Sep 11, 2013

የሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተነገረ! (ድምፃችን ይሰማ)

September 8, 2013

 
የእስሩ መንስኤ ‹‹አባቴን የገደለው መንግስት ነው!›› በማለቱ ነው ተብሏል!
ከሁለት ወራት በፊት በሰው እጅ ሕይወታቸው የጠፋው ሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በመንግስት ደህንነቶች ታፍኖ ተውስዶ መታሰሩ ተሰማ፡፡ በደሴ አረብ ገንዳ አካባቢ ነዋሪ የነበሩትና መንግስት ለፖለቲካ ጥቅም ሲል ገድሏቸዋል ተብሎ በስፋት የሚታመነው ሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በመንግስት ደህንነቶች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ አሁን ያለበት ቦታ በውል መታወቅ አልቻለም፡፡ እንደ አከባቢው ምንጮች ከሆነ የሼኽ ኑሩ ልጅ የታሰረው ከአባቱ ግድያ ጋር በተያያዘ ‹‹አባቴን ያስገደለው መንግስት ነው!›› በሚል በዙሪያው ላሉ ሰዎች በመናገሩ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ወጣት ተመሳሳይ እስር ሲያስተናግድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ተመሳሳይ ንግግር በመናገሩ በደህንነቶች ለቀናት ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ማስፈራሪያና ምክር ተለግሶት ተፈቷል፡፡ ሆኖም ከተፈታ በኋላም የመንግስት ደህንነቶች ያስጠነቀቁትን ‹‹ከአሁን በኋላ አባቴን መንግስት አስገድሎታል እንዳትል!›› የሚል ምክር ጥሶ በመገኘቱ ለድጋሚ እስር ተጋልጧል፡፡
መንግስት ከሼኽ ኑሩ ግድ ጋር በተያያዘ ለሳምንታት የዘለቀ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲያካሄድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዘመቻ ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ተቋማት መግለጫ በማውጣት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም በበርካታ የገጠር ከተሞች በተሌም በአማራ ክልልና ደቡብ ወሎ ‹‹ሕዝቡ የሼኽ ኑሩን ግድያ እንዲቃወም›› በሚል የግዳጅ ሰልፍ እንዲወጣ ከመደረጉም በላይ ‹‹ግድያውን የፈጸሙት ሙስሊሞች ናቸው›› በሚል ‹‹መንግስት እርምጃ ይውሰድ!›› የሚል መልእክቶች በተከታታይ በመንግስት ሚዲያዎች ሲያሰራጭ ነበር፡፡ ሆኖም ከሼኽ ኑሩ ግድያ ጋር በተያያዘ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ምንም ንክኪ እንደሌለውና ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚያደርገው ተቃውሞ ፈጽሞ ይህን መሰል ጸየፍ ድርጊቶችን የሚስተናግድበት መርህ እንደሌለው በማስረገጥ፤ በዋነኝነትም የእንቅስቃሴው መርህ የሆነው ‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም›› መፈክር ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብም በሃይል እርምጃዎች የማያምንና የሚሰነዘርበትን ዱላ በጸጋ ከመቀበል ውጪም አጸፋ የሰጠበት አጋጣሚ እንደሌለ በአስረጂነት ቀርቧል፡፡
አሁን የት እንደታሰር በውል የማይታወቀውና ከቤተሰብ ጋር እንዳይገኛኝ የታቀበው የሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ የገለጸው ሀሳብ አብዛኛው ህብረተሰብ የሚያምንበትና በተለይም በደሴ ከተማ ሕዝብ ዘንድ ግድያውን መንግስት እንደፈጸመው በስፋት የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተለያዩ ወቅቶች ከሼኅ ኑሩ ግድያ ጋር በተገናኘ የመንግስት ረጅም እጆች መኖራቸው የሚያመላክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ሼኅ ኑሩ ከመንግስት ሀላፊዎች ጋር በቅርበት ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም በሞታቸው የመጨረሻ ወቅቶች ግን ከአካባቢው አስተዳደር ሀላፊዎችና የጸጥታ ሹሞች ጋር በአካሄድና መርህ ላይ ባለመስማማታቸው ስብሰባ ረግጦ እስከውጣትና ዳግም አብሮ የመስራት ፍላጎት እንደሌላቸውም ሲገልጹ ነበር፡፡ መንግስት ሞታቸውን ተከትሎም የአስከሬን ምርመራ እንዳይደረግና የቀብር ስነ ስርአቱ በአፋጣኝ እንዲፈጸም በማስደረግ የግድያው ሁኔታ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ የሼህ ኑሩ ግድያ ‹‹በመንግስት የተፈጸመ ድራማ ነው›› ሲል ሕብረተሰቡ ደጋግሞ መግለጹ ይወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment