Feb 22, 2013

ከቫንኮቨር ፀደንያ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስትያን የተሰጠ የአቋም መግለጫ



በስመ አብ በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!!
Ethiopian-Orthodox-Church-Holy-Synod

በሕጋዊውና በብፁእ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመራው የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያስተላለፈዉን የአቋም መግለጫ ስለመደገፍ፡፡

ለአምላካቸዉ ለእግዚአብሄር አምላክነት በግልፅ ስለመሰከሩና ስለተጋደሉ አባቶቻችን በቅዱሳን መጻህፍት እንደተፃፈው በብሉይ ኪዳን ነቢያት አባቶቻችን ፣ በአዲስ ኪዳን ሐዋሪያትአባቶቻችን ፣ ባደረጉት ተጋድሎዎች ተጠብቆ የኖረዉን ስርዓት እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ በክርስቶስ ደም የቆመችዉን የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችንን ዶግማና ቀኖናዋን ሳይፋረስ የመጠበቅና የማስጠበቅ ብሎም ለትውልድ የማስተላልፈ ክርስቲያናዊ አደራ አለብን፡፡
በመሰረቱ ወደ ኋላ ዞር ብልን ስንመለከት የትኛውም ነብይ ወይንም ሐዋሪያ ምንም አይነት ፈተና ሳያገኝ ቅድስናን ወይንም ነብይነትን የተቀበለ የለም፡፡ አንገታቸውን ለሰይፍ ፣ ቆዳቸውን ለስለት፣ ሰውነታቸውን በድንጋይ ተወግረው ስለ እግዚሃቢሄር አመላክነት ለመመስከር ሕይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ይህንን ሃይማኖታችንን ለቀጣዩ ትውልድ አቆይተውልናል፡፡
ታዲያ እኛም ዛሬ እንደ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ያገባናል እንላለን፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች አወዛጋቢ የነበረው የሁለቱ ሲኖዶሶች ጉዳይ በእርቅና በሰላም መንገድ እንዲፈታ ከቤተክርስቲያንዋ አብራክ የወጡት ወገኖቻችን ላለፉት ሶስት አመታት የእርቁን ሂድት ሲያካሂዱ እንደነበር በዜና ማሰራጫዎች በስፋት ሲነገርበትና ስንከታተለው ሰንብተናል፡፡
ከጅምሩ በቅንነትና ለአንድንት ያልትንሳውና የመንግስት እጅ ያለበት የአዲስ አበባው ሲኖዶስ በአባ ዻውሎስ እልፈት የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ያለ አግባብ በቀድሞው የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስተር በነብሩት በአቶ ታምራት ላይኔ ትእዛዝ የተናደውን የቤተክርስትያንዋን ቀኖና እንደማስትካከል ዛሬም እነ አባይ ፀሀይ በሃይማኖታችን ጣልቃ በመግባት የእርቁን ሂደት ሳይቋጭ አዲስ ፓትሪያርክ ለመሾም እየትዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ የዛሬ ዋና መልእክታችን በገሀድ እየተፈፀመና እየተነገረ ያለዉን ለኦርቶዶክስ ምእመናን በድጋሚ ለማሰማት ሳይሆን በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ሲኖዶስ ያወጣውን መግልጫ ሙሉ በሙሉ እንደምንደግፍ ለማሳወቅ እና ዛሬም እንደትላንትናዉ ከአባቶቻችን ጎን በፅናት እንደምንቆም እኛ የፀደንያ ቅድስት ማሪያም ልጆቻቸው በአንድ ድምፅ እንገልፃለን፡፡
ልማት ማለት የነበረዉን እየናዱ ታሪክን እየደመሰሱ ከሆነ ጥፋት እንጂ ልማት አንለዉም፡፡ ለዘመናት የቆየዉንና እንደ ሀገር ቅርስ የሚታየዉን ቤተክርስቲያናችንን እያፈራረሱ የሸንኮራ ተክል መትከል ማለት የሀገርን ሀዉልትና የታሪክ አሻራን ከምጥፋት ለይተን አናየውም፡፡ እንደዋልድባ ከመሳሰሉት ገዳማት ሙሁሮችና ሊቆች የሚፈልቁበት ስፍራ በልማት ስም ማፈራረስ ማለት ጅረቱን ለማቆም ምንጩን ማድረቅ እንደሚሉት ሁሉ ይህ የሀይማኖት፣የባህልና የአገር ማጥፋት ሴራ ክርስትያን ወገኖች ልናስተዉልና በጋራ ልንቋቋመው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ዛሬም ለዚህች አገር በውጪው አለም ተሰደው ወያኔ በቤተክርስቲያናችን ዉስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እያጋለጡና እየተፋለሙ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ችቦ አቀጣጥለው ለቀጣዩ ተውልድ እያስትላልፉ ያሉት አባቶቻችን ትላንትም የጣሊያንን የጠላት ሀይል ታቦትና ካህናትን ጭምር በመያዝ መስዋዕትነትን ከፍለው አኛ ልጆቻቸው በነፃነትና በክብር እንድንኖር ያደረጉት እነኚሁ አባቶቻችን ናቸው፡፡ ታዲያ ከዚህ አብራክ የወጣው ትውልድ ግን አገርና ሀይማኖት ሲጠፋ በየምክንያቱ ተከፋፍሎ አንገቱን ደፍቶ በባይተዋርነት መኖርን የመረጠ ይመስላል፡፡
ከፊታችን ለተጋረጠው ችግር ዝምታና አንገት መድፋቱ መፍተሄ አንደማይሆን አውቀን እውነተኞች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ልጆች እርስ በእርስ ያለውን ንትርክ ትተን ለአገራችንና ለቤተክርስቲያናችን ቅድሚያ በመስጠት እጅ ለእጅ ተያይዘን አጥፊውን በአንድነት እንቋቋም ብለን ጥሪያችንን እናቀርባልን፡፡
እግዚአብሄር አምላካችን ቤተክርስቲያናችንን እና አገራችንን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፡፡
ከፀደንያ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን
ቫንኮቨር, ብሪቲሽ ኮሎምብያ

No comments:

Post a Comment