ከአንድ የገጠር ከተማ ወደ መቐለ ስገባ ጓደኞቼ አንድ ወሬ አካፈሉኝ። ወሬው "መንግስቱ ኃይለማርያም 'ከትግራይ ክልል ምንም ዓይነት ግብር ሰብስበን አናውቅም' አለ" የሚል ነው። መንግስቱ ይሄን ነገር ተናግሮት ሊሆን ይችላል ወይ ላይሆን ይችላል። ዋናው ጉዳይ ተናገረው ወይስ አልተናገረውም አይደለም። እውነት ነው ወይ ስህተት?! የሚል ጥያቄም ለግዜው እንተወው።
ግን ደርግ እንዴት ከትግራይ ግብር መሰብሰብ ይችላል? ግብር ለመሰብሰብ'ኮ ባከባቢው መስተዳድር መዘርጋት አለብህ። መስተዳድር ለመዘርጋት ግዛቱ በቁጥጥር ሥር ማዋል አለብህ። ደርግ ትግራይን አልተቆጣጠረም፤ አላስተዳደረም። ደርግ ትግራይን ካላስተዳደረ እንዴት ብሎ ግብር ይሰበስባል?
ደርግ መስከረም (አከባቢ) 1967 ዓም የመንግስትነት ስልጣን ተቆጣጠረ። ከወራት በኋላ (የካቲት 1967 ዓም) ህወሓቶች ጫካ ገቡ። ደርግ ሀገራዊ ስልጣኑ ለመጨበጥ አስተዳደር ለመዘርጋት ተንቀሳቀሰ። ትግራይን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩ በፊት ህወሓቶች ቀላል የማይባል የትግራይ የገጠር ቦታዎች ተቆጣጥረው በእጃቸው አስገቡ። ደርግና ህወሓቶች ትግራይን ለመቆጣጠር ጦርነት ከፈቱ። በሁለቱም ወገኖች የተደረገ ጦርነት ለ17 ዓመታት ዘለቀ። ትግራይ በዛን ግዜ የጦርነት አውድማ ሆነች።
በ17 ዓመቱ የጦርነት ዘመን ገጠር ትግራይ (ሓራ መሬት ትግራይ) በህወሓቶች ቁጥጥር ስር ነበር። የትግራይ ከተሞች ደግሞ በደርግ ስርዓት ቁጥጥር ወደቀ። ስለዚህ "የደርግ ዘመን" ተብሎ የሚታወቀው ግዜ ለትግራይ የጦርነት ዘመን ነበር። እኔ የደርግ ዘመን አልለውም። ምክንያቱም ደርግ ትግራይን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር አልቻለም። ስለዚህ ለኔ የደርግ ዘመን ሳይሆን "የጦርነት ዘመን" ነበር።
ስለዚህ ህወሓቶች ራሳችሁን ከጦርነት ዘመን አታወዳድሩ። የደርግ ዘመን የጦርነት ዘመን ነው።
No comments:
Post a Comment