Mar 18, 2013

“ለምንድነው የኢትዮዽያ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደኣሸን የሚፈሉ?”


‎! …….. የኢትዮዽያ ፖለቲከኞች ………!
ጥያቄ , “ለምንድነው የኢትዮዽያ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደኣሸን የሚፈሉ?”
በኢትዮዽያ የፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች) ኣመሰራረት ርእዮተ ዓለም (Ideology) ወይ ሳይንሳዊ መርህ መሰረት (Principle based) ያደረገ ሳይሆን በዘረኝነት ወይ ጎሰኝነትና ጎጠኝነት የተቃኘ በመሆኑ ነው። የዚ ሁሉ ምክንያት ምንድነው?
1) የማህበረሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማነስ ነው። በኢትዮዽያ መርህ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ማራመድ የህዝብ ድጋፍ ኣያስገኝም። የፖለቲካ rationality የለም። ድጋፍ ለማግኘት የጎሰኝነትና ጎጠኝነት ቅስቀሳዎች ጠቃሚ ናቸው። ‘እንደዚህ ተበደልን፣ እንዲህ ኣረጉን …’ ስትል የህዝቡን ስሜት (ወይ ቀልብ) መግዛት ትችላለህ። የተለያየ ጎሳና ጎጥ የተለያየ ፓርቲ ያመርታል። ለምሳሌ ህወሓት ድጋፍ የሚሰበስበውና ስልጣን የያዘው በዚ መንገድ ነው።
2) የኣብዛኞቹ ፖለቲከኞች ዋና ዓላማ ስልጣን መሆኑ ነው (ስልጣን መያዝና መሪ ሁኖ መከበር በቃ)። ለዚህም ጥሩ ኣማራጭ የየራሳቸው ፓርቲ በመመስረት የፓርቲው ሊቀመንበር (ፕረዚደንት) መሆን ያምራቸዋል። ለዚህም ነው በሀገራችን እነዚህ “33 የተቃዋሚ ፓርቲዎች “ የሚባሉ ጨምሮ ከ60 በላይ ፓርቲዎች ኣሉ የሚባለው።
3) የገዢው ፓርቲ ሴራዎች:: ህወሓት/ኢህኣዴግ ጥሩ ነገር በመስራት ተቃዋሚዎችን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ የመንግስትን ሃብትና መዋቅር በመጠቀም ተቃናቃኞችን በማፍረስና ማዳከም ሴራ መጠመዱ ሌላው ምክንያት ነው። በሚያደርገው በስለላ የተደገፈ conspiracy የተቃዋሚ መሪዎች (የገዢው ፓርቲ የጥፋት ስራ መሆኑ ስለማይገነዘቡ) እርስበርሳቸው እንዳይተማመኑና ኣንድነት እንዳይፈጥሩ ስለሚያደርግ ነው።
4) የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳሳተ የትግል ኣቅጣጫ (Game Theory)። ኣንዳንድ ፖለቲከኞች (እንዳውም ኣብዛኞቹ) የህዝብን ስሜት ለመግዛት ሲባል ዘረኝነትን የሚቃወሙ እየመሰሉ በተግባር ግን ራሳቸው ዘረኝነትን (ጎሰኝነትን) ያጠቃቸዋል። እንደውጤትም ሁሉም ዘረኛ ሁነው ይገኛሉ። ሌሎች ከነሱ ጋ ከመቀላቀል ይልቅ ከነሱ ራሳቸው ለመከላከል ሲሉ ሌላ ድርጅት መመስረት ይፈልጋሉ። ፓርቲዎችም ይበዛሉ።
ለምሳሌ
(ሀ) ኣንዳንድ ዘረኝነት ወይ ጎሰኝነትን እንቃወማለን፣ በዘር መከፋፈል ይቅር እያሉ የሚሰብኩ ኋይሎች ግንቦት -7 ከዴምህት (ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ ወይ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ኣብሮ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለው ይከሳሉ (ይወቅሳሉ)። ይሄ ፓርቲዎች በዘር ተከፋፍለው እንዲቀሩ ያደርጋል።
(ለ) ህወሓት/ኢህኣዴግ በራሱ ጎጠኝነትን እቃወማለሁ እያለ “ዓረና ትግራይ ፓርቲ ከጠላቶቻችን ሸዋ ፖለቲከኞች በማበር የትግራይን ህዝብ ለመግደል እየተንቀሳቀሰ ነው “ በሚል ስም ያጠፋል። ታድያ ዓረና ፓርቲ ኮ ትግራይ የመገንጠል ዓላማ የለውም፤ ከሌሎች የኢትዮዽያ እህት ፓርቲዎች ይሰራል እንጂ ለብቻው መሆንኮ ኣይደገፍም። ኣብሮነት ጥሩ ነው። ዙሮዙሮ ግን ይሄም ፓርቲዎች እንዳያብሩ ምክንያት ይፈጥራል።
(ሐ) ሰመያዊ ፓርቲ የመሰረቱ ፖለቲከኞች (እንደሚባለው) የኢትዮዽያ ኣንድነት ይሰብካሉ። ዘር ወይ ጎሳ መሰረት ያደረገ ፓርቲ እንደማይደግፉም ይነገራል። እነዚህ ሰዎች ታድያ (የሰማሁት ትክክል ከሆነ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ኣስተሳሰብ ከፖለቲከኛ ኣይጠበቅም) የኣንድነት ፓርቲ ኣባላት የነበሩ ሲሆን ፓርቲው (ኣንድነት) እነሱ የማይፈልጉዋቸውን ሰዎች (እነ ስየ ኣብርሃ የትግራይ ተወላጆችን በኣባልነት ስለያዘ) ከፓርቲው ለቀው በመውጣት “ኣዲሱ”ን ሰማያዊ ፓርቲ መሰረቱ። (የፓርቲዎች ቁጥር ጨመረ)።
ይህንን መረጃ (ምሳሌ ‘ሐ’) ትክክል ከሆነ ማለትም ሰመያዊ ፓርቲ ከሌሎች ብሄሮች (ለምሳሌ ትግራይ) በኣባልነት ካልተቀበለ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? እንበልና ሰማያዊ ፓርቲ ስልጣን ያዘ (የኣንድ ፓርቲ ዓላማ ስልጣን መያዝ ስለሆነ) ከዛ እንዴት ኣድርጎ ሀገርን ያስተዳድራል? ወይስ ኣማራ ክልልና ኣዲስ ኣባባ ብቻ ገንጥሎ ሀገር ሊመሰርት ነው?
ጎሰኝነት ወይ ዘረኝነት ኣንቀበልም ስንል ከተለያዩ ብሄሮች በኣባልነት ኣንቀበልም ማለት ሊሆን ኣይገባውም። በኣጭሩ በኢትዮዽያ ፓርቲዎች እንደ ኣሸን የሚፈሉ ገዢ የሆነ ርእዮተ ዓለም መሰረት ያደረገ የፓርቲ ስርዓት ስለሌለ ነው።
በመጨረሻም
በኢትዮዽያ ፓርቲዎች የሚመሰረቱ በርእዮተ ዓለም ልዩነት ምክንያት ኣይደለም ካልን ታድያ የጋራ ነጥባቸው ምንድነው? በኢህኣዴግ ሙስና መሰረት ያደረጉ ጥቅማጥቅሞች ያገናኛቸዋል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኣንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ ደግሞ ገ ዢውን ፓርቲ መጥላታቸው ነው።
የመጨረሻ መጨረሻ
በመርህ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች የሉም ማለት ግን ኣይደለም። ይኖራሉ ግን የህዝብ ተቀባይነት በቀላሉ ለማግኘት ይቸገራሉ። ስለዚ ኣናያቸውም።
የኢትዮዽያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሆይ፡ እባካቹ ኣንድ ጠንካራ ድርጅት ፍጠሩ። 33፣65 እየተባላቹ ኣታሳፍሩን።
It is so!!!     Abraha Desta from Mekele 

No comments:

Post a Comment