Jan 31, 2013

ለአባይ ግድብ ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ የተሰበሰበው ከ35 በመቶ በታች ነው


ኢሳት ዜና:-የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ከተደረገበት ካለፉት 2 አመታት ጀምሮ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች እና ግለሰቦች ቃል ከተገባው 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 11 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ለመሰብሰብ የተቻለው ከ200 ሚሊዮን ዶላር ወይም 4 ቢሊዮን ብር ሊበልጥ አልቻለም።
መንግስት  ሰራተኞችን እንዲሁም የንግድ ድርጅቶችን በማስገደድ እስካሁን ያሰባሰበው ገንዘብ ፕሮጀክቱን ለማሰራት ከሚፈጀው ገንዘብ ጋር ሲተያይ እጅግ አነስተኛ ነው። በየጊዜው የሚጨምረው የእቃዎች ዋጋ ባለበት ቢቆም እንኳ ግድቡን በተያዘለት የጊዜ ገደብ  ለማስጨረስ የሚያስፈልገው  ከ90 ቢሊዮን ያላነሰ ገንዘብ ለመሰብሰብ እጅግ አዳጋች እንደሚሆን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲያስጠነቀቁ ቆይተዋል።
በፕሮጀክቱ ላይ በተለያዩ ሞያዎች የሚሳተፉ ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጡት በማኔጅመንቱና ስራውን በሚሰራው የጣሊያኑ ሳሊኒ የአስተዳደር ችግር ምክንያት ስራው በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም። ግንባታው በታቀደለት በአራት አመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ሰራተኞች በእርግጠኝነት ይናገራሉ። መንግስት የግድቡ 14 በመቶ ተጠናቋል በማለት ቢያስታውቅም፣ በተያዘለት የጊዜ ገድብ ያልቃል የሚለውን በእርግጠኝነት ከመናገር ባለቀበት ጊዜ ይለቅ የሚል ቅስቀሳ ማካሄድ ጀምሯል።
መንግስት ህዝቡ ለግድቡ ያለው ስሜት መቀዛቀዙን እና መዋጮውም እያነሰ መምጣቱን በመመልከት አዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን ለመዘርጋት አቅዷል።
ግድቡን ለመስራት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ይጠበቅ የነበረው በውጭ አገር ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቢሆንም፣ የኢህአዴግ ደጋፊ ከሆኑ የዲያስፖራው አባላት በስተቀር አብዛኛው ገንዘብ ለማዋጣት ፈቃደኛ አለመሆኑ ገዢውን ፓርቲ ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።
የአባይ ግድብ የአረቡ አብዮት በተነሳ ማግስት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

    No comments:

    Post a Comment