያን ወቅት ታዲያ የኢትዮጵያ ልጆች ዳር ከዳር “ሆ” ብለው ሲነሱ፤ በወገናቸው ላይ የደረሰው በደል ቢያንገበግባቸው፤ “ይሄ ሽርጣም ሱማሌ” ብለው ቢሳደቡ ሊገርመን አይገባም። ከዚያ በፊት በነበሩት ጦርነቶች ፈረንጆች ኢትዮጵያን ሲወሩ፤ “ይሄ ሶላቶ” ብለው እንደሚጠሯቸው ጠላት የነበረውን የሱማሌ ታጣቂ “ይሄ ሽርጣም” እያሉ በመፎከር፤ የገባበት ገብተው ደምሠውታል፤ ዳግመኛም የኢትዮጵያን ድንበር እንዳይሻገር አድርገውታል።
በ1970 የሱማሌ ጦር ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ተደመሰሰ። ከጅጅጋ እና አካባቢው ተፈናቅለው የነበሩት የኢትዮጵያ ሱማሌዎች ወደ ድሮ መንደራቸው ተመልሰው፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሰላማዊ ኑሯቸውን ቀጠሉ። “ሽርጣም ሱማሌ” የሚለውም አባባል እየቀረና እየተረሳ መጣ። ዘንድሮ በሱማሌ ክልል፣ በአሉ ሲከበር… ሌላው ኢትዮጵያዊ ለሱማሌ ኢትዮጵያ የሰራው ውለታ ተረስቶ፤ የመሃል አገር ሰዎች “ሽርጣም ሱማሌ እያሉ ይሰድቡን ነበር” የሚል የጥላቻ መልዕክት ሲተላለፍ ሰማን።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ቀጠለ። “ድሮ ያስተማሩኝ ሰዎች ስማቸው ‘በቀለ፣ መኮንን፣ በየነ’ ነበር። አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል። አስተማሪዎቻችን ስማቸው መሃመድ እና አብዱል ሆኗል።” በማለት ለኢህአዴግን መንግስት ምስጋና ሲያቀርብ ስንሰማ፤ ጆሯችንን ማመን አቅቶን ተገረምነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ሲጀመር፤ የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የመጀመሪያ መምህራን የመጡት ከግብጽ አገር ነበር። በኋላም ላይ ከህንድ ድረስ መምህራን እየመጡ አስተምረዋል፤ ወይም አስተምረውናል። በውጭ ሰው ስለተማርን… “ለምን የውጭ ሰው አስተማረን?” ብለን አንቆጭም፤ ይልቁንም ለእነዚህ መምህራን አክብሮት እና ምስጋናችንን እናቀርባለን እንጂ። በሱማሌ የተመለከትነው ግን ከዚህ የተለየ ነበር… እቺም እድሜ ሆና… እነበቀለ፣ መኮንን እና በየነ የሚባል ስም የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ስላስተማሯቸው የሚናደዱ ሰዎችን ለማየት በቃን።
ደግሞም አንድ ሌላ እያሳቀ የሚያናድድ ነገር ሰማን። ሌላው አስተያየት ሰጪ እንዲህ አለ። “አካባቢያችን ልጅ ምግብ አልበላም ብሎ ሲያስቸግር፤ ‘አማራ መጥቶ እንዳይበላብህ’ በማለት ልጁ አማራ ሳይመጣበት ቶሎ እንዲበላ እናደርግ ነበር።” አለ።
“ጉድ እኮ ነው የሱማሌ ኢትዮጵያ ህዝብ አማራውን ይህን ያህል ይጠሉት ነበር? ማስፈራሪያስ አድርገውት ነበር?” እያልን ተገርመን ሳናበቃ ይኸው ሰውዬ ንግግሩን ቀጠለ።
“በሌላ በኩል ደግሞ የመሃል አገር ሰዎች (አዲሳባ ያለው ሌላው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው) ልጆቻቸው ምግብ አልበላም ብለው ሲያስቸግሯቸው፤ “ሱማሌ እንዳልጠራብህ!” ብለው ሲያስፈሯቸው፤ ምግቡን ጥርግ አርገው ይበሉ ነበር።” ሲል ሰማን። አብረውኝ ኢቲቪን ይመለከቱ የነበሩ “የመሃል አገር” ሰዎችን በጣም አሳቃቸው። እርስ በርስ ተያየንና “ሱማሌ እንዳይመጣብህ!” ተብሎ ምግብ ሲበላ የነበረ ከመሃላችን ነበር?” ብሎ ጠየቀ አንዱ…
ሌላኛው “እኛ አያጅቦን ነው የምናውቀው” ሲል ትንሽ አሳቀን።
“ሱማሌ ሳይመጣብህ!” ተብሎ እያስፈራሩ ምግብ ያስበሉት ይፍረደን” በማለት በጉዳዩ ላይ ስቀን ልናልፍ እንችል ይሆናል። ነገር ግን … ለአማራው ድርጅት ‘ቆሜያለሁ’ የሚለው ብአዴን/ኢህአዴግ ነገሩን እንዴት አይቶት ይሆን?
የብሄር በሄረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ የሚተላለፈው የጥላቻ አስተያየት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ኢቲቪን ከመዝጋታችን በፊት ሌላ አስተያየትም አደመጥን። ሰውየው እንባ እየተናነቃቸው፤ “መናገሻ ከተማችንን አዲሳባን ለማየት እንኳን አይፈቀድልንም ነበር።” ብለው ሲሉ፤ በራስ ተፈሪ መኮንን ዘመን የነበሩ የሱማሌ ፖሊሶች ታወሱን። በወቅቱ በአዲስ አበባ፤ በፖሊስነት ተቀጥረው ሰአት እላፊ እና ጸጥታ የሚያስከብሩት የመጀመሪያ ባለደሞዝ የአዲስ አበባ ፖሊሶች የሱማሌ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። እናም “አዲስ አበባን ለማየት እንኳን አይፈቀድልንም ነበር” እያሉ የሚያለቅሱትን አዛውንት አይተን፤ “ወደ አዲስ አበባ መሳፈሪያ ካላጡ በቀር የባቡር መስመር ከተዘረጋ ራሱ፤ መቶ አመት አልፎታል”። በማለት ታዝበናቸው ዝም አልን።
ሌላዋ ሴት ደግሞ ቀጠለች። ሴትዮዋ መናገር ስላለባት ብቻ የምትናገር ነው የምትመስለው… “የድሮ እና የአሁኑን ሳስተያየው በጣም ብዙ ልዩነት አለው” ብላ ጀመረች። ልጅቷ እንኳንስ ስለቀዳማዊ ሃአይለስላሴ ዘመን ቀርቶ ስለደርግ ለማውራት እድሜዋ የሚፈቅድላት አይደለችም። ወሬዋን ግን በድፍረት ቀጠለች። “የድሮና የአሁኑ በጣም ልዩነት አለው… ዑውውውው።” በማለት የአሁኑን አዳነቀች። አድናቆቷን ሳታቋርጥ “የድሮ እና የአሁኑን ልዩነት ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል” ብላ በቃላት እጥረት ምክንያት ልዩነቱን ሳትነግረን ቀረች።
ሌላው ደግሞ እንዲህ አለ። “ይሄ አካባቢ ለወታደራዊ ጦር ካምፕ ይጠቀሙበት ነበር እንጂ፤ ለህዝቡ ግድ አልነበራቸውም።” አለን። እውነት ነው። ፈረንሳይ ከጅቡቲ አልፋ ወደ ኢትዮጵያ የመስፋፋት ብዙም ህልም አልነበራትም። እንግሊዝ እና ጣልያን ግን… ሁለቱም ከሱማልያ ግዛቶቻቸው ተነስተው፤ ኦጋዴን እና አካባቢውን ጨምረው እስከ ሃረር ድረስ ለመግዛት፤ ግልጽ የሆነ እቅድ እና ሙከራ አድርገው ነበር። ሱማሊያ ነጻ ከወጣች በኋላ ደግሞ ከራሽያ ባገኘችው የጦር መሳርያ በመታገዝ እጅግ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አድርጋለች። በዚህ ጊዜ ሁሉ ሰራዊቱ ከመሃል አገር እየተነሳ፤ ኦጋዴን እና አካባቢው በውጭ ሃይሎች ስር እንዳይወድቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ይህ ሌላውን አገር በወታደራዊ ኃይል የመከላከል ስራ… ዛሬ ስሙ እና ውለታው ተረስቶ “አካባቢውን የወታደር ካምፕ አደርገውብን ነበር” በሚል ወቀሳ መቀየሩ ይገርማል።
አብረውን የነበሩት ጓደኞቼ በኢቲቪ ተናደዋል። ቴሌቪዥኑን ከመስበራቸው በፊት በሰላም ዘጋነውና ሰላማዊ ጨዋታችንን ጀመርን። “ለመሆኑ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደገኛ፣ የመሃል አገር፣ ክርስቲያን፣ አማራ…” እየተባለ ቅጽል እየወጣለት መሰደብ አለበት ወይ? ይህ ደገኛም ሆነ ነፍጠኛ ያሉት ኢትዮጵያዊ ለዚያ ህዝብ ውለታ አላደረገምን? ዝርዝር ውስጥ አንገባም። ሆኖም በታሪክ ቅኝት ወደኋላ መለስ ብለን የእውነትን ማህደር በማገላበጥ ታሪክን እስኪ እንመርምር። እንዲህ ነው።
ወደ አጼ ምኒልክ ዘመን እንሂድ… በፊት በቱርኮች፤ በኋላ ደግሞ በግብጾች ሲተዳደር የነበረው ህዝብ የጠመንጃውን አፈሙዝ በኢትዮጵያውያን ላይ አነጣጥሮ እንደነበር ይታወቃል። በ1524 ዓ.ም. ግራኝ አህመድ እና አሊ ኑር እንደገነኑት ሁሉ፤ በ1876 ዓ.ም. ደግሞ አሚር አብዱላሂን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ገዢዎች ጉልበታቸው የደረጀበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ነዋሪውን በቁጥጥራቸው ስር አውለው፤ “በክርስቲያን መንግስት አንገዛም” ማለታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዚያ እምነት ውጪ የነበሩትን የገደሉበትና ያጠፉበት ታሪክ ነው ያለን። (ይህም በአረብኛ ተጽፎ የሚገኝ ሰፊ ታሪክ ያለው ጉዳይ ነው) አሚር አብዱላሂም ቢሆን፤ ለአጼ ምኒልክ “አልገብርም” ማለት ብቻ ሳይሆን፤ “አንተም እንደኛ ካልሰለምክ በስተቀር፤ በክርስቲያን ንጉሥ አንገዛም” በማለት ለአጼ ምኒልክ፣ ሽርጥ፣ መቁጠርያ እና መስገጃ ምንጣፍ ነበር የላከላቸው።
አጼ ምኒልክ የተላከላቸውን ሽርጥ፣ መቁጠሪያ እና መስገጃ አብረዋቸው ለነበሩ ሙስሊሞች ሰጥተው፤ ፊታቸውን ወደምስራቅ ኢትዮጵያ አዙረው፤ በአሚር አብዱላሂ የሚመራውን ጦር፤ ጨለንቆ ላይ ገጠሙት። በዚያ የጨለንቆ ጦርነት በርካታ ኢትዮጵያውያን አለቁ። ከሚንልክ ጋር የነበሩ የአማራ ተኳሾች እና የኦሮሞ ፈረሰኞች፤ የአሚር አብዱላሂን ጦር አሸነፉት። ጥር 18 ቀን፣ 1879 አካባቢው በምኒልክ ጦር ነጻ ወጣ። አሚር አብዱላሂም በጅጅጋ አድርጎ አገር ጥሎ ጠፋ።
በኋላ ላይ የአሚር አብዱላሂ ዘመዶች ወደምኒልክ ዘንድ መጥተው፤ “እባክዎን አገሩን እንዳያጠፉት” ቢሏቸው፤ “እኔ አገር አቀናለሁ እንጂ አላጠፋም። እዚህ ድረስ የመጣሁትም ሃይማኖት ለማጥፋት አይደለም። ሁሉም ሰው እንደየ እምነቱ ያድራል።” ብለው ወደጀጎል በሰላም ሲሸኙዋቸው፤ ከነሱም ጋር እነበጅሮንድ አጥናፌ እና እነሻቃ ተክሌ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዘው ሀረር ገቡ። ከዚያ በኋላ አካባቢው በርግጠኝነት የኢትዮጵያ ግዛትነቱ ታውቆ፤ በአምስቱም የጀጎል በሮች ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዲሰቀል ሆነ። 3ሺህ ወታደሮችም ከራስ መኮንን እንዲቀሩ አድርገው፤ ክልሉ እንደገና በኢትዮጵያ መንግስት ስር ይተዳደር ጀመር።
አጼ ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፤ የማረኩትን የግብጽ ወታደሮች አልገደሏቸውም። ይልቁንም ግብጾቹ የአሚር አብዱላሂን ጦር ለማበረታት ወታደራዊ ማርሽ ያሰሙ ነበር። አሁንም የምኒልክ ጦር በድል አድራጊነት ወደ አዲስ አበባ ሲገባ፤ አጼ ምኒልክ እነዚህኑ የጦር ሙዚቀኞች ታምቡር እያስመቱና ጥሩንባ እያስነፉ በወታደራዊ ስነ ስርአት አዲስ አበባ ሲገቡ ህዝቡ ግራና ቀኝ ተሰልፎ በታላቅ ደስታ እና እልልታ ተቀበላቸው። ያንጊዜ ታዲያ ማርከው ያመጡት ግብጾቹን ብቻ ሳይሆን፤ ለማዳ እርግቦች በሽቦ ቤት ያሉ እርግቦች እና ትላልቅ ሰሎግ ውሻዎች ጭምር ነበር። ያኔ ታዲያ እንዲህ ተባለ…
የምኒልክ ነገር፣ ይመስለኛል ተረት፤
አሞራው በቀፎ፣ ውሻው በሰንሰለት።
ይህ የሆነው የካቲት 28፣ 1879 ዓ.ም. ነው። እንግዲህ ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው እውነት ይህ ሆኖ ሳለ፤ የአካባቢው ሰዎች “ክልላችንን የጦር ካምፕ አደረጉብን” በማለት ምኒልክን እንደጨፍጫፊ እና ተስፋፊ ሲያዩ “እንቁላል ለመጥበስ መጀመሪያ ቅርፊቱን መስበር ያስፈልጋል” ከማለት ሌላ ብዙም የምንለው አይኖርም። ይልቁንስ ከአስር አመታት በፊት ይመስለናል… በዚሁ ኢቲቪ የተመከትነው አንድ ለቅሶ ነበር። ስለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል፤ ምኒልክ እና አሚር አብዱላሂ ጦርነት ያካሄዱበት ጨለንቆ ድረስ ሄደው፤ መሬቱን ቆፍረው የሟቾችን አጽም ከመቶ አመት በኋላ በማውጣት፤ “ምኒልክ የጨፈጨፏቸው…” ብለው ደረት እየመቱ ሲያለቅሱና ሲያስለቅሱ አይተን፤ “ወይ ታሪክ!?” ብለን ያለፍንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።
በሱማሌ ክልል የተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እና በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰው ውርደት ምን ያህሉን ሰው እንዳበሳጨው ለማወቅ ያስቸግራል። እኛ ግን እንላለን… “የአካባቢው ሰዎች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ወይም ታሪካችንን እና ማንነታችንን አያውቁም ማለት ነው። ሰው ሱማሌ፣ ኦሮሞ ወይም አማራ ስለሆነ አዋቂ አይሆንም። አገር እና ብሄር ሰውን አይለውጥም፤ ትምህርት ግን ሰውን ይለውጣል” ስለዚህ አሁንም ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለን የጋራ ታሪካችንን እንጨዋወት፤ በዚያው እንማማር፤ እንለወጥ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይህ አካባቢ ከጥንት ጀምሮ በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ተይዞ የነበረ ክፍለ ግዛት ነው። በ10ኛው ክፍለዘመን የሱማሌ ነገድ ከታጁራ ቤይ ተነስቶ መስፋፋት ሲጀምር የኦሮሞን ህዝብ እየተገፋ፤ በዋቢ ሸበሌ እና ጁባ ወንዝ መሃል በሚገኘው ቤናዲር በሚባለው ቦታ ላይ እንዲቆይ አድርጎት ነበር። በኋላም ኦሮሞዎቹን… ከታች የባንቱ ህዝብ ከላይ ሱማሌ ሲያስቸግራቸው ወደ ወላቡ፣ አበያ፣ ባሌ ድረስ ዘልቆ ራሱን በገዳ ስርአት እያደራጀ ቆይቶ፤ የግራኝ አህመድ ልጅ ወራሽ የሆነውን አሊ ኑርን ሐዘሎ ላይ ገጥሞ በ1551 ዓ.ም. እስከሚደመስሰው ድረስ በመሃል ብዙ ታሪኮች አልፈዋል። ከ10ኛው እስከ20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አካባቢው በዚህ አይነት ምስቅልቅል ውስጥ ነው የቆየው።
በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የነበረው ምስቅልቅል እንዳለ ሆኖ፤ በተለያዩ ጊዜያት ከሱማልያ ግዛት የጦር መሳርያ ይዘው በመግባት፤ የኦሮሞውን ህዝብ በመግደል እና ከብቱን በመዝረፍ፤ ህዝቡን በማፈናቀል ብዙ ግፍ ተሰርቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ክልል፤ በሌሎች ላብ እና ደም የተገነባ ክልል ነው። ይህን በማለት ወደኋላ ተመልሰን የምንቀይረው ነገር የለም። ሆኖም የማያውቁትን ወይም እያወቁ ሊያውቁ የማይፈልጉትን አንዳንድ ነገሮች ብናስታውሳቸው ክፋት የለውም።
በምኒልክ ዘመን ከተፈጠሩት አኩሪ ገድሎች መካከል የአድዋ ጦርነት አንደኛው ነው። ይህ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በጦር ተማራኪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ምኒልክ ዘንድ ምርኮኞችን አቀረቧቸው። ምኒልክ ምርኮኞች እንዲገደሉ አላደረጉም። ፈረንጅ ተማራኪዎችን ወደ አዲስ አበባ ይዘው ሲመለሱ፤ በኤርትራ እና በሱማሌ ተወላጆች ላይ ለየት ያለ ፍርድ ሰጡ። “ከአውሮፓ ወራሪ ጋር ሆነው የገዛ ወገናቸው ላይ ጥይት መተኮሳቸው ያሳዝናል። አሁንም ቀሪው ህዝብ እነሱን እያየ እንዲማር፤ ተንበርክከው የተኮሱበት ግራ እግራቸው እና ቃታ የሳቡበት ቀኝ እጃቸው ይቆረጥ።” ብለው ፈረዱ እንጂ አልገደሏቸውም።
ወደ አሁኑ የሱማሌ ክልል ልውሰዳቹህ። አካባቢው በ1879 ነጻ ከወጣ በኋላ ህዝቡ በሰላም መኖር ቢጀምርም፤ ኦሮሞዎቹ መሬት እና ከብታቸውን መነጠቃቸው ሊቆም አልቻለም። በወቅቱ የነበሩት የአካባቢው ኦሮሞዎች በተደጋጋሚ በሚደረግባቸው የድንበር ውጊያ ምክንያት ከብቶቻቸውን እየተዘረፉ፤ መሬታቸውን እየተነጠቁ፤ የሞቱት ሞተው፤ የቀሩት አካባቢውን እየለቀቁ ወጡ። ባለንበት ዘመን ደግሞ ሰዎቹን ብቻ ሳይሆን የሰጡትን ስያሜ ጭምር ሊቀይሩት ሲጥሩ ተመለከትን። ለምሳሌ “ጅጅጋ” ማለት በኦሮምኛ “ዝቅ ዝቅ” እንደማለት ነው (የአካባቢው ከፍታ ዝቅ ያለ በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው)። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ጅጅጋ” ማለታችውን ትተው “ጅግጅጋ” በሚል መጤ ስያሜ ለመቀየር እና አዲስ ስም ለመስጠት የሚሯሯጡ ሰዎችን ታዝበናል።
የቅርቡን ታሪክ ትተን… እንደገና ወደኋላ እንመለስ። ይህ ሁሉ ግፍ በኦሮሞዎቹ ላይ ሲሰራባቸው፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዝም አላሉም። ይልቁንም በራስ መኮንን አስተዳደር ወቅት… የሱማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦችን በሚያጣሉት የድንበር ቦታዎች ላይ በሙሉ፤ ነፍጥ የያዙ ወታደሮች ተመደቡ። በኋላ ክልሉን ለቀው ሊሄዱ ሲሉ፤ ህዝቡ እንቢ ብሎ መሬት እየሰጠ፤ ልጆቻቸውን እየዳሩላቸው ኑሯቸውንም እዚያው አደረጉ። እነዚህ ነፍጥ አንጋቾች ወይም ነፍጠኞች…. አብዛኛዎቹ ከሰሜን ሸዋ የተውጣጡ ጎበዝ አልሞ ተኳሾች ነበሩ። ሱማሌው እንደለመደው የኦሮሞውን ከብት እና እርሻ ለመዝረፍ ድንበር እያለፈ ሲመጣ፤ በጥይት እየለቀሙ ስርአት አስያዙት። የ85 አመት አዛውንት የሆኑት አቶ ሉልሰገድ ጎበና የሚነግሩን ቁም ነገር አለ… ቀደም ሲል በ1879 ምኒልክ ድል ሲያደርጉ እነሻቃ ተክሌን ሰንደቅ አላማ አስይዘው ወደሃረር መላካቸውን ተጨዋውተን ነበር። (የሻቃ ተክሌ ልጆች ደግሞ ፊታውራሪ ዝቅ አድርጌ እና ግራዝማች መኩሪያ ብዙ ታሪክ ያላቸው ጀግኖች ናቸው።) የሻቃ ተክሌ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ ናቸው – አቶ ሉልሰገድ። በወቅቱ ልጅ ነበሩ። በአያታቸው ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ። የነገሩኝን ዝርዝር ታሪክ ሰብሰብ አድርጌ ላስነብባችሁ። እንዲህ አሉኝ… “በኋላ ላይ አያቴ ግራዝማች መኩርያ ተክሌ ወደ ጅቡቲ ድንበር አስተዳዳሪ ሆነው ተመደቡ። ከአፋሮች ጋር ጥሩ ወዳጅ ሆነው ነበር። ሱማሌዎቹ ተደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሲዘልቁ፤ አፋሮቹ መጥተው ይነግሯቸዋል። ከዚያም ግራዝማች ሱማሌዎቹን እየተከታተሉ ይቀጧቸው ነበር…” እኚህ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ኑሯቸውን እዚሁ አድርገው፤ እስከ2ኛ የጣልያን ወረራ ድረስ ዘልቀዋል። ከጣልያን ጦርነት በኋላ ኤጄርሳ ጎሩን አስተዳድረዋል። በዚህ አይነት ወልደው እና ከብደው የኖሩትን ሰዎች ነው ታድያ… ዛሬ በብሄር ብሄረሰቦች ሽፋን የሚሰድቧቸው።
“ክልላችንን የጦር ካምፕ አደረጉት” አልነበር የተባለው? እንግዲያው ሌላም ታሪክ እንጨምር። በ1953 ዓ.ም. በዋርዴር እና በገላዲን አካባቢ የሱማሌ ጦር በወገናችን ላይ ጉዳት ሲያደርስ፤ በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የ3ኛ ክፍለ ጦር አንድ ሻምበል ተንቀሳቅሶ ድል ተጎናጽፎ ነበር። በዚያው አመት ጄነራል አማን አምዶም ቡርበርዴን እና ቡክሲን አልፎ ሲመጣ… በጥቂት እግረኛ፣ መድፈኛ እና ፓራ ኮማንዶ ወታደሮች ወሰን አልፈው የመጡ የሱማሌ ወራሪዎችን ደምስሠዋል። ኢትዮጵያውያን በዚህ የኦጋዴን በርሃ የተሰዉት አካባቢውን የጦር ካምፕ ለማድረግ ሳይሆን ህዝቡን ከወራሪ ለመጠበቅ መሆኑን ለማወቅ ዲግሪ መጫን አይኖርብንም። በዚህ የምስራቁን ድንበር በማስከበር ላይ ከተሰማሩት ጀግኖች መካከል፤ በኦጋዴን በርሃ የእድሜውን ማምሻ የጨረሰውን ጀግናው አብዲሳ አጋን መጥቀስ ያስፈልጋል። የሱማሌ ባህል እና ብሄራዊ ማንነቱ እንደተከበረ ሆኖ፤ የኢትዮጵያውያን የህይወት መስዋዕትነት ሊዘነጋ አይገባም።
ዘንድሮ በሱማሌ ክልል የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር፤ ሌላውን ብሄር በመሳደብ ከሚከበር ይልቅ… ሌላው ብሄረሰብ ለዚህ ክልል ያደረገውን መልካም ነገር በማስታወስ፤ ታሪካቸውን በማወደስ… ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚያከብሩበትና የሚያመሰግኑበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆን ነበር። ይህ ግን ሳይሆን ቀረና፤ የትላንቱ ታሪክ ተረስቶ… ጆሯችን የስድብ ውርጅብኝ ለማዳመጥ በቃ።
እሩቅ ባልሆነው በትላንት ታሪካችን… አካባቢው በሱማሌ ወራሪ ሃይል ሲያዝ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ስንብት እናደርጋለን። በወቅቱ የሱማሌ ጦር ከራሽያ ያገኘው የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ነበር። ይህን ሃይል በመያዝ በምስራቅ በኩል እስከ አዋሽ ያለውን የኢትዮጵያ መሬት ለመያዝ በቅተው ነበር። በገላዲን፣ በጅጅጋ፣ በደገሃቡር፣ በቀብሪደሃር፣ በጎዴ… እስከ ድሬዳዋ ድረስ የሱማሌ ጦር በምድር እና በአየር እየታገዘ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ወርሯል። ይህ ሁሉ ወረራ ሲደረግ ታዲያ… የሱማልያ ጦር ዝም ብሎ… መንገዱ አልጋ ባልጋ ሆኖለት አይደለም የገባው። በያንዳንዱ ግንባር የኢትዮጵያ ወታደሮችን እየገደለ፤ ሰላማዊ የሆነውን የአካባቢውን ነዋሪ እየጨፈጨፈ ነበር – ድሬዳዋ ድረስ የዘለቀው።
እነዚህን ሁሉ አካባቢዎች መልሶ በማጥቃት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። በአካባቢው የነበረው 3ኛ ክፍለ ጦር እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል የፈጸሙት ታላቅ ጀብዱ ምንግዜም በታሪክ የሚወደስ ነው። F-5 ተዋጊ ጀቶች ከደብረዘይት እየተነሱ የሱማሌን እግረኛ በመትረየስ ሲረመርሙት፤ እግረኛው የኢትዮጵያ ጦር ደግሞ ሱማሌውን እግር በ’ግር እየተከተለ መግቢያ ያሳጣው ነበር። ከአየር ኃይል አብራሪዎች መካከል እነሜ/ጄነራል አምሃ ደስታ፣ ሜ/ጄነራል ፋንታ በላይ፣ ኮ/ል አስማረ ጌታሁን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ደምሴ ቡልቶ እና ሌሎች… ከምንም በላይ ደግሞ በዚህ ጦርነት ላይ ህይወታቸውን እና አካላቸውን ያጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ ለኢትዮጵያ ሲሉ ከየመን የመጡ መድፈኞች እና የኩባ ወታደሮች ጭምር፤ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለአንድ አፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም – ክብር ለነሱ ይሁን።
ኦጋዴን እና አካባቢው “ራሴን አስተዳድራለሁ” ብሎ ስራ መጀመሩ ደስ ያሰኛል እንጂ፤ ማንንም አያስቆጣም። ነገር ግን አሁን ያለው አይነት ጥላቻ፤ የአንድ መጥፎ ነገር አመላካች ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ለዚያ አካባቢ ህዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የማንሰጠው ከሆነ፤ በርግጥም ችግር አለ ማለት ነው። አንዳንድ የሱማሌ ኢትዮጵያ ሰዎች ሌላውን ብሄር እንዲህ የሚጠሉት ከሆነ፤ “ምናለበት ታላቂቱ ሶማልያ በገዛችን ኖሮ?” የሚል አንደምታን ይፈጥራል።
በኦጋዴን ወይም በሱማሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ሲከበር፤ በአካባቢው ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆች በማቀፍ በልዩነት ውስጥ አብረው መኖራቸው እንደጥሩ ምሳሌ ማሳየት ይቻል ነበር። በብሄር ብሄረሰቦች በአል ሰበብ… ሌላውን ህዝብ ከመሳደብ ይልቅ፤ ስለመስዋዕትነቱ ማመስግን ምንም ክፋት የለውም። ህዝብን ማመስገን ባንችል እንኳን፤ ምናል አምላካችንን ብናመሰግን? አምላክን በትንሹ ማመስገን ካልቻልን ያለንን ያሳጣናልና ተመስገን ማለትን እንወቅበት።
የማመስገን ነገር ከተነሳ አንድ የስንብት ታሪክ እናውጋ።
እኚህ ሰው… በኢትዮ-ሶማልያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪ ነበሩ። በአየር ላይ ሆነው፤ የሱማሌ ተዋጊ ጀቶች ከፊት እና ከኋላ ሲመጡባቸው፤ በአየር ላይ እየተታኮሱ ቆይተው እሳቸው አቅጣጫቸውን ቀይረው ሲምዘገዘጉ፤ ሁለቱ የሱማሌ የጦር ጀቶች እርስ በርስ እንዲጋጩ አድርገው… ጸጥ አሰኝተዋቸዋል። እኚህ የአየር ኃይል አብራሪ በኋላ ላይ የሚያበሩት ጀት ተመትቶ እሳቸው በፓራሹት ወርደው ህይወታቸው ተረፈ። ሆኖም በሱማሌዎች መማረካቸው አልቀረም። ከሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በሱማሊያ እስር ቤት ለአስራ አንድ ከታሰሩ በኋላ ተፈቱ። በእስር ህይወታቸው ያጋጠማቸውን ነገር ሲያጫውቱን እንዲህ አሉ።
“የታሰርኩት በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ነው። እጅ እና እግሬ በካቴና ታስሯል። ከላይ ጣርያው ስለተሸፈነ የጸሃይ ሙቀትን እንጂ ብርሃኗን አይቼ አላውቅም። ወደውጭ የሚያወጡኝ ከጨለመ በኋላ በመሆኑ፤ ቀስ በቀስ የአይኔ ብርሃን ደከመ። እንዳልሞት ያህል ጥቂት ምግብ እና ውሃ ይሰጠኝ ነበር። በዚህ አይነት ለብዙ አመታት ስቆይ አምላኬን አማርሬው አላውቅም። አንድ ቀን ግን አምላኬን አማረርኩት። ‘ለምን እንዲህ ታሰቃየኛለህ?’ ብዬ በአምላኬ ላይ አዘንኩበት። የዚያኑ ቀን የነበርኩበትን እስር ቤት ለመጎብኘት አንድ የሱማሌ ወታደራዊ መኮንን መጣ። መኮንኑ እንደመጣ… እኔ ከጨለማው እስር ቤት እንድወጣ አዘዘ። ከዚያም እጅ እና እግሬ እንደታሰረ እሱ ፊት ቀረብኩ። የሱማሌው መኮንን እጅ እና እግሬ የታሰረበትን ሰንሰለት አይቶ ተቆጣ።”
“እንደዚህ አይነት ከፍተኛ እስረኛ እንዲህ ነው የሚታሰረው?” ብሎ አፈጠጠባቸው። አሳሪ ወታደሮች ግራ በመጋባት ዝም አሉ። እኔም አምላኬ ለቅሶዬን ሰማ። በእጆቼ እና በእግሬ ላይ የታሰረው ሰንሰለት ሊፈታልኝ ነው።” ብዬ ደስ አለኝ።
“የጦር መኮንኑ ቁጣውን ሳይቀንስ ሰንሰለቱን ፍቱ።” አላቸው። ከብዙ አመታት በኋላ ሰንሰለቱ ተፈታልኝ። የሱማሌው መኮንን አሁንም እየተቆጣ… “እንዲህ አይነት ከፍተኛ እስረኛ የሚታሰረው እንደዚህ ነው።” ብሎ… ቀኝ እጄን፣ ከቀኝ እግሬ ጋር፤ ግራ እጄን ደግሞ ከግራ እግሬ ጋር እንዲታሰር አዘዘ፤ እንደትእዛዙም ሆነ። በዚህ አይነቱ አዲስ አስተሳሰር… ቢያንስ ቆሜ እሄድ የነበርኩት ሰው አጎንብሼ ቀረሁ። በፊት እጅና እግር ለየብቻ በታሰሩበት ወቅት እንደልቤ እተኛ ነበር። አሁን ግን ለመተኛትም ተቸገርኩ። በፊት የነበረው አስተሳሰር ናፈቀኝ። ያንን ሁሉ አመት ስታሰር አንድም ቀን አምላኬን አማርሬው የማላውቀው ሰው፤ አሁን እርሜን አንድ ቀን ባማርር የባሰ ነገር መጣብኝ።” በማለት… ሰው ባለው ነገር ማመስገን እንዳለበት አስተምረውና
No comments:
Post a Comment