ምፃችን ይሰማ
ምሽት ላይ ሙስሊሞች በቤታቸው መቀመጥ አልቻሉም
የፍርድ ቤት ማዘዣና ምክንያት የሌላቸው የሌሊት ፍተሻዎች በአዲስ አበባ
ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ መተግበር የጀመረውና ከዚህ ቀደም በተለይም በደቡብ ወሎ በስፋት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የሙስሊም መኖሪያ ቤቶችን ድንገት በመውረር የሚካሄድ ፍተሻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰማ፡፡ ባለፉት ሁለት ሌሊቶች የተካሄደው ድንገተኛ የቤት ውስጥ ፍተሻ ኮልፌ ቀራንዮ፣ ጉለሌ፣ እና ልደታ ክፍለ ከተሞችን ያጠቃለለ ሲሆን ዛሬ ደግሞ እርምጃው ወደ የካ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ሰፍቷል፡፡ ትላንት በኮልፌ ቀራንዮ ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር አለበት በሚባለው ቤተል እና አካባቢው በተለየ መልኩ የበርካታ ሙስሊሞችን ቤቶች ለፍተሻ እና ዘረፋ ተጋልጧል፡፡ የቤት ውስጥ ፍተሻ ሕገ መንግስቱ እንዳስቀመጠው የፍ/ቤት ማዘዣ ሊኖረው እንደሚገባ ቢታወቅም ፍተሻው ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ እና የፍርድ ቤት ማዘዣ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፈታሽ የሚባሉት የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው በሚገኙ ካድሬዎች አማካኝነት የሙስሊም ቤት በመጠቆም በቁጥር በርክተው አንድ ቤት ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፤ ፖሊሶቹ ባልተለመደ መልኩም ፊታቸው ላይ ጭምብል እንነደሚያደርጉ ተነግሯል፡፡ ፖሊሶች ኢስላማዊ የሚባሉ መጻህፍትን በፍተሸው ወቅት እንደሚሰበስብ የታወቀ ቢሆንም ውድ ዋጋ ያላቸውንም ሞባይልና የወርቅ ጌጣጌጥ የመሳሰሉ ንብረቶችንም እንደሚዘርፉ ተሰምቷል፡፡ ይህ ተግባር ከዚህ ቀደም በብዙ ክልሎች በተለይም በአወሊያ፣ በደሴና በአንዋር መስጊድ ግርግር ወቅት በስፋት መስተዋሉ የሚታወስ ነው፡፡ ብዙ ሙስሊሞችም ንብረታቸውን በጸጥታ ሀይሎች ተዘርፈዋል፡፡
የፍተሸው እና የዚሁ አዲስ ዘመቻ አላማ ከወዲሁ የታወቀ ሲሆን በዋነኝነትም በከፍተኛ ጥንካሬ ተቃውሞውን እያካሄደ ያለውን ሙስሊም ኅብረተሰብ ለማስደንበር እና ስጋት ውስጥም ለመክተት የታለመ ነው፡፡ ምንም እንኳ ካለፉት 12 ወራት ወዲህ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የፖሊሶች እና የደህንነት አካላት ያልተቋረጠ ድብዳበ እስርና መሰል ፍተሻዎች እና እንግልቶች ሰላባ ሆነን መቆየታችን እሙን ቢሆንም፤ የሚፈጸምብንን ሁሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና ማስፈራሪያዎች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገን በተቃውሞአችን መቀጠላችን መንግስትን የበለጠ እልህ ውስጥ እየከተተው ተስፋ ቆርጧልም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል፡፡
መንግስት አሁን ባለው ሁኔታ የትኞቹንም የህገ መንግስትና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ያለ ሀፍረት በአደባባይ እየጣሰ የተስፋ መቁረጡን ከፍታ እያሳየንም ይገኛል፡፡ መንግስት ከሀገር ውስጥና ከውጪው አለም ከፍተኛ ትችትና ነቀፌታ የተቀበለበት ጅሀዳዊ ሀረካት ፊልምና፤ ፊልሙን በማሰራጨት ከተላለፋቸው የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎችና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተጨማሪም ፊልሙ ያስገኝልኛል ብሎ የገመተው ውጤት ሙሉ በሙሉ መና ቀርቶ በተቃራኒው ሕዝቡን ለከፍተኛ ተቃውሞ ማነሳሳቱ፤ መንግስትን መሰል የተሰፋ መቁረጥ መገለጫ እርምጃዎች ውስጥ ከተውታል፡፡ ዛሬም መንግስት ጥያቄዎቻችንን ይመልስ፤ መሪዎቻችንንም ይፍታ የሚለው መልእክታችን አለ፡፡ ይህ ካልሆነ ትግላችን በአዲስ መንፈስና ምዕራፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረግጠን እንገልጻለን፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment