Feb 8, 2013

እኛ አቡበከር አህመድ ነን!



ድምፃችን ይሰማ
እኛ አቡበከር አህመድ ነን! የሕዝብ ውክልና ተሰጥቷቸው ሕግ በሚፈቅደው መርህ የሕዝብን ጥያቄ በመያዝ መፍትሄ ለማፈላለግ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሳቢያ ብቻ ወኪሎቻችን እነሆ ዛሬ አሸባሪ ተሰኝተውና ሕጋዊ እና መልካም ስራቸውም ከሽብር ድርጊት ጋር ለማያያዝ ተሞክሮ በመንግስት ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ ሕጋዊ ኮሚቴዎቻችንን ‹‹አሸባ›› እና ‹‹ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚንቀሳቀሱ›› በማለት በይፋ ወንጅሏቸዋል፡፡ መንግስት የሀሰት ድራማ በማዘጋጀት ኮሚቴዎቻችንን ከህዝብ ለማግለል ከንቱ ሙከራ አድርጓል፡፡ በርካታ ወራት የደከመበትንና ትርፍ አልባ የሆነውን ‹‹ፊልሙንም›› ፍፁም የሕግ የበላይነትን በደፈጠጠ ድፍረትና ማን አለብኝነት ለሕዝብ አቅርቧል፡፡ መንግስት በሠላማዊ መንገድ መብቱ እንዲከበርለት ድምፁን የሚያሰማውን ያልታጠቀ ሲቪል ሠላማዊ ሕዝብ ከሶማሊያው አልሸባብ እና ሌሎች ታጣቂዎች ጋር ለማዛመድ ቅንጣትም ያክል እፍረት አልተሰማውም፡፡ ሰላማዊው ሕዝብ በመንግስት አንደበት በይፋ አሸባሪ ተብሏል፡፡
ነገ ጁምዓ በእስር ላይ የሚገኙት ውድ ኮሚቴዎቻችንና ዳዒዎቻችን ዛሬም ህጋዊ ወኪሎቻችንና የሠላም አምባሰደሮቻችን እንጂ ሽብረተኞች አለመሆናቸውን ለማረጋገጥም ታላቅ አገር አቀፍ የተቃውሞ መርሀ ግብር ይኖረናል-ኢንሻ አላህ፡፡ በዕለቱም ኮሚቴዎቻችንና እኛን በፍጹም ሊለያዩን እንደማይችሉም ጠንካራ መልዕክት እናስተላልፋለን፡፡ እኛ አቡበከር አህመድ ነን፣ እኛ ካሚል ሸምሱ፣ እኛ ያሲን ኑሩ፣ እኛ አህመድ ሙስጠፋ፣ እኛ ኑሩ ቱርኪ ነን፣ እኛ ኮሚቴው ነን፣ እኛ በቃሊቲ የታሰሩ ወንድሞቻችን ነን፣ እኛ በመላዋ ኢትዮጵያ የምንገኝ ሕገ መንግስታዊ መብታችንን የተገፈፍን፣ የዜግነት ክብራችንን የተነጠቅን ጭቁን ሙስሊሞች ነን፡፡ እኛ ሰላማዊአገር ወዳድ ዜጎች ነን፡፡
ተቃውሞው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ በታላቁ አንዋር መስጂድ ይካሄዳል፡፡ ለነገው ተቃውሞ ሁላችንም ‹‹አሁንም ሕጋዊ ወኪሎቻችን ናቸው›› የሚለውን መሪ ቃላችንን በወረቀት አትመን ከፍ አድርገን የምናሳይ ሲሆን ዝርዝር የተቃውሞ ሂደቱ እንደሚከተለው ይሆናል፡-
• የጁምዓ ሰላት እንደተጠናቀቀ ለ 5 ደቂቃ ሃበሻዊው ቢላል በጠራራ ፀሃይ በባዶ ሰውነቱ ረመጥ ላይ አ ስተኝተው ቋጥኝ ሲጭኑበት እንዳለው ‹‹አሐዱን አሐድ!›› እንላለን፡፡
• ሕገ መንግስታዊውን የእኛንና የመሪዎቻችንን መብት እንዲሁም የፍ/ቤት ውሳኔ ጭምር በኢትዮጵያ እያልተከበረ እንዳልሆነ ለማሳየት ለ 5 ደቂቃ ‹‹ሕጉ ተጥሷል!›› እንላለን፡፡
• ለ 5 ደቂቃ ‹‹የሐሰት ክስ አይገዛንም!›› በማለት ኮሚቴዎቻችን በሽብር መከሰሳቸውን በጭራሽ እንደማንቀበልና አሁንም ህጋዊ ወኪሎቻችን መሆናቸውን እናውጃለን፡፡
• ለ 5 ደቂቃ ‹‹ኢስላም ሠላም!›› በማለት ሰላማዊነታችንን እናረጋግጣለን፡፡
• ለ 5 ደቂቃ ‹‹ጥያቄያው ይመለስ!›› በማለት ጥያቄዎቻችን አሁንም ፍትሃዊ መልስ እንደሚሹ እንገልጻለን፡፡
ሒደቱ ከዚህ ቀደም እንደምናደርጋቸው ተቃውሞዎች ሁሉ በሠላም ተጀምሮ በሠላም እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የተለመዱ ጥንቃቄዎችን ማድረጋችንን እንዳንረሳ እያስታወስን፣ በተለይም ከመንግስት የደሕንት አካላት ሊደርሱ የሚችሉ ትንኮሳዎችን ትኩረት ሰጥተን በመከታተል ማክሸፍና መከላከል ይኖርብናል፡፡
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment