Sep 11, 2013

'' ትግሉን አለመቀላቀላችሁ ጊዜዉን ያረዝመዉ ይሆናል እንጅ ለዉጥ ከማምጣት አያግደንም ''እርዮት አለሙ

አንዲትን ወጣት ሴት መምህር ጋዜጠኛ ከእስኪሪቢቴ እና እንጀራ ውጭ በእጇ ይዛ የማታውቅ በቤተሰቦቿ በጓደኞቿ በስራ ባልደረባዎቿ የተከበረችና የተወደደች በህይወት ዘመኗ በምንም አይነት መጥፎ ተግባር ላይ ተሳትፋ የማታውቅ ምንም አይነት የወንጀልም ሆነ የክስ ሪከርድ የሌለባት ብዙ ጊዜዋን ከተማሪዎች ጋር እና ከምታስጠናቸው ህጻንት ጋር የምታሳልፍ፤ የቀረውን ጊዜዋን ደግሞ ስትታዘብ የዋለቻቸውን ስርዓቱ የፈጠራቸውን ችግሮች፤ ስለ ህግ የበላይነት መጓደል፤ ስለዜጎች እኩልነት፤ ስለ አደርባይነት፤ ስለ እምነት ነፃነት… በድፍረትና በሀቀኝነት ስትከትብ ታሳልፋለች፡፡ መምህርና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እና በቲያትሪካል አርት ሁለት ድግሪ ያላት ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በቃሊቲ እስር ቤት አስከፊ የእስር ጊዜ እያሳለፈች ነው፡፡
ይሄ መቼም የሚተቻቸውን በሰበብ በአስባቡ ማሰር የአምባገነኖች መለያ በመሆኑ ከልጅቱ ጥንካሬ አንጻር አይደንቅም፡፡ የሚገርመው ከ5 ወር በፊት ርዕዮት በጠና ታማ በነበረበት ሰዓት ማረሚያ ቤቱ ወደህክምና ቦታ ለመውሰድም ሆነ መድሀኒት ለማቅረብ ፍቃደኛ አለመሆኑ ብዙዎቻችንን አስደንግጦን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከእናቷ ውጭ ማንም እንዳያያት ከልክለዋል፤ ለዚች ወጣት ሴት ይሄ ሁሉ ጭካኔ ለምን?
ዛሬ በርዕዬት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እያየን አንዳንዶቹ አልሰማንም አላየንም ብለን ቁጭ ፤ አንዳንዶቻችን እግሬ አውጪኝ ብለን ሸሽት፤ አንዳንዶች እስከመጨረሻው አብረው ቆመዋል፡፡ ዛሬ ግን የሁላችንንም ድምጽ ከያለንበት መስማት ትፈልጋለች፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ታስራ እንኳ ሰብአዊ መብቷ ሊከበር ይገባል፡፡
ርዕዮት ከማንም የተለየ የዚህችን ሀገር ሀላፊነት የመሸከም እዳ የለባትም፤ የእኛን ሁሉ እዳ ነው የተሸከመችው!

No comments:

Post a Comment