Mar 28, 2013

ጥልያን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው

በላይ ዘለቀ ጀግና ብቻ አልነበረም፡፡ ባንዳነትን አድረባይነትን ሎሌነትን አጥብቆ ይጠላም እንደነበር ከዚህ ታሪኩ መረዳት እንችላለን፡፡ “….በላይ ዘለቀ ተኩሶ አይስትም ::ፍጥነቱ ደሞ ሲደግንና ሲተኩስ እኩል ነው ::ውጊያ ሊጀምር ሲል "እኔ ሳልተኩስ እንዳትተኩሱ " ብሎ ያዛል ::አንዳንድ ጊዜ በውጊያ ሰአት "እርስዎ እዚህ ይቆዩን " ሲሉት "ምን ?" ይላል ቁጣ እየጀመረው ::"እርስዎ ከወደቁ መሪ የለንም " ሲሉት "ወይድ ! እኔ አሮጌ ነፍጠኛ ነኝ ::"ይልና ግንባር ይጋፈጣል :: በላይ ዘለቀ እራሱ ሲዋጋ "ገምባው " ይተበባለው ጥሩንባው ይነፋል ::"ገምባው "ባንዳን ያስበረግጋል ::ጥልያንን ያብረከርካል ::
በላይ ዘለቀ የዘመኑን አስተሳሰብ በማወቁ ህዝቡን ለማስተባበር "ትልቅ ሰው " ማስፈለጉን በመገንዘቡ እሱ እራሱ ግን ተራ ሰው በመሆኑ የንጉስ ተክለሀይማኖት ሀረግ ለሆኑት ለልጅ ሀይሉ በለው ደብዳቤ ጻፈላቸው :: የደብዳቤው ሀሳብ ባጭሩ "ህዝቡን ለማስተባበር እርስዎ የበላይ ሆነው እነን የጎበዝ አለቃ ይሹሙኝና ጠላትን እንቋቋመው ::እኔም እዋጋለሁ ::እርስዎ ወደጦር ግንባር መድረስ አይኖርብዎትም ::" የሚል ነበር ::ደጋግሞ ደብዳቤ ጻፈላቸው ::ገጸበረከትም ላከላቸው ::...ጠመንጃ ሽጉጥ ዝናር ከነጥይቱ ሶስት መቶ ብርና ካባ :: ልጅ ሀይሉ በለው ለደብዳቤዎቹ አንድም መልስ ሳይሰቱ አንድ ቀን አንድ የትእዛዝ ደብዳቤ ላኩበት ::"ደብረወርቅ ገበያችንን ያለአግባብ ቀረጡብን ብለዋልና ከንግዲህ ቆቅ የሰገረ ወፍ የበረረ እንዳይደርስባቸው ::የተወሰደባቸውም ቀረጥ እንዲመለስላቸው ::"
በላይ ዘለቀ ተናደደ ::አብረውት የነበሩትን "ጎበዝ እግዚአብሄር የወለደው ሰው አለ ?" ሲል ጠየቀ :: "እግዚአብሄር ይፈጥራል እንጂ አይወልድም " አሉት :: "ንጉስስ ?" "ንጉስም እግዚአብሄር ይቀባዋል እንጂ አይወልድም ::ይፈጥረዋል እንደሌላሰው " "እኔንም ፈጥሮኛል ::ሊቀባኝ አይችልም ?" "የሱ ሀይል ካደረብዎ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ ::" "እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ለማንም አልታጠቅም ::" ተመስገን ፈንታ የበላይ ዘለቀ የቅርብ ጉዋደኛው ነበር ::አንድ ቀን ከጠላት በፊት ተመስገን ፈንታ በላይ ዘለቀን "ሸዋ ሄደን ለትልቅ ሰው እንደር ::እንሾማለን ;እንሸለማለን "አለው :: "እኔ ሰው ሆኜ ለሰው አላድርም "አለ በላይ ዘለቀ :: "ባንተ ተኩስ ;ባንተ ወኔ ;ባንዳፍታ ትሾማለኽ :: "ጀግንነት እደጃችን ድረስ ይመጣ እንደሆነ ማን ያውቃል ?" አለው በላይ ዘለቀ ::አመታት አለፉ ::
ሞረድ እጀ ጠባብ ካስመራ እሚመጣ አፈ ሾሌ ሱሪና ተመሳሳይ ኮኮት ጥንግ ድርብ ጥበብ ኩታ በቅሎ እንደተጫነች ጠመንጃ ከነሙሉ ዝናር ጥይት ...በላይ ዘለቀ ይህንን ሁሉ አዘጋጀና ተመስገን ፈንታን ጠርቶ ; "ያ የጌታ አዳር ሄደን እንሸለማለን ያልከው ይኸውና "ብሎ ሸለመው ::በአርበኝነት ዘመን ጉዋደኛሞቹ አልተለያዩም :: በላይ ዘለቀ መጀመርያ "ራስ " ብሎ የሾመው ተመስገን ፈንታን ነበር :: "እኔንስ ራስ አልከኝ ::አንተ ማን ልትባል ነው ?" አለው ተመስገን ፈንታ :: "እኔንማ እናቴ አንደዜ በላይ ብላኛለች " አለ በላይ ዘለቀ ::” ……….
የበላይ መጨረሻም ይህ ሆነ፡፡ ንጉስ ሹም ሽር አደረጉ ::በላይ ዘለቀ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በሁዋላም ከአገሬው ጋር ሆኖ ጠላትን ተዋግቶ ነጻ ያወጣው ጠቅላይ ግዛት ለራስ ሀይሉ ተሰጠ :: በላይ ዘለቀ ወዳዲሳባ ተጠርቶ ደጃዝማች ተብሎ የቢቸና አውራጃ ገዥ ሆኖ ተሾመ :: የቢቸና አውራዣ ገዥ ሆኖም ሊሰራ አልቻለም ::ከደብረ ማርቆስ ትእዛዝ እየመጣ ወረዳዎቹ ሁሉ ቀድሞ ባንዳ የነበሩ ሰዎች ተሾሙባቸው ::ብስጭት በዛበት በላይ ዘለቀ :: "ሊወጋን ነው ....እምቢ አለ ..."እያሉ ማስወራት ጀመሩ :: በቂ ካስወሩ በሁዋላ ከራያና አዘቦ ጦር አስዘመቱበት :: (ጎጃመማ በላይ ዘለቀን ወይ ይወደዋል ወይ ይፈራዋል :: ) በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ከጥቂት ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ሆነው ወደ ሳማ አምባ ሸሹ ::በላይ ዘለቀ ሸፈተ ተባለ :: ሳማ አምባ ያለ ሁለት በር የላትም ሁለቱንም በር ይዘው ሀያ አምስት ቀን ሌትና ቀን ተዋጉ :: "ምረነዋል ልቀቁት ይምጣ "የሚል መልእክት ከንጉሱ መጣ :: ከሳማ አምባ ከወረዱ በሁዋላ ተከበቡና መሳሪያቸውን ተነጥቀው እንደ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ :: በላይ ዘለቀ ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ "ምህረት " አደረጉለትና ቅጣቱ ወደ እስራት ተለወጠለት ::
መስከረም 1936 አ .ም በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ በያገሩ ተበትነው ታሰሩ :: በላይ ዘለቀና ወንድሙ እጅጉ ዘለቀ ወሊሶ በበቀለ ወያ ጠባቂነት ታሰሩ :: የበላይ ዘለቀ ምቀኖች አሁንም አላረፉለትም ::በላይ ዘለቀ ከዳ ;አመለጠ ጠፋ እየተባለ ይወራ ጀመር ::በቀለ ወያ ተያዘና "ምን ቢሰጥህ ነው የለቀከው ?"ተባለ ::"እረ እኔ አልለቀኩትም አለ :::: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀን ወደ አዲስ አበባ አመጡዋቸውና ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አሰሩዋቸው :.ያ ሰው እናምልጥ እያለ እነ በላይ ዘለቀን ይጎተጉታቸው ጀመር :: አንድ ቀን "ጠባቂዎቻችንን የኛ ወዳጆች ገዝተዋቸዋልና እናምልጥ ::በንዲህ ያለ ስፍራ እነ እገሌ መኪና ይዘው እየጠበቁን ናቸው ::"አል :: "ወንድሞቸ በየቦታው ተበታትነው ታስረው እኔ ማምለጥ ምን ያረግልኛል ?" አለ በላይ ዘለቀ :: "ፈራህ እንዴ በላይ ዘለቀ ?"አለው :: "እኔ የዘለቀ ልጅ !" በላይ ዘለቀ ወንድሙን ላከው መኪናው እተባለበት ስፍራ መኖሩን ለማረጋገጥ ::ወንድምየው በተባለበት ስፍራ መኪና አየ ::እስረኞቹና ጠባቂዎቻቸው አብረው አመለጡ ::እመኪናው ቦታ ሲደርሱ መኪናው የለም ::እንግሊዝም የለም :: ጠባቂዎቻቸው ከዚያ ሮጠው አጠገባቸው ከነበረው ጫካ ገቡና ደጋግመው ተኮሱ ::ምልክት ነው :: በላይ ዘለቀ እጠላቶቹ ወጥመድ ውስጥ መግባቱን አወቀ :: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ከዚያ እሮጠው አመለጡ :: ሰላሌ ደርሰው በቅሎ ለመከራየት ሲነጋገሩ ተከበቡ :: በላይ ዘለቀ በጦር ፍርድ ቤት ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ ፍርዱን አጸደቁት :: ጥር 1937:.በላይ ዘለቀ በስቅላት ሞተ ::እድሜው ሰላሳ አምስት አመት ነበር ::
ጥልያንን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው ::ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ ሰላሳ አምስት አመት ታስረው በለውጡ ተፈቱ::መልኩን ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ እንዲህ ብለው ይገልሱታል :: "አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል ::ከንፈሩ ከበድ ይላል ::ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ ረጅም ጣቱ መልካም ወተት የተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ ::እግረ ቀጭን ::"…………..”
ዛሬም እንደዚህ ነው…. ስንት አድርባዮችና አሰመሳዮች አለን? ኑሮአችንን በሌሎች ህልውና ላይ የመሰረትን? የአፋኝ ሥርዐት ሎሌ በመሆን የወንድሞቻችንን ደም ከንቱ ያደረግን…..?

No comments:

Post a Comment