Feb 13, 2013

በኢህአዴግ ዉስጥ በተፈጠረዉ የስልጣን ሽኩቻ የትግራይ ክልል የመገንጠል አደጋ አንዣቦበታል


ኢሳት ታማኝ ምንጮቸን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በኢህአዴግ ዉስጥ የተፈጠረዉ የስልጣን ሽኩቻ እየከረረ መጥቶ ዛሬ ከከፋ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን ፤ ይህንን ተከትሎ ስልጣኑ ከህወሓት እጅ የሚያመልጥ ከሆነ ህወሓት ትግራይን ሊገነጥል ይችላል ብሏል፡፡
ኢሳት በዘገባዉ የአቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተቀባይነት አጥቷል ያለ ሲሆን ፤ ኦህዴድና ብአዴን አቶ ሔይለማርያምን የህወሓት አገልጋይ ናቸዉ በማለት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለእኛ ይገባል ሲሉ ከረር አድርገዉ እየተሟገቱ ይገኛል ብሏል፡፡
ሆኖም ህወሓቶች በበኩላቸዉ ከፊትም ከኃላም ሆኖ አገሪቱን የመምራቱ ጉዳይ የእኛ ነዉ በማለት አሻፈረኝ ብለዋል ያለዉ ይህ የኢሳት ዘገባ ስልጣን ከህወሓቶች የሚወጣ ከሆነ ህወሓት ትግራይን የመገንጠል ፕሮግራሙን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል ሲል የግጭት ተንታኝ ቡድንን ጠቅሶ አትቷል፡፡
ኢሳት በዘገባዉ እንደገለፀዉ ህወሓቶች አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝን ከፊት በማድረግ ከኃላ በመሆን ስልጣኑን የማስጠበቅ ስልት ሊከተሉ የነበረ ቢሆንም አሁን በቅርቡ አቶ ሐይለማርያምን ከፊት ማምጣት ለምን አስፈለገ ፣ እኛ ከፊትም ከኃላም በመሆን ሀገሪቱን መምራት ይገባናል የሚል ሀሳብ የሚያራምድ ተቃዋሚ ቡድን ከመሀከላቸዉ ተነስቷል፡፡  ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ብርሃነ ገ/ክርስቶስና አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖ  ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጭተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ የተጠቀሱትን ሰዎች ወደ ስልጣን መምጣት የማይቀበል በአቶ ስብሀት ነጋ የሚመራ 3ኛ ቡድንም በህወሓት ዉስጥ ተፈጥሯል ያለዉ ይህ የኢሳት ዘገባ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት የመከላከያ ኢታማጆር ሹም የሆነዉን ሳሞራ የኑስን ፣ ጌታቸዉ አሰፋን… ለመያዝ በሰፊዉ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብሏል፡፡
ኢሳት አያይዞ በዘገባዉ እንደገለፀዉ ይህን መሰል መከፋፈል በህውሀት ዉስጥ ከመፈጠሩ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታና የኢህአዴግ ሊቀመንበርነቱን ለተለያዩ ከህወሓት ቡድኖች ለሚወጡ ሰዎች በመስጠት ልዩነቱን ለማቻቻል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ፤ ብአዴንና ኦህዴድ ግንባር በመፍጠር ከእንግዲህ በኃላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለህወሓቶች መሰጠት የለበትም ፤ ይልቁንም ለብአዴን ወይም ለኦህዴድ መሆን አለበት ሲሉ አሻፈረኝ ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment