በትግራይ አድዋ ወረዳ የሚገኙ ሦስት የአልመዳ ፋብሪካዎች (አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ አልመዳ ልብስ ስፌት ፋብሪካና (አልመዳ ) ሳባ እምነበረድ ፋብሪካ) የኬሚካል ቆሻሻ (Chemical Residue) የሚጠራቀምበት ከመሬት በታች የሚገኝ ጋን ፈንድቶ ወደ ላይ በመተኮሱ የአከባቢ ብክለት አስከትሏል። ይህንን የቆሻሻ ኬሚካል ማጠራቀምያና ማጣርያ ፍንዳታ አደገኛና መርዘኛ ሽቶ በመፍጠሩ በአከባቢው (እስከ አስር ኪሜ ራዲያስ ድረስ) የዉሃና የአየር ብክለት አስከትሎ በሰዎችና እንስሳት የመታመም ምልክቶች እየታዩ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ የፋብሪካዎቹ ሰራተኞች (ከ 500-600 የሚደርሱ) ችግሩ ተቋቁመው እንዲሰሩ ስለ ተገደዱ የጤና ችግር እንዳያስከትልባቸው በመስጋት ለትግራይ ክልል መንግስትና ለትእምት ሓላፊዎች አቤት ያሉ ሲሆን እስካሁን ግን መልስ አላገኙም። መንግስት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል።
ሁለት፡ ታሕታይ ማይጨው
በትግራይ ክልል፡ ማእከላዊ ዞን፣ ታሕታይ ማይጨው ወረዳ (ከሁለት ሳምንት በፊት ነው) የመንግስት ሰራተኞች ከህወሓት ሓላፊዎች ጋር አለመግባባት ፈጥሯል። በወረዳው ወደ 650 የሚሆኑ አስተማሪዎች፣ 420 የግብርና ሰራተኞች፣ ከ300-350 የጤና ሰራተኞችና ከ550 በላይ የወረዳው የመንግስት አስተዳደር ሰራተኞች የኢኮኖሚ ጥያቄ አስነስተዋል። እነኚህ ሰራተኞች የወር ደመወዛቸው አነስተኛ ሁኖ ሲያበቃ (ግብር ሲቆረጥበት የባሰ እንደሚያንስ ነው) ተጨማሪ ወጪ ስለበዛባቸው መኖር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
ደመወዛቸው አነስተኛ፤ ከዚህ የመንግስት (የማይቀረውን) ግብር ይቆረጣል፣ የህወሓት የአባልነት መዋጮ ይቆረጣል፣ የትግራይ ልማት ማህበር (TDA) ይቆረጣል፣ የአባይ ግድብ ይቆረጣል፣ (የቀይ መስቀል የሚቆረጥባቸውም አሉ) ወዘተ … ። በቃ መቁረጥ ነው። ተጣርቶ እጃቸው የሚገባ በጣም ትንሽ ብር ነው። በትንሽ ብር (ከንሮ ውድነቱ ጋር ተደምሮ) ህይወት ለነሱ መከራ ሁናለች።
ችግራቸው ለዞኑ አስተዳደር ለማስረዳት ሞክረዋል። ‘ወጪ በዝቶብናል’ አሉ። አስተዳዳሪውም ‘የመንግስት ትእዛዝ ነው’ አለ። እንሱም ‘ቢያንስ የህወሓት አባልነት መዋጮ ይቀነስልን’ አሉ። አስተዳዳሪውም ‘ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ የህወሓት አባል መሆን አለበት፤ አለበለዝያ ግን ከስራው ይባረራል’ ብሎ አስፈራራቸው። አሁን ተስፋ በመቁረጥ ላይ ናቸው።
ሦስት፥ ሽሬ
በሽሬ አከባቢ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር መኖሩ ለማወቅ ችያለሁ። ከሩቅ ቦታ የሚመጣው የጉድጓድ ውሃ (ንፁህ ያልሆነ ውሃ) በብዙ ብር ይገዛል። አብዛኞቹ የሽሬ ሆስፒታል ታካሚዎች በውሃ ወለድ በሽታዎች የሚሰቃዩ መሆናቸው መረጃ ደርሶኛል። በአከባቢው ከዓመታት በፊት በእስራኤላውን ባለሙያዎች የተጠና የውሃ ቁፋሮ ተደርጎ እንደነበርና በሙስና ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀርቶ እስካሁን ድረስ የዉሃ ችግሩ እንዳለ ነው።
አራት፡ የትግራይ መንግስት ፕላን
የትግራይ መንግስት በግብርና ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት ብዙ ዉሃ ለማቆር የሚያግዙ ቁፋሮዎች አከናውነዋል። ብዙ የዉሃ ጉድጓዶች ተቆፈሩ። ውሃ ተጠራቀመ። አርሶ አደሮች በዓመት ሁለቴ ማፍራት እንዲችሉ ምርጥ ዘርና መዳበርያ (fertilizer) በብድር እንዲወስዱ ተገደዱ (ካልወሰዳቹ መሬታቹ ለሌላ ሰው አሳልፈን እንሰጠዋለን በሚል)። አርሶ አደሮቹ ተበድረው ወሰዱ። ተጠቀሙበት። እህሉ ሳይደርስ የቁፋሮውን ውሃ ደረቀ። ፍሬ ሳይሰጥ ቀረ። ብድሩ ግን አለ። ከሰኔ ወር በፊት ብድሩ መመለስ አለባቸው። ከየት አምጥተው ይከፍሉታል? አርሶ አደሮቹ ተጨናንቋል።
አንድ ነገር ሲተገበር መጀመርያ በጥናት የተደገፈ መሆን አለበት።
No comments:
Post a Comment