Jan 30, 2013

የሙስሊም መሪዎች የችሎት ውሎ አስቂኝ ነው ተባለ


የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት በዝግ ችሎት በሚካሄደው የሙስሊም መሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ 190 ምስክሮች እንደሚቀርቡ አቃቢ ህግ ቢያስታውቅም እስካሁን የቀረቡት  ምስክሮች  11 ናቸው። ምስክሮችን የመስማት ሂደቱ በ10 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም፣ በአሁኑ አካሄድ  አቃቢ ህግ የምስክሮችን ቁጥር ካልቀነሰ በስተቀር በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥም ላይጠናቀቅ ይችላል።
የውስጥ ምንጮች እንደገለጡት አቃቢ ህግ ምስክሮችን  ሲያቀርብ የአባታቸውን ስም ብቻ በመጠቀም ነው። ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጋ ምስክሮቹ የመኖሪያ አድራሻቸው ፣ ስራቸውና ማንነታቸው እንዲገለጥ ለዳኞቹ ቢያመለክቱም፣ ዳኞቹ “የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ምስክሮቹ አድራሻቸውንም ሆነ ስራቸውን እንዲገልጡ አይገደዱም” የሚል ምክንያት በመስጠት ጥያቄውን አልተቀበሉትም።
አቶ ተማም ” በህገመንግስቱ አንቀጽ 20 መሰረት አንድ ጉዳይ በዝግ ችሎት ሊታይ የሚገባው አገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆን ብቻ ነው በማለት ” ቢከራከሩም  ዳኞቹ ” የምስክሮች ድህንነትም የአገር ደህንነት ነው” በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸውን ምንጫችን ገልጸዋል።
ጠበቃ ተማም ” በ1997 ዓም በቅንጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ሂደት ላይ  እንደተደረገው የተከሳሾች ቤተሰቦች እና ዘመዶች  ባይቀርቡ እንኳን ቢያንስ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የውጭ ዲፕሎማቶች እንዲገኙ ችሎቱ ፈቃድ ይስጥ በማለት ቢጠይቁም” ዳኞቹ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ክርክሩ ያለታዛቢ እንዲቀጥል ሆኗል።
ምስክሮቹ ተከሳሾች በአደባባይ የተናገሩትን ከመድገም ውጭ እስካሁን አንድም አዲስ ነገር አለመናገራቸው ታውቋል። ምስክሮቹ የተመሰከረባቸውን ተከሳሾች ጠቁሙ ሲባሉ ሌሎችን ሰዎች እንደሚጠቁሙ፣ እስረኞችም በምስክሮች ድርጊትና በፍርድ ቤቱ ሂደቱ ድራማ እየተዝናኑ መሆኑ ታውቋል።
አጠቃላይ የፍርድ ሂደቱ የተበላሸ ኧንደሆነ የተረዳው መንግስት፧ ከውርደት ለመዳን በሚል  የፍርድ ሂደቱን በዝግ ችሎት እንዲካሄድ ማድረጉን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ህግ ባለሙያ ተናግረዋል።

    No comments:

    Post a Comment