Mar 29, 2013

! ….. ‘ህወሓት ለህዝብ ሮሮ ጀሮ የለውም’ …!


ህወሓቶች በ9ኛው የኢህኣዴግ ጉባኤ ተሸማቀው መመለሳቸው ተሰምተዋል። በሁሉም የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች
ኣለመተማመንና እርስበርስ መናናቅ ቢስተዋልም ህወሓቶች የለመዱቱን ‘ክብር’ በመነፈጋቸው (የሚያቀርቡት ሓሳብ ሲብጠለጠል በማየታቸው) እጅግ እንዳዘኑና እንዳፈሩ ለማወቅ ተችለዋል።

ድሮም ቢሆን እነዚህ ተራ የህወሓት ኣባላት (የኣሁኑ መሪዎች ማለቴ ነው) ከሌሎች የድርጅት መሪዎች በቀጥታ (የሓሳብ) ክርክር ኣድርገው ኣያውቁም። በመለስ በኩል ነበር የሚገናኙ። መለስ ለየብቻቸው ያሳምናቸው ነበር። ኣሁን ይሄን ሚና የሚጫወት የለም። እናማ ህወሓቶች ተንቀናል (ተሰሚነት ኣጣን) ብለው ኣኮረፉ፣ ኣፈሩ። በትክክል ውርደት ነው። ኣንድ ተሳታፊ ‘ ቢስቢስ እኮ አሎምና’ (ትግርኛ) ብለዋል።

እንደዉጤቱም ከጉባኤው መልስ በትግራይ በኣብዛኛው የክልል መንግስት መስርያቤት በስብሰባ ተጠምደዋል። ትናንት (ሓሙስ መጋቢት 19, 2005) የመንግስት ሰራተኞች ስራቸው ትተው ስብሰባ ዉለዋል። የመንግስት ስራ ትተው ለፓርቲ ስብሰባ መጥራት ተገቢ ኣልነበረም።

እነሱ ስልጣናቸውን የሚያራዝሙበት ስብሰባ (የህዝብ ጅንጀና) ሲያካሂዱ ህዝቡ (ተገልጋዩ) ግን የፍትሕ ግልጋሎት ኣጥቶ ሲሰቃይ ማየት ያሳዝናል።

የመኾኒ ነዋሪዎች መኖርያ ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸዋል። በቅርብ ግዜ ወደ 7 ሺ ቤቶች ይፈርሳሉ (ገጠሩ ጨምሮ መሆን ኣለበት እንጂ 7ሺ ቤቶች በመኾኒ ከተማ ይኖራል ብዬ ኣልገምትም)። በመጀመርያ ዙር 1500 ቤተሰብ ይፈናቀላል። ይቀጥላል።

እነዚህ ነዋሪዎች መኖርያ ቤታቸው ሲፈርስ ሌላ ኣማራጭ መጠልያ ስለሌላቸው መንግስት መፍትሔ እንዲያፈላልግላቸው ለወረዳው ኣስተዳዳሪዎች ኣቤት ብለው ነበር። መትፍሔ ኣላገኙም። ችግሩ ያስጨነቃቸው ነዋሪዎች ከ150-200 የሚሆኑ ተወካዮች መርጠው ወደ ክልል መንግስት ቢሮ (መፍትሔ ፍለጋ) ላኩ።

የክልል መንግስት ሓላፊዎች ወደ ወረዳቸው እንዲመለሱ ያዛሉ። ‘የወረዳ ኣስተዳዳሪዎችማ መፍትሔ ሊሰጡን ኣልቻሉም፣ ለዚህ ነው ወደ ክልል የመጣነው።’ ተወካዮቹ ይመልሳሉ። የክልሎችም ‘እኛ የምናውቀው ነገር የለም’ በሚል ከኣከባቢው እንዲርቁ ያስገድዷቸዋል።

የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምንድነው? “ኣንደኛ ቤታችን የሚፈርሰው ኣለኣግባብ ነው። ሁለተኛ መኖርያችን መንግስት በሃይሉ የሚያፈርሰው ከሆነ ሌላ ኣማራጭ መጠልያ ልያዘጋጅልን ይገባል።” ይላሉ። በተጨማሪም “መንግስት ለውጭ ዜጎች (ለምሳሌ የኤርትራ ስደተኞች) መጠልያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ የተለያዩ ነገሮች ሲያዘጋጅላቸው ለኛ (ለዜጎቹ) ግን ያለ ምንም ኣማራጭ መኖርያችን ለማፍረስ እየተዘጋጀ ነው” ብለው ይከሳሉ።

የክልል ባለስልጣናት መፍትሔ ስላልሰጡዋቸው (ባለስልጣናቱ ለግል ወይ ፓርቲ ስብሰባቸው እንጂ) ለህዝብ ፍትሕ ወይ ግልጋሎት ደንታ ስለሌላቸው ተወካዮቹ ወደ ዓረና ትግራይ ፓርቲ መስራቤት በመሄድ ጉዳያቸውን ማስረዳታቸው ሰምቻለሁ። ሰዎቹ ከመኾኒ- መቐለ ለሳምንት ያህል መመላለሳቸው ገልፀውልኛል። የመንግስትም የግልም የሚድያ ሽፋን ኣለማግኘታቸው ያሳዘናቸው ይመስላል። በመጨረሻም ‘ህወሓት ለህዝብ ሮሮ ጀሮ የለውም’ የሚል ኣስተያየት ሰንዝረዋል።

እባካቹ ህወሓቶች ከመንግስት ስራ የፓርቲ ስብሰባ ኣታስቀድሙ። የመንግስት መስራቤትም ለፓርቲ ስራ ማዋል ሙስና ነው። የፓርቲና የመንግስት ስራ የተለያዩ ናቸው። ቅድምያ ለህዝብ ስጡ። ያለ ህዝብ ስልጣን የለም፣ ሃብት የለም፣ ‘መከበር’ የለም። ሁሉም ነገር የሚያደረው ህዝብ ነው።

ለህዝብ ቅድምያ እንስጥ።

It is so!!!

Mar 28, 2013

“ሀገሬ ገመናሽ” (ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ ክፍል ሁለት)



በየፍርድ ቤቶችሽ የፍትህ ውርጃ ሲፈፀም ዝም አልሽ።
ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ
ልዕልና ጋዜጣ
ምንጭ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ብሎግ
በቀደም ሳት ብሎኝ፣
ለመጀመሪያ ልጄ ብቻ የፈረንጅ ሸራ ጫማ ገዝቼ ገባሁ። ያለወትሮዬ ማለቴ ለወትሮው ገበያ የምወጣው ሁለቱንም ልጆቼን ይዤ ስለነበረ ነው። ታዲያ ያን እለታ ማታ ትልቅዋ ልጄ ጫማውን ስትለካ፣ የታናሽ እህትዋ አይን ከሚለካው ጫማ ጋር ሲንከራተት ተመለከትኩ፤ ወይም የተመለከትኩ መሰለኝ። ‹‹ከወደድሽው ላንቺም ይገዛልሻል››አልኳት፤ የትንሽዋን ልጄን አይን እየሸሸሁ። በውስጤ አድሏዊነት ተላወሰ። በልጅትዋ ህሊና ውስጥ ይህ ስሜት እንደማያድር ባውቅም፣ የእኔን ሃሳብ ግን ቶሎ ላስወግደው አልቻልኩም። አየሽ ሀገሬ? እንኳን ህዝበ አዳምና ሔዋንን በእኩልነት ቤት ሆኜ አኖራለሁ የሚል ሀገር፣ አንድ ተራ ምስኪን ወላጅ እንኳን በጎጆው አድሏዊነት እንዳይሰፍን ይጥራል። አንቺ ግን ሀገሬ! … አንቺ ግን ዝሆንና ጥንቸል እያፋለምሽ ለአሸናፊው ታጨበጭቢያለሽ፤ ትሸልሚያለሽ።
መቼም ማንም ቢሆን፣ የአደባባይ ውበቱን እንጂ የጓዳ – ጎድጓዳ ገመናውን ሲነግሩት አይወድምና አንቺም ከአደባባይሽ ጀርባ መዝለቄ እንደማይጥምሽ አውቃለሁ። አደባባዮችሽማ ለዜጎችሽ የጋራ ፍትሀዊ መኖሪያነትሽን ይመሰክሩልሻል። መቼም የዜጋ ሁሉ እኩልነት የሚረጋገጠው በህግ ፊት ባለው እኩል መብት አይደል? ይህ ደግሞ ከገጠር ቀበሌሽ አንስቶ እስከ መዲናሽ ባሉ አደባባዮችሽ የሚታይ ነው። የወረዳ ፍርድ ቤት፣ የዞን ፍርድ ቤት፣ የክልል ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ፍርድ ቤት፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰበር ሰሚ ችሎት… የፍትህ ቢሮ… ይህ ሁሉ አደባባይሽን ያደመቅሽበት የዜጎችን እኩልነት ማስጠበቂያ ተቋም ነው። ሀገሬ! ለመሆኑ በእነዚህ ተቋማት ምን እያደረግሽ እንዳለሽ ታውቂያለሽ?
አንዳንዴ ሳስበው ፍርድ ቤቶችሽና የፍትህ ተቋማቶችሽ ለዜጎች እኩል ያለመሆናቸውን የምታስታውቂበት ስፍራ ይመስለኛል። ይህን ስትሰሚ እንደምትቆጪ አውቃለሁ። ገመናው ሲሸፈንለት እንጂ ሲገለጥበት የሚወድ ማን አለ! አሁን እስቲ አንቺ ህግ አቁሜያለሁ፣ ዳኛ ሰይሜያለሁ ትያለሽ? ሀገሬ ሙች አፍሽን ሞልተሸ አትይም። ምነው ብትይ እማኝ ጠቅሼ እሞግትበት ሞልቶኛል።
አንድ አትዮጵያዊ ለትምህርት ውጭ ሄዶ ሳለ፣ በፈቀድሽው ከታክስ ነፃ መብቱ ተጠቀመና አውቶሞቢል ገዝቶ መጣ። አንቺንና ያቆምሽውን መንግስት እያሞገሰ አራት አመት በአውቶሞቢሉ ተጠቀመና ተመልሶ ለትምህርት ሄደ።
ባለቤቱ ደግሞ አሁንም አንቺንና መንግስቷን እያመሰገነች ስትነዳ፣ አንድ ቀን በጉምሩክ አሳሽ ጓዶች ተያዘች። መቼም ‹‹ለምን?›› ማለትሽ አይቀርም። የመኪናው ሊብሬ በባለቤትዋ ስም ስለነበር፣ አንቺ በአውቶሞቢሉ መገልገል አትችይም ተብላ፣ ተያዘች። መኪናው ታሰረ። አጣሪ ተቋቋመ። አጣሪው አጣርቶ ‹‹ባለመብቱ ባለቤትዋ በመሆኑ፣ በአውቶሞቢሉ መጠቀም መብትዋ ነው›› ብሎ ሪፖርት አቀረበ። ኮፒው ደግሞ ለሴትየዋ ደረሰ። ታዲያ ሀገሬ ጉዳዩ የቀረበለት የጉምሩክ ባለስልጣን፣ ቀረጡን ትከፍያለሽ አላት። ተያይዞ የቀረበውን ሪፖርት ተመልክቶት እንደሁ ጠየቀችው። አለመመልከቱን፣ ቢመለከተውም እንኳን ሪፖርቱ እግዚአብሔርም ቢመጣ ከመክፈል እንደማያስጥላት፤ ካልከፈለች መኪናዋ ጉምሩክ ውስጥ እንደሚታሸግበት ነገራት።  ሀገሬ፣ ሴትየዋና ባለስልጣኑ ሁለቱም ያንቺ ዜጎች፣ ሁለቱም ኢትዮጵያዊ ናቸው። ቆይ ህግሽ ላይ ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ›› የሚለው ሀረግ ማንን አስበሽ ያሰፈርሽው ነው? እና ሴትዮዋ ሃምሳ አራት ሺህ ብር ከፈለች። ከመክፈልዋ በፊት ግን ሀገሬ ሙች አልቅሳ ለምናዋለች። ከእግዚአብሔር በላይ ያስቀመጥሽውን ዜጋ መለመን እንጂ ምን መፍትሔ አለ! ባለቤትዋ ይህን ሲሰማ መጀመሪያ ያዘነው ባንቺ አይደለም። ባስቀመጥሽው ባለስልጣን ትእቢትና ድንቁርና ተደነቀ። ህግ ፊት አቅርቦ፣ ባለቤቱ በህግ የተሰጣትን መብት የሚጥስበት ከህግ የከበረ መብት እንደሌለው ሊያሳየው፣ ባለስልጣኑን ህግ ፊት ሊገትረው ከአውሮፓ ሲበር መጣ፤ ጠበቃ ቀጠረ።
በቀጠሮው ቀን እሱና ጠበቃው ማልደው ፍርድ ቤት ደረሱ። ተከሳሽ አልቀረበም። የመስሪያ ቤቱ ጠበቃ እንኳን አልቀረበም። ዳኛዋ ሌላ ቀጠሮ ሰጡ። በቀጠሮውም ቀን የቀረበ የለም። ዳኛዋ ባለስልጣኑ ፍርድ ቤቱን ማዋረዱን፣ ከአንዴም ሁለቴ በቀጠሮ አለመቅረቡን ከምንም ሳይቆጥሩ ፍርዱን ገመደሉት። ባለስልጣኑ ትክክል መሆኑን፣ ሴትየዋ መያዛቸው፣ ገንዘቡንም መክፈላቸው አግባብ መሆኑን ፈረዱ።
ሀገሬ፣ ያ ከአውሮፓ የፍትህ ጥማት ሲያበር ያመጣው ሰው፣ በፍትህ መዶሻሽ የተጨፈለቀ ዜግነቱን ይዞ ወደአውሮፓ ተመለሰ። አየሽ ሀገሬ! ለዚህ ነው የምሞግትሽ፤ እኛን ዜጎችሽን ከወባ፣ ከተስቦ ብትፈልጊም ከኤች.አይ.ቪ በላይ የጎዳን በየፍርድ ቤትሽ በህግ የበላይነት ለማያምን  ዳኛ ያስጨበጥሽው መዶሻ ነው።
እንዴ እውነቴን እኮ ነው! ሀገሬ ሙች እውነቴን ነው። ለወባው፣ ለተስቦውና ለኤች.አይ.ቪ.ው እድሜ ለቱጃሮቹ ጓደኞችሽ እንጂ፣ መች መድሀኒት ይገደናል- መርከብ ሞልተው ይልኩልናል። ደግሞ ብንሞትስ! እድር አለን እንቀበራለን። ቆይ እድር ባይኖረንስ! ደግሞ ለመቅበር! አበሻ እንኳን ሞተሽለት ገና በጣር ተይዘሽ፣ ላይ ላዩን መተንፈስ ስትጀምሪ ነው ጉድጓድ መቆፈር የሚጀምረው። ግን ሀገሬ እንዲህ በቁማችን በፍትህ መዶሻሽ ስንሰባበር፣ እነዚህ የወባና የተስቦ መድሀኒት በመርከብ ሞልተው የሚልኩልን ጓደኞችሽ አንቺንም ሆነ መንግስትሽን ሀይ አላሉልንም። እና ሀገሬ፣ ይህ የአንቺ ብቻ ሳይሆን የነሱም ገመና ነው።
ቆይ እኔ የምለው መንግስት ከህግ በላይ ነው እንዴ!? እስቲ ንገሪኝ ሀገሬ- መንግስት የሆኑት ከእኛው መሀከል፣ እንደኛው ዜጋ የነበሩት አይደሉም እንዴ! ዜጎችሽ አይደሉም እንዴ ‹‹መርጣችሁናል›› ብለው መንግስት የሆኑት! ታዲያ ለምንድነው የፍትህ መዶሻሽ እነሱ ላይ ቄጠማ የሚሆነው? ይኽው በአንቺ ውስጥ ከልጅነት እስከ እውቀት ስኖር መንግስት ከሳሽም ተከሳሽም ሆኖ ሲረታ እንጂ ሲፈረድበት አይቼም፣ ሰምቼም አላውቅም። ምን ያስቃል ሀገሬ! በእርግጥ ገንዘብን፣ ወይም ደግሞ ሌሎች ቀለል ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ አንድ ሁለት ፋይሎች በመንግስት ካሳ ከፋይነት እንዲዘጉ አድርገሽ ሊሆን ይችላል። ይህን ተይና እውነት ሀገር ከሆንሽ፣ እስቲ በሰብአዊና በዜግነት መብት ጉዳይ መንግስትን ከስሶ ያሸነፈ አንድ ዜጋ ጥሪ! እረ ጉደኛ ነሽ፣ ሀገሬ!
እኔ የምልሽ የህግ ትምህርት ቤት፣ ምናምን ምን ያደርግልሻል? ለምን አምስትና ስድስት ዓመት ህግ ታስተምሪያለሽ? ለእኛ ለዜጎችሽ ያቆምሽው፣ ህግ እንዳይዛነፍ፣ በየፍርድ ቤቱ ያስቀመጥሽው መዶሻ አናት አናታችንን እያለ ቅስማችንን እየሰበረ፣ ከዜግነት ተራ እንዳያስወጣን አይደለም እንዴ! በአንቺ በሀገሬ ህግ፣ እንኳን መርጠኽኛል፣ ያለ ባለስልጣንና መንግስት ቀርቶ፣ እየሱስ ክርስቶስም ቢሆን፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ አብሮኝ ቢኖር፣ በህግ ፊት እኩል ነን። አቦ ሀገሬ በፍትህ ስም የምትሰሪው ግፍ በዛ! የምር በዛ። ወይ በቃ የህግ ትምህርት ቤቶችሽን ዝጊና ዳኛ ለምታደርጊያቸው ዜጎች እንዴት የባለስልጣንንና የመንግስትን የስልክ ትእዛዝ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አንድ ሁለት ሳምንት አሰልጥነሽ … በቃ!
አንዳንዴ ሳስበው ያ ታከለ የሚመኘውን ምኞት እኮ ሁላችንም ልንመኘው ነው! ሀገሬ መቼም ታከለን ታውቂዋለሽ። ለነገሩ አንዳንዶቹን አውቀሽ ችላ ትያቸዋለሽ እንጂ፣ አንቺ ዜጋሽ መቼ ይጠፋሻል። እሱም አንዱ ፍትህ መከበር አለበት፤ ያለ ህግ የበላይነት ሀገርና ህዝብ አይቆምም፣ ባይ ነው። ታዲያ የውልሽ፣ ከአመት ተመንፈቅ በፊት የቢ.ፒ.አር አሰራሩን ተቃውመሀል ተብሎ ከስራ ታገደ። ሁለት ወር ያለ ስራ ደመወዝ በላ። በሶስተኛው ወር ደመወዙ ቆመ። ሀላፊውን ሊያነጋግር ሄዶ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤውን ተቀብሎ መጣ። ታዲያ ያን ሰሞን እቤቴ መጣና፣ ‹‹ገንዘብ አበድረኝ›› ሲለኝ፣ ያው እንደወትሮው ወር መዳረሻ ገዶት ይሆናል፣ ብዬ ‹‹ስንት መቶ?›› ስለው ‹‹ሰባት ሺህ›› አይለኝ መሰለሽ!? መስሪያ ቤቱን ሊከስ እንደሆነም ነገረኝ። ገንዘቡን ለጠበቃና ለአንዳንድ ተጨማሪ ወጪ ፈልጎ ነው። ባንክ በቆጠብኩት ሁለት ሺህ ብር ላይ ከባለቤቴ ቤተሰቦች አምስት ሺህ ብር ተበድሬ ጨምሬ ስሰጠው ‹‹ተው! ይቅርብህ! የመስሪያ ቤቱን ባለስልጣን የሾመው መንግስት ነው። መንግስት ደግሞ ከሶም ተከሶም ይረታል። ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስን አስብ። ቃሉ ቢለወጥም ያው መንግስት ማለት ንጉስ ነው። ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል፣ መስሪያ ቤቶችና መንግስት ያላቸው ልዩነት የተዋረድ ብቻ ነው›› አልኩት። ሀገሬ ሙች አልሰማኝም። እንዲያውም አልሰማ ቢለኝ በየመስሪያ ቤቶቻቸው የተሰየሙ ትንንሽ መንግስታትን ከሰው አቅላቸውን የሳቱ፣ ‹‹ቂጣቸውን በሳንጃ የተወጉ›› ዜጎችን በየዘመኑ ማየቴን፣ ገመናሽን ገልጬ ነገርኩት። አልሰማ ብሎ ፋይሉን በወረዳ ፍርድቤት ከፈተ።
በወረዳ ፍ/ቤትሽ የክስ ፋይል በከፈተ በአራት ወሩ የውሳኔውን ወረቀት አምጥቶ አሳየኝ ሀገሬ ሙች እልሻለሁ ገረመኝ! አንቺ እኮ ትገርሚያለሽ! የፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔ ከማህተሙና ከፊርማው ልዩነት በስተቀር፣ ያው የተባረረበት ደብዳቤ ግልባጭ ነው። አዘነ። ሀገሬ ሙች አዘነ። የፍትህ መዶሻሸ ያረፈበትን አናቱን ቀና አድርጎ መመልከት አቃተው።
ታከለ ግን የዋዛ ዜጋ አይደለም። ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል››ን እየተረተ ይግባኝ አለ። ይኽው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰው ሰርቶ በየወሩ ደመወዝ ሲቀበል፣ እሱ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች፣ የተባረረበትን ደብዳቤ እያፀደቀ ይመጣል።
እና ታከለ ምን ተመኘ መሰለሽ! ሀገሬ ሙች እንደገመናሽ ዝግናኔ የግል ፍርድ ቤት ቢመኝ አይፈረድበትም። አንድ እሁድ ቀን አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ማኪያቶ ስንጠጣ፣ ከመንገዱ ባሻገር ያለውን የግል ሆስፒታል እየተመለከተ ‹‹በህይወት ዘመኔ ማየት የምመኘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?›› አለኝ። ‹‹ምን›› አልኩት፤ ቁብ አልሰጠሁትም። ‹‹እዚያ ህንፃ አናት ላይ በግል ሆስፒታሉ ስያሜ ምትክ ‹‹ብርሃን ከፍተኛ የግል ፍርድ ቤት፣ መለያችን ይግባኝ አልባ ፍርዳችን ነው!›› የሚል ተጽፎ ማየት። ሀገሬ ሙች አያስቅም! ደግሞ ሰው እንጂ ሀገር ሲስቅም ሲያለቅስም አያምርበትም።
እውነቱን እኮ ነው! በመንግስት ፍርድ ቤት መንግስትን መርታት ካልተቻለ፣ ለምን በግል ፍርድ ቤት አይሞከርም። በቃ ሀገሬ አንቺም የፍትህ ገመናሽን መክላት ካማረሽ፣ በቃ የግል ፍርድ ቤት ክፈቺ። እና የመንግስት ፍ/ቤቶች በዜጎችሽ መካከል ያለን ክስ ይመልከቱ። በማንኛውም ሁኔታ በመንግስትና በዜጋ መካከል ያለን ክስ ደግሞ በግል ፍርድ ቤት እንዲታይ አድርጊ። ያኔ የዜጎችሽ አናት መንግስት ለዳኞችሽ ባስጨበጣቸው መዶሻ አይነደልም። ዜጎችሽ ቀና ብለው ይሄዳሉ፤ ስለፍትህ ስርአትሽም መልካሙን አብዝተው ይናገራሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንቺ ደስ ይልሻል። አንቺ ደስ ሲልሽ ደግሞ እኛም መልሶ ደስ ይለናል።
ስለፍትህ ገመናሽ ስናገር የሰሙ አንዳንድ ዜጎችሽ፣ ‹‹እንዴት ሰው፣ ከሰው ገመና አልፎ የሀገርን ገመና አንድ — ሁለት — እያለ ያብጠለጥላል!›› እያሉ ያብጠለጥሉኛል። እኔ ምን ተዳዬ! ሀገሬ አንቺ ራስሽ ገመናሽን መች ሸፈንሽውና እኔ እኮነናለሁ? እንዴ! የምር እኮ ነው የምልሽ! ገመናሽን እንደጋለሞታ ደጃፍ ገልጠሽዋል እኮ! አንቺ ራስሽ አይደለሽ እንዴ ተቃዋሚ፣ አሸባሪ፣ አክራሪ ብለሽ ዜጎችሽን ባሰርሽ ማግስት አኬልዳማ፣ ጀሀዳዊ ሐረካት– ምናምን የሚል ፊልም እየሰራሽ የፍትህ – ገመናሽን ቲቪ ያስገባሽው! እውነት ሀገሬ ያሳፍራል።
ለዚህ እኮ ነው መንግስት የገባበት ክስ የዝሆንና የጥንቸል ፍልሚያ ነው የምልሽ። ያውም ሮጣ የማታመልጥ እግርዋ የተሰበረ ጥንቸል! ሲጀመር ለመንግስት ዝሆንነትን ሰጥተሻል። ጠመንጃ አለው፤ እስር ቤት አለው፤ ቲቪ አለው፤ ራዲዮ አለው፤ ዳኛ አለው፤ አቃቤ ህግ አለው። ይህ ሁሉ ካለኝ ደግሞ እኔም ብሆን፣ ዝሆን መሆን አያቅተኝም። ተቃዋሚ፣ ሽብርተኛ፣ አክራሪ ተብሎ የተመረጠው ደግሞ ጥንቸል ነው። ጥንቸል ከዝሆን ቢፋለም እድሉ አንድ ነው- ሮጦ ማምለጥ። አንቺ ግን ሀገሬ! ጥንቸሎችሽ በፍትህ ስርአትሽ ሮጠው ነፃ የሚወጡበት የመርፌ ቀዳዳ የምታህል ቀዳዳ እንኳን እንዳትኖር፤ ክሳቸው እንኳን ወጉ ተነቦላቸው የእምነት – ክህደት ቃላቸው ሳይሰማ፣ እንዴት እንዳከረሩ፣ እንዴት እንዳሸበሩ ፊልም ሰርተሽ በቲቪ ትለቂዋለሽ። በፍትህ አደባባይ ሮጠው እንዳያመልጡ የጥንቸሎቹን እግር ስብርብር አደርገሽ ማለት ያኔ ነው! .. ኧረ በእውነት ይዘገንናል! አባቶቻቸው ተጠርጥረው ከተከሰሱበት ወንጀል ነፃ የሚወጡበትን ቀን የሚናፍቁ ልጆችን … እናቶቻቸውን.. ጎረቤቶቻቸውን… አስቢ እስቲ! አንቺ በእነሱ ቦታ ብትሆኚና ፍትህን ያስከብርልኛል ያልሽው መንግስት በተጠረጠሩብሽ ላይ፣ እንደዚያ ያለ ፊልም እያቀረበ የፍትህን ጽንስ ለውርጃ ሲዳርግ ብትመለከቺ ምን ትያለሽ! ምንስ ታደርጊያለሽ! ዳሩ አንቺ ሀገር እንጂ ዜጋ አይደለሽም። ዜጋስ ብትሆኚ እግሮችዋ የተሰበሩ ጥንቸል ሆነሽ መታገል ከማይሰለቸው ዝሆን ፊት ብትቆሚ እጣሽ ምንድነው? አቦ ሀገሬ ተይኝ! ገልጠው የማይጨርሱት ገመና አድሎሻል

ጥልያን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው

በላይ ዘለቀ ጀግና ብቻ አልነበረም፡፡ ባንዳነትን አድረባይነትን ሎሌነትን አጥብቆ ይጠላም እንደነበር ከዚህ ታሪኩ መረዳት እንችላለን፡፡ “….በላይ ዘለቀ ተኩሶ አይስትም ::ፍጥነቱ ደሞ ሲደግንና ሲተኩስ እኩል ነው ::ውጊያ ሊጀምር ሲል "እኔ ሳልተኩስ እንዳትተኩሱ " ብሎ ያዛል ::አንዳንድ ጊዜ በውጊያ ሰአት "እርስዎ እዚህ ይቆዩን " ሲሉት "ምን ?" ይላል ቁጣ እየጀመረው ::"እርስዎ ከወደቁ መሪ የለንም " ሲሉት "ወይድ ! እኔ አሮጌ ነፍጠኛ ነኝ ::"ይልና ግንባር ይጋፈጣል :: በላይ ዘለቀ እራሱ ሲዋጋ "ገምባው " ይተበባለው ጥሩንባው ይነፋል ::"ገምባው "ባንዳን ያስበረግጋል ::ጥልያንን ያብረከርካል ::
በላይ ዘለቀ የዘመኑን አስተሳሰብ በማወቁ ህዝቡን ለማስተባበር "ትልቅ ሰው " ማስፈለጉን በመገንዘቡ እሱ እራሱ ግን ተራ ሰው በመሆኑ የንጉስ ተክለሀይማኖት ሀረግ ለሆኑት ለልጅ ሀይሉ በለው ደብዳቤ ጻፈላቸው :: የደብዳቤው ሀሳብ ባጭሩ "ህዝቡን ለማስተባበር እርስዎ የበላይ ሆነው እነን የጎበዝ አለቃ ይሹሙኝና ጠላትን እንቋቋመው ::እኔም እዋጋለሁ ::እርስዎ ወደጦር ግንባር መድረስ አይኖርብዎትም ::" የሚል ነበር ::ደጋግሞ ደብዳቤ ጻፈላቸው ::ገጸበረከትም ላከላቸው ::...ጠመንጃ ሽጉጥ ዝናር ከነጥይቱ ሶስት መቶ ብርና ካባ :: ልጅ ሀይሉ በለው ለደብዳቤዎቹ አንድም መልስ ሳይሰቱ አንድ ቀን አንድ የትእዛዝ ደብዳቤ ላኩበት ::"ደብረወርቅ ገበያችንን ያለአግባብ ቀረጡብን ብለዋልና ከንግዲህ ቆቅ የሰገረ ወፍ የበረረ እንዳይደርስባቸው ::የተወሰደባቸውም ቀረጥ እንዲመለስላቸው ::"
በላይ ዘለቀ ተናደደ ::አብረውት የነበሩትን "ጎበዝ እግዚአብሄር የወለደው ሰው አለ ?" ሲል ጠየቀ :: "እግዚአብሄር ይፈጥራል እንጂ አይወልድም " አሉት :: "ንጉስስ ?" "ንጉስም እግዚአብሄር ይቀባዋል እንጂ አይወልድም ::ይፈጥረዋል እንደሌላሰው " "እኔንም ፈጥሮኛል ::ሊቀባኝ አይችልም ?" "የሱ ሀይል ካደረብዎ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ ::" "እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ለማንም አልታጠቅም ::" ተመስገን ፈንታ የበላይ ዘለቀ የቅርብ ጉዋደኛው ነበር ::አንድ ቀን ከጠላት በፊት ተመስገን ፈንታ በላይ ዘለቀን "ሸዋ ሄደን ለትልቅ ሰው እንደር ::እንሾማለን ;እንሸለማለን "አለው :: "እኔ ሰው ሆኜ ለሰው አላድርም "አለ በላይ ዘለቀ :: "ባንተ ተኩስ ;ባንተ ወኔ ;ባንዳፍታ ትሾማለኽ :: "ጀግንነት እደጃችን ድረስ ይመጣ እንደሆነ ማን ያውቃል ?" አለው በላይ ዘለቀ ::አመታት አለፉ ::
ሞረድ እጀ ጠባብ ካስመራ እሚመጣ አፈ ሾሌ ሱሪና ተመሳሳይ ኮኮት ጥንግ ድርብ ጥበብ ኩታ በቅሎ እንደተጫነች ጠመንጃ ከነሙሉ ዝናር ጥይት ...በላይ ዘለቀ ይህንን ሁሉ አዘጋጀና ተመስገን ፈንታን ጠርቶ ; "ያ የጌታ አዳር ሄደን እንሸለማለን ያልከው ይኸውና "ብሎ ሸለመው ::በአርበኝነት ዘመን ጉዋደኛሞቹ አልተለያዩም :: በላይ ዘለቀ መጀመርያ "ራስ " ብሎ የሾመው ተመስገን ፈንታን ነበር :: "እኔንስ ራስ አልከኝ ::አንተ ማን ልትባል ነው ?" አለው ተመስገን ፈንታ :: "እኔንማ እናቴ አንደዜ በላይ ብላኛለች " አለ በላይ ዘለቀ ::” ……….
የበላይ መጨረሻም ይህ ሆነ፡፡ ንጉስ ሹም ሽር አደረጉ ::በላይ ዘለቀ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በሁዋላም ከአገሬው ጋር ሆኖ ጠላትን ተዋግቶ ነጻ ያወጣው ጠቅላይ ግዛት ለራስ ሀይሉ ተሰጠ :: በላይ ዘለቀ ወዳዲሳባ ተጠርቶ ደጃዝማች ተብሎ የቢቸና አውራጃ ገዥ ሆኖ ተሾመ :: የቢቸና አውራዣ ገዥ ሆኖም ሊሰራ አልቻለም ::ከደብረ ማርቆስ ትእዛዝ እየመጣ ወረዳዎቹ ሁሉ ቀድሞ ባንዳ የነበሩ ሰዎች ተሾሙባቸው ::ብስጭት በዛበት በላይ ዘለቀ :: "ሊወጋን ነው ....እምቢ አለ ..."እያሉ ማስወራት ጀመሩ :: በቂ ካስወሩ በሁዋላ ከራያና አዘቦ ጦር አስዘመቱበት :: (ጎጃመማ በላይ ዘለቀን ወይ ይወደዋል ወይ ይፈራዋል :: ) በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ከጥቂት ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ሆነው ወደ ሳማ አምባ ሸሹ ::በላይ ዘለቀ ሸፈተ ተባለ :: ሳማ አምባ ያለ ሁለት በር የላትም ሁለቱንም በር ይዘው ሀያ አምስት ቀን ሌትና ቀን ተዋጉ :: "ምረነዋል ልቀቁት ይምጣ "የሚል መልእክት ከንጉሱ መጣ :: ከሳማ አምባ ከወረዱ በሁዋላ ተከበቡና መሳሪያቸውን ተነጥቀው እንደ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ :: በላይ ዘለቀ ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ "ምህረት " አደረጉለትና ቅጣቱ ወደ እስራት ተለወጠለት ::
መስከረም 1936 አ .ም በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ በያገሩ ተበትነው ታሰሩ :: በላይ ዘለቀና ወንድሙ እጅጉ ዘለቀ ወሊሶ በበቀለ ወያ ጠባቂነት ታሰሩ :: የበላይ ዘለቀ ምቀኖች አሁንም አላረፉለትም ::በላይ ዘለቀ ከዳ ;አመለጠ ጠፋ እየተባለ ይወራ ጀመር ::በቀለ ወያ ተያዘና "ምን ቢሰጥህ ነው የለቀከው ?"ተባለ ::"እረ እኔ አልለቀኩትም አለ :::: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀን ወደ አዲስ አበባ አመጡዋቸውና ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አሰሩዋቸው :.ያ ሰው እናምልጥ እያለ እነ በላይ ዘለቀን ይጎተጉታቸው ጀመር :: አንድ ቀን "ጠባቂዎቻችንን የኛ ወዳጆች ገዝተዋቸዋልና እናምልጥ ::በንዲህ ያለ ስፍራ እነ እገሌ መኪና ይዘው እየጠበቁን ናቸው ::"አል :: "ወንድሞቸ በየቦታው ተበታትነው ታስረው እኔ ማምለጥ ምን ያረግልኛል ?" አለ በላይ ዘለቀ :: "ፈራህ እንዴ በላይ ዘለቀ ?"አለው :: "እኔ የዘለቀ ልጅ !" በላይ ዘለቀ ወንድሙን ላከው መኪናው እተባለበት ስፍራ መኖሩን ለማረጋገጥ ::ወንድምየው በተባለበት ስፍራ መኪና አየ ::እስረኞቹና ጠባቂዎቻቸው አብረው አመለጡ ::እመኪናው ቦታ ሲደርሱ መኪናው የለም ::እንግሊዝም የለም :: ጠባቂዎቻቸው ከዚያ ሮጠው አጠገባቸው ከነበረው ጫካ ገቡና ደጋግመው ተኮሱ ::ምልክት ነው :: በላይ ዘለቀ እጠላቶቹ ወጥመድ ውስጥ መግባቱን አወቀ :: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ከዚያ እሮጠው አመለጡ :: ሰላሌ ደርሰው በቅሎ ለመከራየት ሲነጋገሩ ተከበቡ :: በላይ ዘለቀ በጦር ፍርድ ቤት ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ ፍርዱን አጸደቁት :: ጥር 1937:.በላይ ዘለቀ በስቅላት ሞተ ::እድሜው ሰላሳ አምስት አመት ነበር ::
ጥልያንን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው ::ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ ሰላሳ አምስት አመት ታስረው በለውጡ ተፈቱ::መልኩን ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ እንዲህ ብለው ይገልሱታል :: "አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል ::ከንፈሩ ከበድ ይላል ::ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ ረጅም ጣቱ መልካም ወተት የተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ ::እግረ ቀጭን ::"…………..”
ዛሬም እንደዚህ ነው…. ስንት አድርባዮችና አሰመሳዮች አለን? ኑሮአችንን በሌሎች ህልውና ላይ የመሰረትን? የአፋኝ ሥርዐት ሎሌ በመሆን የወንድሞቻችንን ደም ከንቱ ያደረግን…..?

Mar 26, 2013

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ 60 የአማራ ተወላጆችን ይዞ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ መኪና ተገልብጦ 59 ሰዎች ሞቱ


መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ከአካባቢው ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አደጋው የተፈጠረው፣ ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው መኪና ትክሻ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ጀዴሳ በሚባል ወንዝ ውስጥ ገብቶ ነው።
ከትናንት ወዲያ በተፈጠረው አሰቃቂ አደጋ ለሞቱት ሰዎች የደረሰላቸው ሰው አለመኖሩን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገልጽ የፈለጉ ተፈናቃይ አርሶደሮች ተናግረዋል።
ከሞቱት መካከል ህጻናትና ሴቶችም ይገኙበታል። በአደጋው ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
በተመሳሳይ ዜናም በዛሬው እለት በርካታ አርሶ አደሮች በክልሉ ልዩ ሚሊሺያ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
የክልሉ ባለስልጣናት የሚፈናቀሉት ሰዎች በህገወጥ መንገድ ወደ ክልሉ የገቡ ናቸው ሲሉ ለአዲስ አድማስ መናገራቸው ይታወሳል።
የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን በተለከተ አስተያየታቸውን የሰቱት የሕግ ባለሞያ አቶ ግዛው ለገሠ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 32 “የመዘዋወር ነፃነት” በሚል ርእስ ስር ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ፤ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት መብት እንዳለው መደንገጉን ለጋዜጣው ገልጸዋል።

የእስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ግለሰብ ብአዴን ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ሰው መሆናቸው ታወቀ

የእስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ግለሰብ ብአዴን ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ሰው መሆናቸው ታወቀ
መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ ከተካሄደው ምርጫ በፊት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ሀጂ መሁመድ ሲራጅ ሙሀመድ ኑር አባታቸው ዋግ ውስጥ ነባር የብአዴን ታጋይ የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ተፈራ ዋልዋ እና የአቶ አዲሱ ለገሰ የቅርብ ሰው እንደነበሩ ከብአዴን ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግለሰቡ በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ እንዲኮላሽ ከመንግስት ከፍተኛ ተልእኮ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና አሁንም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ለመንግስት ምክር እየሰጡ የሚገኙ ናቸው።
የግለሰቡ ታሪክ እንደሚያስረዳው ታጋይ አባታቸው ሲራህ መሀመድ ኑር እንደሞቱ ወጣቱ ሲራጅ በአቶ አዲሱ አማካኝት የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበርን እንዲያደራጁ ተመርጠው ማህበሩ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በዚህ አስተዋጽኦቸውም፣ ምንም አይነት በቂ የእስልምና እምነት ትምህርት ሳይኖራቸው የአማራ ክልል እስልምና ጉባኤ ሃላፊ ተብለው በመንግስት ከተሾሙ በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ በክልሉ ውስጥ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
በ1997 ዓም ግለሰቡ ወደ ፌደራል ተዛውረው መጠነኛ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት እንዲቀስሙ ከተደረጉ በሁዋላ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ በመሆን ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሀጂ ሙሀመድ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የክልሉን የእስልምና ምክር ቤት በከተማዋ መሀል አደባባይ ላይ በአለ አራት ፎቅ ህንጻ እያሰሩ ሳለ፣ ከህንጻው ስራ ጋር በተያያዘ ገንዘብ ማጉደላቸው በመረጋገጡ ፣ የህንጻው ስራ እስካሁን ካለመጠናቀቁም በላይ ግለሰቡ እንዳይጠየቁ ተደርጓል።
በሰቆጣ ለእናታቸው እጅግ ዘመናዊ ህንጻ የገነቡት ሀጂ ሙሀመድ፣ ሶስት የንግድ መኪኖችን ገዝተው በንግድ ስራ ላይ ከመሰማራታቸው በላይ፣ በባህርዳር፣ በአዲስ አበባ እና በሰቆጣ የንግድ ቤቶችንና የመኖሪያ ቤቶችን በራሳቸውና በወንድሞቻቸው ስም በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ወደ ሀብታሞች ጎራ ለመቀላቀል ችለዋል።
በቅርቡ በተደረገው የመጅሊስ ምርጫ ስልጣናቸውን ያስረከቡት የ40 አመቱ ሀጂ ሙሀመድ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ ድርጅት ከፍተው መንግስትን እያማከሩ ነው።
በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም መሪዎች እና ድምጻችን ይሰማ በማለት ዘወትር አርብ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ምክር ቤቱ ነጻ አይደለም በማለት ጥያቄ ማቅረባቸው ትክክልና በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን የብአዴን ምንጮች የዋና ጸሀፊውን ማንነት በማስረጃ በማስደፍ እንደ ማሳያ አቅርበዋል። በቅርቡ የተተኩት የመጅሊስ አባላትም እንዲሁ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊና አባላት መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አያይዞ ገልጾአል።
አቶ ተፈራ ዋልዋ ብዙውን ጊዜ አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ አልፎ አልፎ በህይወት ያሉት የሀጅ መሀመድ ሲራጅን እናት የታጋይ ሲራጅ ሙሀመድ ኑርን ባለቤት እየሄዱ እንደሚጠየቁቸው ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሀጂ አል ሙሀመድ ሲራጅን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Mar 21, 2013

በደም እንደመጣን በደም ነዉ የምንወጣዉ!!! ህዉሃት





የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮችን ምዝገባ አካሂዶና ለተፎካካሪዎችም ምልክት ሰጥቶ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በቅርቡም ተፎካካሪዎች ፖሊሲያቸውንና ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት የሰዓት ድልድል አድርጎ የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሯል፡፡

ስሜት እና ቁጥር ለየቅል?
ወ/ሮ ዘርዬ በለጠ ዕድሜያቸው 39 ሲሆን የቤት እመቤት ናቸው፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ይኖራሉ፡፡ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት ለምርጫው የሰጡት ትኩረት ይህን ያህል አይደለም ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ ምርጫ ምንም ይሁን ምን በብዙኅኑ ዘንድ በውል የታወቀ አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም ምረጡ ተብለን እስከተጠየቅን ድረስ መምረጥ ተገቢ ነው ብዬ ስለማስብ እመርጣለሁ፡፡ ማንን ልምረጥ? ማን ምን ይሁን? ማን ከማን ጋር ይፎካከር? ግን ምንም መረጃ የለኝም፡፡ እኔም ፈልጌ አላጣራሁም፤›› ይላሉ፡፡

ከአንድ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ባህሪያት መካከል አንዱ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር (turn out) ማየት ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለምርጫ ከደረሱ ዜጎች እስከ 70 በመቶ ወጥተው ድምፃቸውን ከሰጡ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ሕዝቡም ለሚሰጠው ድምፅ ከፍተኛ ዋጋ መስጠቱን የሚያመላክተው የሚሰጠው ድምፅም በትክክል ይቆጠራል፣ ለውጥም ያመጣል በሚል እምነት የታጀበ ነው፡፡

የተመዝጋቢው ቁጥር በተለይ ደግሞ ተመዝግቦ የምርጫ ካርድ ወስዶ በምርጫው ዕለት ድምፅ የሚሰጠው ቁጥር ማነስና መብዛት ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታም አመላካች ነው፡፡ ድምፄ በትክክል አይቆጠርም የሚል ግምትና እምነት ካደረበት የመራጭ ካርድም ወስዶ ድምፁን መስጠት እንደ ከንቱ ልፋት ስለሚቆጥረው ሒደቱን ከቁብ አይቆጥረውም፤ አይመዘገብም፤ ከተመዘገበም ድምፅ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ድምፄ ይጭበረበራል በሚል፡፡ ወይም ደግሞ እንደ ወ/ሮ ዘርዬ ለምን እንደሚመርጥም መረጃ የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2005 ዓ.ም. በሚካሄደው የአካባቢ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ ከታኅሳስ 22 አስከ ጥር 21 2005 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ደግሞ ጊዜውን በማራዘም ጥር 24 እና 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ባካሄደው የምዝገባ ወቅት ቀድሞ ያስቀመጠው ግምትና ተመዘገበ ያለውን የሕዝብ ቁጥር አነፃፅሮ አስቀምጧል፡፡ ቦርዱ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 86 ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰው 40 በመቶ (34.5 ሚሊዮን) ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ተመዝግበው ካርድ ይወስዳሉ ብሎ የገመተው 83 በመቶ ወይም 28.5 ሚሊዮን ሕዝብ እንደነበር በመረጃ ሰንጠረዡ አስፍሯል፡፡

ቦርዱ ባካሄደው ምዝገባ 30.6 ሚሊዮን ሕዝብ የምርጫ ካርድ የወሰደ ሲሆን፣ ይኼም በቦርዱ ቀድም ሲል ከተገመተው 83 በመቶ አልፎ 88.93 በመቶ ደርሷል፡፡

ካለፉት ምርጫዎች ጋር  ሲነፃፀር ዘንድሮ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የመራጮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ምርጫ ቦርድ የመዘገበው ቁጥር እውነት ነው ወይ አይደለም በማለት በርካቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለማንሳት ምክንያት የሚሆኑ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛው ምርጫው ሊካሄድ የቀረው ጊዜ ከአንድ ወር የማይበልጥ ቢሆንም፣ በሕዝቡ ውስጥ ‹‹ምርጫ ምርጫ›› የሚሸት መንፈስ አለመኖሩ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክም ሆነ ትዊተር) በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስለ ኬንያ ምርጫ በርካታ ነገሮች ሲጽፉና ሲወያዩ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተካሄደው የኬንያ ምርጫ ለበርካታ ኬንያውያን ሞት ምክንያት የነበረ ሲሆን፣ በንፅፅር የአሁኑ ሰላማዊና ብዙም ትችት ያልቀረበበት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋን አሸንፈው ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዚዳንት የሚሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው፡፡ ስለኢትዮጵያ መጪው ምርጫ አንስቶ የሚወያይ ግን እስከዚህም ነው፡፡

በኢትዮጵያ በቅርቡ የሚካሄደው ምርጫ የመንግሥት ለውጥ የሚደረግበትና አዲስ መሪ ለማየት የሚጓጓበት ባይሆንም፣ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዋና መገለጫ የሚሆነው የሕዝብ ተሳትፎ ግን ከዋናው ምርጫም የበለጠ ክብደት ሊሰጠው በተገባ ነበር፡፡ ሕዝቡ ከክፍለ ከተማ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የቅርብ አስተዳዳሪዎቹን በቀጥታ የሚመርጥበት በመሆኑ፣ የሕዝቡ ዋና ቅሬታዎች የሆኑት የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚታዩበት የመንግሥት አስተዳደር እርከንም ነው፡፡

መንግሥት፣ ኢሕአዴግና ቦርዱ ሕዝቡ የምርጫውን አስፈላጊነት ሙሉ ግንዛቤ አግኝቶ ተመዝግቦ ከሚቀርቡለት ዕጩዎች መካከል ለመምረጥ መዘጋጀቱን እየተናገሩ ነው፡፡ አንድ ማስረጃቸውም፣ ካርድ የወሰደው የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡ ተመዘገበ በሚባለው መራጭ ቁጥር ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ግን ሕዝቡ ውስጥ ስለምርጫው ያለው ስሜት የሞተ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ሌላ ጥርጣሬ ያላቸው አሉ፡፡ በተደጋጋሚ በገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ የሚነሳበት ምርጫ ቦርድ፣ መንግሥትን (ኢሕአዴግን) ለማስደሰት ቁጥሩን ከፍ አድርጎ አለመሆኑን ምንም ማረጋገጫ የለም ይላሉ፡፡ ሕዝቡ በምርጫ ሒደት ተስፋ የቆረጠ የሚመስል ሁኔታ እየተስተዋለበት ሲሆን፣ በምርጫ ወቅት የቀበሌ ሠራተኞች (ካድሬዎች) ቤት ለቤት ባደረጉት ቅስቀሳ በተፅዕኖና መንግሥትን በመፍራት ካርድ የወሰደው ይበዛል የሚል ግምት ያላቸውም አሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ መዘገብኩት በሚለው ተመዝጋቢ ቁጥር ብዛት ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ የሌላቸው ጥቂቶች ይመስላሉ፡፡

ያለ ተወዳዳሪ ምርጫ
የምርጫው ወሬ በተጀመረ ሰሞን ምርጫ ምርጫ የሚሸቱ ዜናዎችና መግለጫዎች መሰማት ጀምረው ነበር፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመነጋገር በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማነጋገር በአዳማ በጠራው ስብሰባ የተነሳ ነበር፡፡

በወቅቱ ‹‹የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር የሚያሠራ አይደለም›› በሚል ከምርጫው ፕሮግራም በፊት በእዚህ ጉዳይ ላይ ከኢሕአዴግ ጋር ቁጭ ብለው ለመነጋገር ጥያቄ ያቀረቡ ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል በተለይ ‹‹33ቱ›› የሚባሉት የጋራ ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም ቅሬታቸውን አግባብ ባለው መንገድ ለምርጫ ቦርድና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አቅርበው ሰሚ አለማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

ዕጩዎች የምርጫ ምልክት የሚወስዱበት ቀነ ገደብ ቢጠናቀቅም፣ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ውድድር ውጪ ሆነዋል፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክንና መኢአድን ጨምሮ ዋና የሚባሉ የተቃዋሚ ስብስቦች የሚገኙበት ነው፡፡ መንግሥት 29 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክት ወስደው ለዕጩነት መዘጋጀታቸውን ቢገልጽም፣ ከዚህ የሚበልጥ ቁጥርና ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚዎች ወደ ሒደቱ ለመምጣት ምንም ጥረት አላደረጉም፡፡ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አንድ ዕጩ በማቅረብ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለመወዳደር የወሰነው በምርጫው ሒደት አምኖበት እንዳልሆነ በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ከምርጫው ሒደቱ ራሱን ለማግለል የወሰነው፣ እንደ ፓርቲ ለሦስተኛ ጊዜ ራሱን ከምርጫ ካገለለ በሚቀጥለው ምርጫ መሳተፍ ስለማይችል ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ የሕግ ተፅዕኖ ምክንያት በሒደቱ የሚሳተፈው ኢዴፓ፣ ከምርጫው ራሱን እንዳገለለ ነው የሚታሰበው፡፡

የተቀሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድም በሕዝብ አይታወቁም፣ አለበለዚያም ከኢሕአዴግ አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ስለሚጠብቁ በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነትም እስከዚህም ነው የሚሉ አሉ፡፡ በምርጫው ያላቸው ሚናም ለሕዝቡ አማራጭ ሆነው ይፎካከራሉ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግን በሒደቱ በማጀብ ከዓለም አቀፍ ነቀፌታ መታደግ ብቻ ነው ተብለው የሚታመኑ ናቸው፡፡ በዚህም ሒሳብ አንድም የሚታወቅ ተቃዋሚ የማይወዳደርበት የአካባቢ ምርጫ፣ ያለተቃዋሚ የሚደረግ ምርጫ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነው፡፡

የ97 ጦስ
አቶ አበራ ዘገዬ ዕድሜያቸው 56 ሲሆን የእንጨት ሥራ ባለሙያ ናቸው፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ወትሮም ቢሆን የተጋነነ ሁኔታ አይታይበትም፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ምርጫውም ቢሆን ከ97 ዓ.ም. በኋላ ያን ያህል አጥጋቢ አይመስለኝም፤›› በማለት ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሰሞኑን ተጀመረ የተባለውን የምረጡኝ ቅስቀሳ ግን ልብ ብዬ ሰምቼውም አላውቅም፡፡

 ይህ ደግሞ የኔ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ሰው ስሜት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው ስለጉዳዩ ሲያወራ አይታይም፡፡ በአጠቃላይ የምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቅዝቀዝ ያለ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኔ በአግባቡ በተመቸኝ ሰዓት ሄጄ ነው የምርጫ ካርዴን የወሰድኩት፡፡ የማውቃቸው ሌሎች ብዙ ሰዎች ግን ኑ ውሰዱ ተብለው እንደወሰዱ አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሞቅ ሞቅ ያለ ቅድመ ምርጫና የምርጫ ወቅት የታየበት ሦስተኛው አገራዊ የ97 ምርጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሆኖም ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ኅብረት ፈጥረው ገዥውን ፓርቲ ተፈታትነው የነበሩ ተቃዋሚዎች ተበታትነዋል፡፡ በምርጫው ማግስት በፀደቁት አንዳንድ አፋኝ ሕጎች የተወሰዱ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ተከትሎ በ2000 ዓ.ም. የተደረገው የአካባቢ ምርጫ ጀምሮ ነበር ኢሕአዴግ የፖለቲካ ሁኔታውንና የምርጫውን ሒደት ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የቻለው፡፡

በወቅቱ እስከ አምስት ሚሊዮን አባላት የመለመለው ኢሕአዴግ፣ ለአካባቢ ምርጫ በአጠቃላይ እስከ ሦስት ሚሊዮን መቀመጫዎች እንዲቀርቡ ያደረገ ሲሆን፣ በወቅቱ ጠንካራ ከነበሩ ተቃዋሚዎች ኅብረትና ኦፌዲን ራሳቸውን ከሒደቱ ሲያገሉ፣ ኢዴፓ ለተሳትፎ ሲል ተወዳድሯል፡፡ በቅንነት የተደረገ ምርጫም አልነበረም በማለት የሚተቹ ብዙ ናቸው፡፡

ቀጥሎም በተካሄደው የ2002 ዋና ምርጫ መድረክ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ሆኖ ብቅ ያለ ቢሆንም፣ ከአንድ የፓርላማ መቀመጫ ውጪ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከምርጫው በፊት ጀምሮ የፖለቲካ ምኅዳሩ የማያፈናፍን ሆኗል በሚል የሚቀርብበትን ትችት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ኢሕአዴግ፣ ሒደቱ በነበረበት ቀጥሎ ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ውጪ ሆነው፣ ሕዝቡ በተፅዕኖ የምርጫ ካርድ የሚወስድበትና የደበዘዘ የምርጫ ሒደት የሚታይበት የአሁኑ ወቅት ላይ መደረሱን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቺዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

የብዙ አስተያየት ሰጪዎች ሥጋት የፖለቲካ ምኅዳሩ አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ሕዝቡም ሆነ ዋነኛ ተቃዋሚዎች በምርጫ መንግሥት መለወጥ አይቻልም የሚል ሙሉ ሙሉ ተስፋ መቁረጥ እንዳያስከትል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሰላማዊ መንገድ ኢሕአዴግን መቃወምና መታገል አይቻልም የሚል ስሜት ሊፈጠር እንደሚችል ይታመናል፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫን ሥልጣኑን ለማራዘም የሚጠቀምበት ስልት ነው በሚል ነፍጥ የሚያነሱ አማፂዎች የበለጠ ድጋፍ እያገኙ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ሥጋትም አለ፡፡

የትግራይ ህዝብ ስማ!!


ሰሞኑን በውዴታም ይሁን በግዴታ በመቀሌ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ሲጨፍሩ፣ ሲዘሉ፣ ከበሮ እየመቱ የባህላቸውን ዘፈንና ውዝዋዜ ሲያወርዱ አይተናል። ምክንያቱ በግልጽ ባይነገርም ሲደበቅ የነበረው የህወሃት ሃብትና ንብረት ውጤት የሆኑ፣ በልዩ የመንግስት ድጋፍ የተከናወኑ ግዙፍ ተቋሞች በጎዳና ለህዝብ ሲቀርቡም ተስተውሏል። ልማቱ መልካም ነው። ደስ ይለናል። ምንም ተቃውሞ የለንም። ግን መልዕክት አለን።
ለማን?
ምሬትን፣ ጭቆናና መንገፍገፍ ሲበዛ በፍቃደኛነት በቦንብ ላይ እንደሚያስሮጥ ለሚያውቀው የትግራይ ህዝብ!! የትግራይ ህዝብ ስማ!!
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት የትግራይ ክልል በትምህርት፣ በኤሌክትሪክ፣ በመንገድ፣ በእርሻ፣ በደን፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ ወዘተ ከሌሎች ክልሎች ሁሉ ርቃ መሄዷን ይፋ አድርጓል። በዚህም ደስ ይለናል። አይከፋንም። ከዚህ በላይ እንዲሆን እንመኛለን። ነገር ግን አንድ መልዕክት አለን።
ለማን?
አሁንም ለትግራይ ህዝብ!!
ሓውዜን የትግራይ ወጣቶች ለትግል ግልብጥ ብለው እንዲወጡ አደረገ። ሓውዜን የደረሰው የቦንብ ድብደባ ማንና እንዴት እንደተቀነባበር ብዙ የሚባልለት ቢሆንም የምሬት ጫፍ ሆኖ ህዝብን አሸፍቷል። ዛሬ መጨቆን ያንገፈግፋል ብለው ለትግል በተነሱና በተሰው ታጋዮች ደምና አጥንት ላይ የቆሙ ሌሎች ሓውዜኖች እንዲፈጠሩ አድርገዋል። እያደረጉም ነው።
ይህ በማን ስም እየሆነ ነው? በህወሃት አማካይነት በትግራይ ህዝብ ስም!!
ኦሮሚያ ልጆቿን በእስርና በጥይት እያጣች ነው። በጨለማ ቤት እየተሰቃዩ ያሉ የኦሮሞ ልጆች ግፍ ሰፍሮ ሞልቷል። አማራው አገር አልባ ሆኖ በየጎዳናው እየወደቀ ነው። እየተለዩ ከየክልሉ እየተባረሩ ነው። የመኖር ዋስትናቸውን ተከልክለው በሞትና በጣር መካከል ያሉ ህጻናትና ነፍሰጡሮች ለቅሶ ሰማይ ደርሷል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ እስር ቤት የሚማቅቁና የሚሰቃዩ ሰውነታቸውም የሚተለተል አሉ። የተገደሉ አሉ። ይህንን የሚያደርገው ደህንነቱ የተቆጣጠረውና መሳሪያ ያነገተው ኃይል ነው። ይህ ኃይል ደግሞ ህወሃት ነው። ህወሃት ይህንን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው በትግራይ ህዝብ ስም ነው። እያመረተ ያለው ደግሞ ብዙ ሓውዜኖችን ነው። በደልና የበቀል ስሜት ላንድ ጎሳ ወይም ሕዝብ ብቻ የተሰጠ አይደለምና ሌሎችም ሊነሱ ይችላሉ። መቼና እንዴት? አይታወቅም። በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ … ብዙ ችግርና ምሬት አለ።
በጋምቤላ ግፍ ነዶውን እየወዘወዘ ነው። በጋምቤላ በዘመናት ወደፊት የማናገኛው የደን ሃብት እየወደመ ነው። በጋምቤላ ሰላማዊ ህዝቦች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሬታቸውን እየተነጠቁ ለውጪ “ባለሃብቶች” እንዲሁም ለትግራይ ተወላጆች እየተከፋፈለ ነው። በባሌ፣ በቦንጋ፣ በወለጋ፣ ድፍን ኦሮሚያና የደቡብ ክልል ደን እየተጨፈጨፈ ትግራይ በደን እየተሸፈነች ነው ብሎ መጨፈር ለትግራይ ህዝብ ኩራት አይሆነውም። ኢትዮጵያዊ ነው የሚባለው የትግራይ ህዝብ እሱ የሚጠላውና ልጆቹን የገበረለት ግፍ በሌሎች ወገኖቹ ላይ ሲፈጸም ዝም ማለቱ ለምንና ከምን የመነጨ እንደሆነ ለማወቅ የሚፈልጉ አሉና ጥያቄውን እናቀርባለን።
ስለመፈናቀል ስናወራ “የትግራይ ተወላጆች ተፈናቀሉ” ሲባልና “ተፈናቀልን” ብለው ቅሬታና አቤቱታ ሲያቀርቡ አንሰማም። ይልቁኑም የአማራን ለም መሬት ለትግራይ በመከለል በደል የሚፈጽመው ህወሃት የሚባለው በትግራይ ህዝብ ስም የተደራጀና በነጻ አውጪ ስም እስካሁን አገር የሚመራ ቡድን ነው። ይህ ሁሉ ሲደረግ የትግራይ ህዝብ ያውቃል። ቢያንስ ቢያንስ የሰው መሬት ወርረው የተቀመጡት አይክዱትም። ግን ይህ እስከመቼ ይቀጥላል? ፍርሃት አለን። ለምን? ይህ ሁሉ ሌላኛው የሓውዜን ክፍል ነዋ!!
ስለ ግብር ሲነሳ የትግራይ ተወላጆች በግብር ዕዳ፣ በባንክ እዳና እንደ ልብ ነጻ ሆኖ በመንቀሳቀስ ችግር ቅሬታ ሲያሰሙ አይደመጥም። በመላው አገሪቱ በኢንቨስትመንት ተሰማርተው በሰላም እየሰሩ ነው። ሌሎች ግን በብሔር ተለይተው መከራ ይደረስባቸዋል። ህወሃት በማንነታቸውና ባመለካከታቸው እየነጠለ ከጨዋታና ከኑሮ መስመር ያወጣቸዋል። የጭቃ ቤት፣ አርሰው የሚበሉበት ከብት፣ ዶሮና በግ ሃብት ተብሎ ይወረስባቸዋል። ይህ እውነት ለትግራይ ምሁራን የተሰወረ አይደለም። ይህም ሌላው ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም በሌሎች ዜጎች ላይ የሚፈጥረው የምሬት ሓውዜን ነው!!
ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ሲነሳ የመጀመሪያው መስመር ላይ ሆነው አገሪቱን የሚያልቡት የቀድሞ ታጋዮችና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎች ናቸው። ጤፍ ወደ ኤርትራ በማጋዝ፣ ባህር ዛፍና ቡና በማሻገር፣ የዱር እንስሳትን ቆዳና ቀንድ በመነገድ የተሰማሩት ይታወቃሉ። ብዙ እጅግ ብዙ ማለት ይቻላል። የምናነሳቸው ማሳያዎች ሁሉ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ፣ … ሓውዜኖች ናቸውና እዚህ ለጊዜው ላይ  እናቁም!!
ሻዕቢያ ድንገት ወረራ አካሂዶ ድፍን ትግራይን ሲቀጠቅጥ፣ ህጻናትን በቦንብ ሲቆላ፣ አገሬ ብሎ የተነሳን ህዝብ በማያውቀው ወንጀል እየሰፈሩ ማሰቃየት ይቆም ዘንድ የትግራይ ህዝብ በቀጥታ ድምጹንና ተቃውሞውን በአግባቡ ማሳየት የሚገባው ወቅት ላይ እንደሚገኝ ይሰማናል፤ ደግሞም እናምናለን። ዛሬ “ውርሱን እንጠብቃለን” በማለት የሚጮህላቸው አቶ መለስ በወቅቱ ክህደት ሲፈጽሙ የደረሰው ዛሬ እየተነጠሉ የሚመቱትና መድረሻ ያጡ ወገኖች ናቸው። ዛሬም ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ናቸው። በሰባና ሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ ልብ ውስጥ የተፈጠሩት ሓውዜኖች ወደ ቁጣ ሲለወጡ አምስት አምስት ሆኖ መደራጀት፣ በስውር መታጠቅና በየሰፈሩ ያሉትን አስተባባሪዎች ስም ለቅሞ በመያዝ “ሳልቀደም ልቅደም” ብሎ መራወጥ አያዋጣም፤ ጊዜው ስለሚያልፍበት የትም አያደርስም። ሓውዜናዊ ህይወት የሚኖር ሕዝብ ከደረሰበት በላይ የሚያጣው ስለማይኖር እንኳን ስለማጣት ስለመኖርም አያስብም፡፡ በዚህ ከቀጠለ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በየቦታው ራሱ ህወሃት የፈጠራቸው ሓውዜኖች መናደፍ መጀመራቸው አይቀርም።
“ህወሓትን እናስቀድም … ጠላቶቻችንን እናጥፋ” በሚል የማያቋርጥ ጥላቻ መቀጠል ተጨማሪ ሓውዜኖችን ከመፍጠር በስተቀር “ጠላትን” ማጥፋት የማይቻል እንደሆነ ከዚህ በፊት በሕዝብ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ተሞክሮ ማስረጃ ነው፡፡ በበረሃ “ጠላትን እናጥፋ”፤ ሥልጣን ይዞ “ጠላትን እናጥፋ”፤ አገር እየመሩ “ጠላትን እናጥፋ”፤ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ “ጠላትን እናጥፋ” … 40ዓመት ሙሉ በ“ጠላትን እናጥፋ” መርህ የሚጓዘው ህወሃት “ጉድጓድ የሚምስ ራሱ ይወድቅበታል” የተባለው የተቀደሰ አባባል ሲፈጸም እንዳየነው ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማጥፋት የሚመኘው ህወሃት የራሱ መጥፊያ የሆኑ በርካታ ሓውዜኖችን ፈጥሯል፡፡
“የ100 ዓመት የቤት ስራ ሰጥተናቸዋል” በሚል በየድረገጹ የሚለጠፉ ተራ ድንፋታና ትዕቢት የሚፈጠሩትን ሓውዜኖች ከማብዛት ውጪ ትርፍ የላቸውምና ወደ ደጉ መንገድ መመለስና ሰብዓዊነትን በማስቀደም፤ ተደጋግፎ መኖርን ማጎልበት ይሻላል ለማለት እንወዳለን። ተሳስበውና ተረዳድተው የሚገነቡት የትም ሆነ የት የአገር ነውና ሁሉም ይኮራበታል፤ ይጠብቀዋል። ተጠቃሚ ይሆንበታል። የሚያምርብንም ይህ ነው። ህወሃት አልሰማም ብሏል። የትግራይ ህዝብ ግን ስማ!! ይህ ሁሉ የሚደረገው በስምህ ነው!!