ከበትረ ያዕቆብ
ዉድ የሀገሬ ልጆች ከሁሉም በማስቀደም እንደምን ናችሁ ? ደህና ናችሁ ? እንዴት ናችሁ ? ስል የጠበቀ ሰላምታየን ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ መቼም እዚች ላይ ምነዉ ሰላምታ አበዛህሳ እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም “አሸባሪ ፣ ፀረ ሰላም ፣ አክራሪ”… ወዘተ የሚል ተለጣፊ ስም ለሀገር ወዳድና ለመብታቸዉ መከበር ድምፃቸዉን ለሚያሰሙ ሁሉ በጅምላ እየተሰጠ ዜጎች በሀሰት በሚወነጀሉበት ሀገር ፤ በእያንዳንዷ ቀን እንደ መልካም ተግባር መሰል ዜጎችን ጠልፎ ለመጣል የተንኮል ወጥመድ ሲጠመድ በሚዋልበት ሀገር ፤ በየስራ ቦታዉ ፣ በየመዝናኛ ስፍራዎች ፣ በየመንገዱ… ሲያነፈንፉ የሚዉሉ የወሬ ‹‹ተኩላዎች›› እንደ አሸን በፈሉበት ወቅት ፣ ንፁህ ዜጎች በግዳጅ ያልፈፀሙትን ኃጢያት እንዲናዘዙ በሚገደዱበት ሀገር ፤ በልቶ ማደር በከበደበት ጊዜ አጥብቆ ደህንነትን መጠየቁ ተገቢ ነዉና፡፡ እንደዉም ከዛም በዘለለ ብዙ ቢባል እንኳ የሚበዛ አይመስለኝም፡፡ መቼም እዚህ ላይ ለማለት የፈለኩት ለሁሉም ሰዉ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ለሰላምታ ያህል ይህን ካልኩ ወደ ፍሬ ሀሳቤ ልለፍ፡፡
እንደሚታወቀዉ በአለማችን ለጋዜጠኞች አደገኛ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ እንደዉም ግንባር ቀደሟ፡፡ እርግጥ ከላይ ከጠቀስኩት በመነሳት ለምን ለጋዜጠኞች ብቻ ትላለህ ፤ ጠቅለል አድርገህ ለዜጎቻቸዉ አደገኛ ከሚባሉት አገራት መካከል አገራችን ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሟ ናት አትልም? ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም ያን ያልኩት በዋናነት በፅሑፌ ላነሳዉ ወደ ፈለግኩት ርዕሰ ጉዳይ በቀጥታ ለመንደርደር ያመቸኛል በሚል እንጅ ትክክል ናችሁ፡፡ እናም እንደሚታወቀዉ በሀገራችን ጋዜጠኞች ለብዙ ችግርና ፈተና ይዳረጋሉ፡፡ ለምሳሌ ከሚደርስባቸዉ መጠነ ሰፊ የሚባል ማስፈራሪያ ፣ ዛቻና ወከባ ባሻገር በእብሪተኛና ኃላፊነት በጎደላቸው የደህንነት ሰዎች ሰብዓዊነት በጎደለዉ ሁኔታ ይደበደባሉ ፣ ያለ ምክንያት ለሰዉ ልጅ ቀርቶ ለእንስሳት እንኳን ወደማይመቹ ‘እስር ቤቶች’ ይወረወራሉ ፣ ሲልም ከዚያ የከፋ ነገር ይፈፀምባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ሙያዊ ኃላፊነታቸዉን መወጣታቸዉ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በእነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት አለሙ ላይ እየተፈፀመባቸዉ ያለዉ ዘግናኝ ግፍ እንዲሁም በእነ ተመስገን ደሳለኝ ላይ እየደረሰ ያለዉ መከራ ለምሳሌነት ተጠቃሽ ነዉ፡፡ እንግዲህ እኔም ይህችን አጭር ፅሑፍ ቢጤ ለመፃፍ ምክንያት የሆነኝ ከዚህ ከሀገራችን መንግስት ጋዜጠኞችን የማሳደድ አባዜ ጋር በተያያዘ በእኔም ላይ በደህንነት አባሎች እየተፈፀመብኝ ያለ ወንጀል ሲሆን ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያዉቀዉ መልካም ነዉ በሚል እሳቤ አንዳንድ ነገሮችን ለመጠቆም ወድጃለሁ፡፡
ዉድ የሀገሬ ልጆች እንደሚታወቀዉ ከዚህ በፊት በደረሱብኝ የተለያዩ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች ምክንያት ለደህንነቴ በመስጋት ከምሰራበት መንግስታዊ ካልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ስራዬን ለመልቀቅና መኖሪያዬን ከባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመቀየር ተገድጄ ነበር፡፡ ይህንንም ያደረግኩት ከባህር ዳር ይልቅ አዲስ አበባ አንፃራዊ ሰላም ያለበትና ለደህንነቴም ቢሆን የተሻለ ነዉ በሚል ተስፋ ነዉ፡፡ እንግዲህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዋናነት መሰረቱን ጣሊያን ሀገር ላደረገ http://www.assaman.info ለተባለ ድህረ-ገፅ የምሰራ ስሆን ፤ በተጨማሪም በፈቃደኝነት ሀገርን የማገልገል አላማ በማንገብ http://www.thedailyjournalist.com በተባለ ድህረ-ገፅ እና እንደከዚህ ቀደሙ የግሌ በሆነዉ http://www.ethiopiahot.wordpress.com (personal Blog) ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ከዚህም ባሻገር ፅሑፎቸን እንደ http://ecadforum.com ላሉ የተለያዩ ኢትዮጵያዊ ድህረ ገፆች በመላክ እንዲወጡ አደርጋለሁ፡፡
ይሁንና ምንም እንኳን እዉነቱ የምሰራዉ ስራ ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ቢሆንም ሰሞኑን እየደረሱብኝ ያሉት ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች ከበፊቶቹ እየተለዩና እየከበዱ የመጡ ሲሆን ፤ ከእስራት ወደ ግድያም ተሸጋግሯል፡፡ የምንደዉለዉ ከማዕከላዊ ነዉ የሚሉት እነዚህ የደህንነት ሰዎች በፅሑፎቼ ላይ ተገቢ አስተያየት ከመስጠት እና እንዲስተካከል ከመጠየቅ ይልቅ በአምባገነን ስሜት አፋቸዉን ሞልተዉ መፃፍ አቁም ስንልህ ባለማቆምህ “ልናስወግድህ” ነዉ በማለት እየዛቱብኝ ይገኛሉ፡፡ የዛቱትንም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እየገለፁ ይገኛል፡፡
ለምሳሌ በጥር 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ በ7፡51 ሰዓት ላይ በተደረገልኝ የስልክ ጥሪ፡- “ደጋግመን እንድታቆም ነግረንህ ነበር፡፡ አንተ ግን እንኳን ልታቆም እንደዉም ብሶብሃል፤ባለፉት ግዚያት በተደጋጋሚ ይከሰስ ተብሎ አስፈላጊ ዶክመንቶችን በመሰብሰብ አንዳንድ ዝግጅት ስናደርግ ነበር፡፡ በተለይም ከኦጋዴን ጋር በተያያዘ ፅፈህ በለቀቅከዉ ፅሑፍ እና ከዚያ ወዲህ በለቀቅካቸዉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በቅርቡ ቶርቸር ምናምን በሚል ሌላ ፅሑፍ ለቅቀሀል፡፡ ስለሆነም አሁን አንተን ማስወገድ የሚለዉን የተሻለ አማራጭ ሁኖ አግንተነዋል፡፡ በማንኛዉም ዓይነትዘዴ አንተን ማስወገድ፡፡” የሚል ከበድ ያለ ዛቻ ሰንዝረዉብኛል፡፡
በድጋሚ በጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ በ10፡05 ሰዓት ላይ በተደረገልኝ ሌላ የስልክ ጥሪ ደግሞ፡- “ባለፈዉ የነገርኩህን አቅልለህ ወይም እንደ ቀልድ እንዳላየኸዉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡… ከዚህ በኋላ ከአንተ ጋር የመጨቃጨቂያ ጊዜ የለንም፡፡ …የስራህን ዋጋ በቅርቡ ታገኛለህ…፤ ተዘጋጅ!!” በማለት ዝተዉብኛል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች በተጨማሪ እነዚህ የደህንነት ሰዎች የተለመደዉን “ሽብርተኛ” የሚል የሐሰት ካባ በሙያ ጓደኞቼ ላይ እንደደረቡት ሁሉ በእኔ ላይም ለመደረብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በተደጋጋሚ “እያንዳንዷን ስራህን እናዉቃለን ፣ ለማን እንደምትሰራም እንዲሁ ፣ ስለአንተ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን…” እያሉ ለሐሰት ዉንጀላ መንገድ እየጠረጉ ይገኛል፡፡ በተለይም በጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በተደረገልኝ የስልክ ጥሪ ላይ ከንግግራቸዉ በግልፅ እንደተረዳሁት የኢህአዴግ መንግስት “አሸባሪ” ሲል ከፈረጀዉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጭ ግንባር(ኦብነግ) ጋር ምንም የሚያገናኘን ነገር በሌለበት ሁኔታ ግንኙነት ያለ ለማስመሰል እየሞከሩ ነዉ፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የግንባሩ በሆነዉ ድህረ-ገፅ ላይ የወጡትን ፅሑፎቼን ለግንኙነቱ እንደ አንድ ማሳያ እንደሆኑ በተዘዋዋሪ እየጠቀሱ ይገኛል፡፡
እዚህ ላይ ግልፅ ማድረግ የምፈልገዉ እነዚህ ፅሑፎች እኔ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጭ ግንባርን ለመርዳት በማሰብ የፃፉኳቸዉ ወይንም እኔ በቀጥታ ለግንባሩ የላኳቸዉ አለመሆናቸውን ነዉ፡፡ ይልቁንም የግንባሩ ጋዜጠኞች ከተለያዩ ድህረ-ገፆች ላይ ራሳቸዉ እንደማንኛውም የዓለማችን ጋዜጠኛ የወሰዷቸዉ ናቸዉ፡፡ ሆኖም ግን በእኔ ስለተፃፉና ስሜ ስለተጠቀሰባቸዉ ብቻ ያንን ሊሉ ችለዋል፡፡ ይህም ደግሞ ድህረ-ገፆችና የዜና አዉታሮች መረጃን እንዴት እንደሚቀባበሉ ጠፍቷቸዉ ያደረጉት ነዉ የሚል እምነት የለኝም ፣ እንዴትስ ድህረ-ገፆችን በማናለብኝነት ሲዘጉ ፣ ሲከፍቱ ፣ ኢሜሎችን ያለ ይለፍ ቃል (Password) ሲጎረጉሩ ለሚዉሉት የኢህአዴግ ‹‹ተኩላዎች›› ይህን መረዳት ያዳግታቸዋል?
ዉድ የሀገሬ ልጆች! እኔ ለማንም ኢትዮጵያዊ መጥፎ የምመኝ ፣ የሀገርን ደህንነት ለርካሽ ጥቅም ስል አሳልፌ የምሰጥ ፣ ሽብር ፈጣሪ… አይደለሁም፡፡ እኔ ሀገሬን ፣ ወገኔን የማፈቅር ፣ ለሀገሬና ወገኔ ለሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ፣ ፍቅርና ብልፅግናን ሌት ተቀን የምመኝና የምሰራ አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ እኔ አቅሜ በቻለዉ መጠን በሙያዬ ሀገሬንና ወገኔን ለማገልገል ሙሉ በሙሉ ፍቃደኛ የሆንኩና ለዚያም የምንቀሳቀስ ተራ ሰዉ ነኝ፡፡ እነርሱ ሊያስመስሉ እንደሚሞክሩት አይነት ወንጀለኛ ሳልሆን መብቱን በአግባቡ ለመጠቀም የሚታትር ንፁህ ዜጋ ነኝ፡፡ ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግልፅ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው የደህንነት ሰዎችም ሆኑ አለቆቻቸዉ አንድ ሊያዉቁት የሚገባ ቁም ነገር አለ እላለሁ፡፡ ይህም እኔንና መሰል ምስኪን ጋዜጠኞችን አሳዶ በመደብደብ ፣ በማሰር ወይም በመግደል የመንግስትን ጉድፍ ከአለም ህዝብ አይን መሸሸግ ከቶም አይቻልም፡፡ እንኳን እነርሱ እንደሚያስቡት ቀርቶ ጊዜያዊ መፍትሄ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ መሰል እርምጃቸዉ የሚያመልኩትን ፓርቲያቸዉንም ሆነ የገነቡትን አምባገነናዊ አገዛዝ የባሰ መጥፎ ገፅታን እያላበሰዉና በሀገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ተቃዉሞን እያስከተለበት ይሄዳል፡፡ ይሄም ዞሮ ዞሮ የሚፈሩትን ዉድቀት ያስከትላል፡፡ እዚህ ላይ ምናልባት እነ እስክንድር ነጋን በማሰራቸዉ እየደረሰባቸዉ ያለዉ የፖለቲካ ክስረት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ደግሞም ዱላዉና እስሩ የበለጠ እልህን ይፈጥር ይሆናል እንጅ እኔንም ሆነ የሙያ አጋሮቼን ከምንወደዉ ሙያችን ሊያቆራርጠን ፍፁም አይቻለዉም፡፡
ዉድ የሀገሬ ልጆች! ሀገር እንድታድግ ወይንም በማይጨበጥ ተስፋ ኢህአዴግ አስመዘግበዋለሁ የሚለዉ አይነት የኢኮኖሚ ብልፅግና ታስመዘግብ ዘንድ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ በየተሰማራበት የሙያ ዘርፉ የሙያዉን ስነ ምግባር አክብሮ በትጋት ሊሰራ ይገባል፡፡ ጋዜጠኛዉ ፣ ዶክተሩ ፣ ኢንጅነሩ ፣ ነጋዴዉ ፣ መምህሩ ፣ ፖለቲከኛዉ… ሁሉም፡፡ ይህ የግሌ አመለካከት ሳይሆን የአለም ህዝብ በጋራ የተስማማበት እዉነት ነዉ፡፡ ከዚህ የእዉነት ሀ፣ ሁ በመነሳትም ባሳለፍኩት የስራ ጊዜያቶች በምወደዉ የጋዜጠኝነት ሙያዬ ለሀገሬ ይበጃል ያልኩትን በታማኝነት ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁንም እየሞከርኩ እገኛለሁ፡፡ ለወደፊቱም ሙያዬ ያልተበረዘ ንፁህ መረጃን ለህዝበ ማድረስ እንደመሆኑ ያንን ከማድረግ ምንም አይነት ማስፈራሪያም ሆነ ዛቻ እንደማያቆመኝ በእርግጠኝነት ለመናገር እወዳለሁ፤ ይህንንም እናንተ ዉድ የሀገሬ ልጆች በግልፅ እንድታዉቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment