ዋና ዜና
አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከካይሮ ሕክምና ፋኩልቲ ካገኙ በኋላ፣ እ.ኤ.አ. ማርች በ1997 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ፈተና አልፈው ተቋሙን ተቀላቅለዋል፡፡
ከዚያም በለንደን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በአሜሪካ፣ በቱርክና በሶርያ በሚገኙ የግብፅ ኤምባሲዎች ሠርተዋል፡፡ የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳና የሆስኒ ሙባረክ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ መስከረም 2003 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡
ከዚያ በፊት ግን ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ባደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የግብፅ ቋሚ ልዑክ ምክትል አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዓባይ ጉዳይ፣ በሁለቱ አገሮች ግንኙነትና በግብፅ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የማነ ናግሽ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱ ትላልቅ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስብሰባዎችን ያወያያሉ፡፡ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሱም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤተሰባዊ የሆነ ቅርበት የመሠረቱ ይመስላሉ፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው?
አምባሳደር መሐመድ፡- ለዚህ አመሰግናለሁ፡፡ በመጀመርያ እዚህ አዲስ አበባ ስኖር አገሬ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ፡፡ በአጠቃላይ ቤተሰቤ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞችና እህቶች ጋር የቀረበ ማኅበራዊ ግንኙነት ነው ያለው፡፡ የአገሮች ግንኙነት እንደ ግለሰቦች ግንኙነት ነው፡፡ እኔ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼ ጋር መልካም ግንኙነት ሳይኖረኝ በሁለቱ አገሮች መካከል ወዳጅነት መፍጠር አልችልም፡፡ ከሕዝቡም ሆነ ከባለሥልጣናቱ የቀረበ ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው ያለኝ፡፡ እዚህ በመኖሬም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተፈጥሮዬ ሁሌም መማር እወዳለሁ፡፡ መማር የሚቻለው ደግሞ ሰውን ከልብ በመቅረብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርብ ኢትዮጵያ እንደመጣ አምባሳደር በሁለቱ አገሮች መካከል ምን ዓይነት አዲስ መሠረት ለመጣል አስበዋል?
አምባሳደር መሐመድ፡- በመጀመርያ ሥራዬን የምወጣው ከአንድ አቅጣጫ አይደለም፡፡ የተለያዩ አቅጣጫዎችን ነው የምመለከተው፡፡ ሥራዬን ከተለመደው የዲፕሎማሲና መንግሥታዊ አሠራሮች ወጣ ባለ መንገድ ነው ለማከናወን የምፈልገው፡፡ ቢሮ ቁጭ ብዬ ደብዳቤዎችንና መልዕክቶችን ከመለዋወጥ ይልቅ፣ ሁሌም ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼ ጋር መጫወትና መወያየት ነው የምመርጠው፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ተጨባጭ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር እፈልጋለሁ፡፡ በመካከላችን ያሉት ሁለንተናዊ የንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም አካዳሚያዊ ትብብሮች እንዲበለፅጉ ነው የምፈልገው፡፡ በሕክምናም እንዲሁ፡፡ ቀደም ሲል ለውስጥ ደዌ ዕርዳታ የሚሰጥ የሕክምና ተቋም እዚሁ አስመርቀን በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ አሁንም በተጨማሪ የኩላሊት መተካት ሕክምና ለማካሄድ አቅደናል፡፡ ካንሰርና ሌሎች ውስብስብ በሆኑ በሽታዎች ላይ ለማገዝ በተጨባጭ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እስካሁን የተለያዩ የሕክምና ቡድኖች ኢትዮጵያ መጥተው ለተለያዩ ታካሚዎች ዕርዳታ አድርገው ሄደዋል፡፡
ሰሞኑን የግብፅ የወደፊቶቹ ዲፕሎማቶች እዚህ መጥተው ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዲገናኙ አድርገናል፡፡ እጅግ ትልቅ ሥራ ነው የተሠራው፡፡ በጣም ነው ደስ ያላቸው፡፡ ከ30 በላይ ሠልጣኝ ወጣት ዲፕሎማቶች እዚህ መጥተው የልምድ ልውውጥ ሊያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ከሌሎች ጋር የነበራቸው ቆይታ እጅግ ጠቃሚ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በጋዜጣና በቴሌቪዥን ከሚያውቋት ውጪ ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል በአካል መገንዘብ ችለዋል፡፡ በወሬ ከሚሰሙት በዓይን ያዩት እጅግ ጠቅሟቸዋል፡፡ ይኼ ለሁለቱም አገሮች የወደፊት ግንኙነት ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከፍተኛ የባህል ልውውጥ እንዲኖር እየሠራን ነው፡፡ የተለያዩ የግብፅ አርቲስቶች መጥተው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ትርዒታቸውን አሳይተዋል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ አርቲስቶችን ወደ ግብፅ ለመውሰድ እየሠራን ነው፡፡ በሃይማኖትም በኩል ዛሬ [ሐሙስ] አምስት የግብፅ ጳጳሳት በአዲሱ ፓትሪያሪክ ምርጫ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዳንድ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ልዑካን ልውውጥ ተደርገው ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ለቆየው ውዝግብም አዲስ ምዕራፍ ከፍተው ነበር፡፡ አሁን ግንኙነቱ ያለበትን ደረጃ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር መሐመድ፡- የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ፍላጎት ትብብር መፍጠር ነው፡፡ በተለይ የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳ በኋላ የሁለቱ አገሮች መልካም ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ይኼ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡ አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ በመተማመን፣ በራስ መተማመንና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሒደቱ ደግሞ በሁለት አቅጣጫ የሚገለጽ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ እውነተኛ ፍላጎቱን የሚገልጽበት ሲሆን፣ የሕዝብ ለሕዝብ (ፐብሊክ) ዲፕሎማሲ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ቀደም ሲል ከግብፅ የመጣው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የወዳጅነትና የትብብር መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ከኢትዮጵያ ደግሞ በቅርቡ ተመሳሳይ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ግብፅ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ ጎን ለጎን የሁለቱም አገሮች መንግሥታት ለዚህ የሕዝብ ፍላጎት ይፋዊ ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ወደተግባር የሚተረጎምበት ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ተጠናክሮ ወደላቀ ወዳጅነት እንደሚሸጋገር እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼ አዎንታዊ ገጽታ እንዳለ ሆኖ ግን ጅምሩ ከልብ የመነጨ እንደሆነ ጥርጣሬ ያላቸው አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ‹‹ስትራትፎር›› የተባለው ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ የመረጃ ኩባንያ የዊኪሊክስን ሰነድ ጠቅሶ ባሰራጨው ዘገባ፣ ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ አዲሱ የህዳሴ ግድብ ላይ አደጋ ለማድረስ ማቀዳቸውንንና የአገሮቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚስጥር ማሴራቸውን ዘግቧል፡፡
አምባሳደር መሐመድ፡- ታሪኩን ሰምቼዋለሁ፣ አንብቤዋለሁም፡፡ ከእውነት የዘለለ ነው፡፡ ምንም መሠረትም የላቸውም፡፡ እውነታው ግን የኢትዮጵያም የግብፅም ዕጣ ፈንታ አንድ ነው፡፡ በታሪክም በመጪው ጊዜም የሚጋሩዋቸው የጋራ እሴቶች አሉ፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚሆኑት ደግሞ በትብብር መንፈስ መሆኑን ተማምነዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፣ የንግድ ልውውጥ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች የአካዳሚክና የሕክምና ትብብሮች እየተደረጉ ነው፡፡ እነዚህ አሉታዊ የሚዲያ ዘገባዎች መሬት ላይ እየሆነ ካለው ተጨባጨ ሁኔታ ፍፁም ተቃራኒ ናቸው፡፡ የዘገባውን መሠራጨት ተከትሎ የግብፅ መንግሥት ውሸት መሆኑን ለኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል፡፡ አንዱ ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛው ዊኪሊክስ ከግብፅና ከሱዳን አገኘሁት ያለው መረጃ የህዳሴው ግድብ ይፋ ከመሆኑ በፊት ነው፡፡ በመሠረቱ ግን በህዳሴው ግድብም ቢሆን ሦስቱም አገሮች [ሱዳንን ጨምሮ] በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አነሳሽነት አንድ የባለሙያዎች የጋራ ቡድን አቋቁመው ቡድኑ በማጥናት ላይ ነው ያለው፡፡ ትብብር ማለት ይኼ ነው፡፡ ቡድኑ በታችኛው ተፋሰስ አባል አገሮች ላይ የሚኖረውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ አጣርቶ በመጪው ግንቦት ወር ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ ነው እንዲህ ዓይነት መሠረተ ቢስ ሪፖርቶች የወጡት፡፡
ሪፖርተር፡- የዊኪሊክስ መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ቢባል እንኳን፣ ሌሎች ተጨባጭ ሥጋቶች ደግሞ ይነሳሉ፡፡ ሱዳንና ግብፅ የዓባይን ውኃ በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም ያስችላል ተብሎ የሚታመንበት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ሳይፈርሙ እስካሁን በእምቢተኝነታቸው ቀጥለዋል፡፡
አምባሳደር መሐመድ፡- ግብፅ፣ ሱዳንና ኮንጎ ይህንን ስምምነት አልፈረሙም ማለት ከትብብሩ መንፈስ መራቃቸውን አያመላክትም፡፡ ምክንያቱም ሦስቱም አገሮች ውኃውን በትብብር መርህ መጠቀምን በፅኑ ያምናሉ፡፡ በዚህም መሠረት የናይል ተፋሰስ መድረክ (NBI) ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ትብብር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) አንዱ የትብብር መርህን ማስፈጸሚያ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ የተለያየ አመለካከት መኖሩ ከትብብር ሒደቱ መውጣት አይደለም፡፡ ትብብር የሚፈጸምበት ማዕቀፍ ላይ ነው ልዩነት ያላቸው፡፡ አንተባበርም ውኃውንም በጋራ አንጠቀምም የሚል አይደለም፡፡ የሐሳብ ልዩነት መኖሩ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ መከበርም አለበት፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው በውይይትና በንግግር አንድ የጋራ የትብብር ቀመር ለመፍጠር ነው፡፡ በዚህ ቀመር ውስጥ ደግሞ በእያንዳንዱ አንቀጽና ጉዳይ ላይ መግባባትና መስማማት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ከአንድ የትብብር ደረጃ ወደ ሌላ ሽግግር ላይ ስለሆንን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ የሚነሳው ትልቁ ቅሬታ በተለይ ግብፅና ሱዳን አሮጌዎቹ ስምምነቶች (እ.ኤ.አ. 1929 እና 1959) ሙሉ ለሙሉ ቀርተው በአዲስ ስምምነት እንዲተኩ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው…
አምባሳደር መሐመድ፡- እነዚህ ነገሮች ከቅኝ ገዢዎቻችን የወረስናቸው ናቸው፡፡ እኛ ራሳችን ያመጣናቸው አይደሉም፡፡ እንደ ድንበርና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ ችግሮች ከቅኝ ገዢዎች የተወረሱ ናቸው፡፡ ያ ማለት ግን ያለፈውን ትተን ወደፊት መራመድ አንችልም ማለት አይደለም፡፡ ያን ለማድረግ ግን መነጋገርና መግባባት አለብን፡፡ በአካሄዳችንም በመድረሻችንም ላይ መነጋገር አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በቅርቡ የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር በካይሮ በተካሄደው ‹‹የዓረብ አገሮች የውኃ ምክር ቤት ስብሰባ›› ላይ የህዳሴውን ግድብ የምትገነባው ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳንን ለመጉዳት ሆን ብላ ያሴረች መሆኗን ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ የተጀመረውን የትብብር መንፈስ አያስተጓጉልም? የግድቡን ተፅዕኖ በማጥናት ላይ ባለው ቡድን ሥራስ ላይ አሉታዊ ሚና አይኖረውም ይላሉ?
አምባሳደር መሐመድ፡- በእውነት ለመነጋገር እንዲሀ ዓይነት ንግግር በምን ሁኔታ ላይ እንደተባለ፣ የተባለውም በትክክል ምን እንደሆነ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከተባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ውጪ ተወስዶ ተተርጉሞ እንደሆነ የተሳሳተ ምሥልና አዝማሚያ ስለሚያስከትል ነው፡፡ አሁን የሳዑዲ ምክትል ሚኒስትር የተናገረውን አላገኘንም፡፡ በሚዲያ የወጣውን ዘገባ ብቻ ነው እየሰማን ያለነው፡፡ እናም ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ነገር ብቻ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ለግብፅም ሆነ ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገር መሆኗን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ዛሬም [ሐሙስ] ራሱ የሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ሚኒስትር ከአቻቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትር ጋር ሲወያዩ እዚያው ተገኝቼ ነበር፡፡ እናም ሳዑዲ ዓረቢያ ከሁለቱም አገሮች ጋር መልካም ወዳጅነቷን ጠብቃ ትቀጥላለች የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በሦስቱም አገሮች መካከል ለተጀመረው የትብብር መንፈስም አዎንታዊ ሚናዋን ትወጣለች ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የዓባይ ቀን በዓል ምክንያት በዓባይ ምንጭ ዙሪያ የተሠሩ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎችን በጋራ ጎብኝተን ነበር፡፡ ምን ተሰማዎት?
አምባሳደር መሐመድ፡- እንዳየኸው በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ነበር የተከበረው፡፡ አንዱ ለበዓሉ ድምቀት ምክንያት የሆነው ደግሞ ከናይል ተፋሰስ መድረክ (NBI) ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የጣና በለስ የውኃ ፕሮጀክት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ያደረጉልንን ገለጻና በዓይናችን ያየነውንም ጭምር ማመን ነው ያቃተን፡፡ በአጠቃላይ የተሠራው ሥራ ዘላቂ ልማት የምንለውና ሦስቱን ኅብረ ቀለሞችን ያካተተ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን በዓባይ ወንዝ ያለው የአካባቢ መራቆትና ሌሎች ችግሮች ለአየር ንበረት ለውጥ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ደግሞ አንድ አገር ብቻውን የሚወጣው አይደለም፡፡ የውኃውን ደኅንነት ለመጠበቅና በወንዙ ዙሪያ ያለውን ሕዝብ ከድህነት ለማውጣት ያለንን የሰውና የቴክኖሎጂ አቅም አቀናጅተን ተባብረን መሥራት ነው ያለብን፡፡ ይኼ ነው እምነታችን፡፡ ይኼ ደግሞ ትብብር ምን ያህል የጋራ ጠቀሜታ እንዳለው ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ከትብብር ወጪ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለንም አመላካች ነው፡፡ ይኼ ግዙፍ ወንዝ የልማትና የብልፅግና እንጂ የግጭትና የቅራኔ ማዕከል መሆን የለበትም፡፡ እምነታችንን ሊያስቀይሱን የሚሞክሩ ሁሉ አይሳካላቸውም፡፡ ምክንያቱም ተቀባይነት የላቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የግብፅ መንግሥታትም ሆኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኃላፊነት የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግብፃውያን ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ምንም ዓይነት የግድብ ፕሮጀክት እንዳትሠራና ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችም ዕርዳታ እንዲከለክሉ ሲያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ይኼ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል ማለት እንችላለን?
አምባሳደር መሐመድ፡- የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አንድ በጥበብ የተሞላ አባባል ደጋግመው ሲናገሩ ሰምቼያለሁ፣ “ጠላታችን አንድና አንድ ብቻ ነው እሱም ድህነት ነው፡፡” ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ኃላፊነት እንዲሰማህ የሚያደርግም አባባል ነው፡፡ የእኛም የጋራ ጠላት ነው፡፡ እዚህ አገር ያለው ድህነት እንዲጠፋ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም እዚህ አገር የሚከሰት አንድ መልካም ሆነ መጥፎ ነገር በግብፅ ላይ ቀጥተኛ ውጤት ነው ያለው፡፡ በግልባጩም እንደዚሁ፡፡ የተሳሰረ ሕይወት ነው ያለን፡፡ በመሆኑም ድህነትን ለማጥፋት በጋራ መሠለፍ አለብን፡፡ ያን ለማድረግ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከት የለብንም፡፡ ያለን አማራጭ በጋራ መበልፀግና መተባበር ብቻ ነው፡፡ ወንዙን በሁለት መንገድ ማልማት ይቻላል፡፡ አንደኛው ሁለታችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ሁለተኛው የዚህ ተቃራኒ ግን አንዱ ሌላውን እየጎዳ መልማት ነው፡፡ ይኼ በፍፁም የማይጠቅመን አካሄድ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነትም የለውም፡፡
ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችን በተመለከተ ግን የራሳቸው የዕርዳታ ማዕቀፍና ፖሊሲ አላቸው፡፡ አንድ የውኃ ባለሙያ ወይም አንድ አገር ስላለ ሳይሆን በራሳቸው መንገድ ነው ዕርዳታ ወይም ብድር የሚሰጡት፡፡ ግብፅ ግን በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዳያገኙ አታደርግም፡፡ እንዲያውም ታበረታታለች፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፕሮጀክቶች በግብፅ በሚገኙ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርሱ እርግጠኞች መሆን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በሁሉም ቦታ ውኃ የሕይወት ምንጭ ቢሆንም፣ ለግብፃውያን ደግሞ ዓባይ ብቸኛ የውኃም የሕይወትም ምንጭ ነው፡፡ ለዚህም ነው ውኃን በተመለከተ አሳሳቢነቱ በግብፅ ሁሌም ከፍ ያለ የሚሆነው፡፡ ሌላ የውኃ ምንጭ የለንም፡፡
ሪፖርተር፡- ከሦስት ሳምንታት በፊት አንድ በዋሺንግተን ዲሲ የሚኖሩ ታዋቂ ግብፃዊ ኢማም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በአገራቸው ክርስቲያኖች ላይ እንዲነሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ስብሰባ ላይ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የሙስሊሞች ንቅናቄ አንፃር የኢማሙን ንግግር እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር መሐመድ፡- ስለዚህ ነገር ሰምቼያለሁ፣ የተባለውንም አድምጬያለሁ፡፡ ለእኔ እንዲህ ዓይነት ትምህርት በፍፁም ሃይማኖታዊ አይደለም፤ እስልምናንም ክርስትናንም አይወክልም፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ የጋራ አስተምህሮ አላቸው፤ ስለ ፍቅር፣ መረዳዳትና መከባበር ነው የሚያስተምሩት፡፡ ስለመገዳደልና ስለመታኮስ አይደለም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ራሱን እኔ ኢማም ነኝ የሚል ሁሉ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ፂሙን ያስረዘመ ሁሉ ኢማም አይባልም፡፡ እዚህ ላይ ነው ቁም ነገሩ፡፡ እንዲህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት እንደ ሃይማኖት ጥሪ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- የግብፅ መንግሥት ግን የኢማሙን ንግግር በመቃወም መግለጫ አላወጣም እኮ?
አምባሳደር መሐመድ፡- ንግግሩ እንደ ቁም ነገር አልተቆጠረም፡፡ እንደ አንድ የሃይማኖት ጥሪም አልተቆጠረም፡፡ የትኛውንም የግብፅ የኅብረተሰብ ክፍልም ሆነ የመንግሥት አካል አይወክልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ከንቱ ጥሪ ማስተባበል ትልቅ ቦታ መስጠት ይሆናል፡፡ ፀረ ሃይማኖትና አፍራሽ ጥሪ ነው ብለን እንለፈው፡፡
ሪፖርተር፡- ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላም ካይሮ ውስጥ አሁንም ሕዝባዊ አመፁ ቀጥሏል፡፡ ስለ ወቅታዊ ሁኔታው አጭር ማብራሪያና በአካባቢው ስለሚያስከትለው ተፅዕኖ ሊነግሩን ይችላሉ?
አምባሳደር መሐመድ፡- እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ አመፅ አሳባቢና ፈተኝ ነው፡፡ የግብፅ የፖለቲካ ሒደትንና የግብፅ ማኅበረሰብን ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ እያሸጋገረ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2011 ላይ የፈነዳው የግብፅ ሕዝባዊ አመፅ የመሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት ነው፡፡ በአንድ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ከተከሰተ በኋላ ድኅረ መንቀጥቀጥ (After Shock) ይኖራል፡፡ እሱን ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ይኼ ደግሞ የማናቸውም ሕዝባዊ አብዮቶች ባህሪ ነው፡፡ ድኅረ አብዮት ግራ የሚያጋባ፣ የተወሳሰበና ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡ የግብፅ አብዮትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በሽግግር ላይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተመሳሳይ ወቅት የተከሰቱ ሕዝባዊ አብዮቶች የተቀዛቀዙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት እንዲህ ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ያስገደደው እንግዳ ነገር ወይም አዳዲስ ተዋናዮች የሉበትም? በአጭር ጊዜስ እልባት የሚያገኝ ይመስልዎታል?
አምባሳደር መሐመድ፡- የሕዝባዊ አብዮቱን የሽግግር ጊዜ ለማሳጠር ኃላፊነት መውሰድ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ በአጭር ጊዜ ዕልባት ያገኛል የሚል ተስፋም አለኝ፡፡ ነገር ግን አንድ እውነት አለ፡፡ የፖለቲካ ሁኔታው አዲስ ክስተት ይታይበታል፤ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ ተዋናዮችም ተቀላቅለውበታል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ተዋናዮች ገንቢ የሆነ የፖለቲካ ማዕቀፍ መፍጠር ግድ ይላቸዋል፡፡ ይኼንን አዲስ ማዕቀፍ ለመፍጠር የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ያላቸው ፖለቲከኞች መናበብ፣ መግባባትና የጋራ መድረክ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን ለማድረግ ትንሽ ጊዜ እየወሰደ ይሆናል፤ ምክንያቱም ሃልዮት አይደለም ሒደት ነው፤ ክስተትም ነው፡፡ ወሳኝ የፖለቲካ ድርድር የሚደረግበት ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ያ ማለት አንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ የማይታረቅ የፖለቲካ ልዩነትም አለ፤ መቻቻል አለባቸው፡፡
ያ ልዩነት በዲሞክራሲያዊ አግባብ ጊዜ ራሱ የሚፈታው ይሆናል፡፡ እስካሁን የጠፋው ይኼ የጋራ መድረክ ነው፡፡ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ግን አለ፡፡ እየተከናወነ ካለው ለውጥ ጀርባ የግብፅ ሕዝብ አለ፡፡ በፖለቲካ ሒደቱ ንቁ ተሳታፊ ሆኖ መቀጠል አለበት፡፡ የአዲሱ የግብፅ ታሪክ ዋና ተዋናይ መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ ሚናው ከዚህ ሒደት ውጪ መሆን እንደሌለበት በደንብ የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡
No comments:
Post a Comment