Mar 26, 2013

የእስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ግለሰብ ብአዴን ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ሰው መሆናቸው ታወቀ

የእስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ግለሰብ ብአዴን ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ሰው መሆናቸው ታወቀ
መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ ከተካሄደው ምርጫ በፊት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ሀጂ መሁመድ ሲራጅ ሙሀመድ ኑር አባታቸው ዋግ ውስጥ ነባር የብአዴን ታጋይ የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ተፈራ ዋልዋ እና የአቶ አዲሱ ለገሰ የቅርብ ሰው እንደነበሩ ከብአዴን ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግለሰቡ በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ እንዲኮላሽ ከመንግስት ከፍተኛ ተልእኮ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና አሁንም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ለመንግስት ምክር እየሰጡ የሚገኙ ናቸው።
የግለሰቡ ታሪክ እንደሚያስረዳው ታጋይ አባታቸው ሲራህ መሀመድ ኑር እንደሞቱ ወጣቱ ሲራጅ በአቶ አዲሱ አማካኝት የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበርን እንዲያደራጁ ተመርጠው ማህበሩ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በዚህ አስተዋጽኦቸውም፣ ምንም አይነት በቂ የእስልምና እምነት ትምህርት ሳይኖራቸው የአማራ ክልል እስልምና ጉባኤ ሃላፊ ተብለው በመንግስት ከተሾሙ በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ በክልሉ ውስጥ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
በ1997 ዓም ግለሰቡ ወደ ፌደራል ተዛውረው መጠነኛ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት እንዲቀስሙ ከተደረጉ በሁዋላ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ በመሆን ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሀጂ ሙሀመድ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የክልሉን የእስልምና ምክር ቤት በከተማዋ መሀል አደባባይ ላይ በአለ አራት ፎቅ ህንጻ እያሰሩ ሳለ፣ ከህንጻው ስራ ጋር በተያያዘ ገንዘብ ማጉደላቸው በመረጋገጡ ፣ የህንጻው ስራ እስካሁን ካለመጠናቀቁም በላይ ግለሰቡ እንዳይጠየቁ ተደርጓል።
በሰቆጣ ለእናታቸው እጅግ ዘመናዊ ህንጻ የገነቡት ሀጂ ሙሀመድ፣ ሶስት የንግድ መኪኖችን ገዝተው በንግድ ስራ ላይ ከመሰማራታቸው በላይ፣ በባህርዳር፣ በአዲስ አበባ እና በሰቆጣ የንግድ ቤቶችንና የመኖሪያ ቤቶችን በራሳቸውና በወንድሞቻቸው ስም በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ወደ ሀብታሞች ጎራ ለመቀላቀል ችለዋል።
በቅርቡ በተደረገው የመጅሊስ ምርጫ ስልጣናቸውን ያስረከቡት የ40 አመቱ ሀጂ ሙሀመድ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ ድርጅት ከፍተው መንግስትን እያማከሩ ነው።
በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም መሪዎች እና ድምጻችን ይሰማ በማለት ዘወትር አርብ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ምክር ቤቱ ነጻ አይደለም በማለት ጥያቄ ማቅረባቸው ትክክልና በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን የብአዴን ምንጮች የዋና ጸሀፊውን ማንነት በማስረጃ በማስደፍ እንደ ማሳያ አቅርበዋል። በቅርቡ የተተኩት የመጅሊስ አባላትም እንዲሁ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊና አባላት መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አያይዞ ገልጾአል።
አቶ ተፈራ ዋልዋ ብዙውን ጊዜ አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ አልፎ አልፎ በህይወት ያሉት የሀጅ መሀመድ ሲራጅን እናት የታጋይ ሲራጅ ሙሀመድ ኑርን ባለቤት እየሄዱ እንደሚጠየቁቸው ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሀጂ አል ሙሀመድ ሲራጅን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment