በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
ይህ ጽሑፍ ለእኔም የተጻፈ በመሆኑ አንድ ቀልድ እንደመግቢያ ልናገር፤ አማኑኤል ሆስፒታል ሕመምተኛው ውጭ ይጽፋል፤ ሀኪሙ ይመጣና ‹‹ከበደ፣ እንደምናደርህ?›› ብሎት ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ ሀኪሙ ምን እየጻፍክ ነው? ይልና ይጠይቃል፤ ህመምተኛው ‹‹ደብዳቤ›› ይላል፤ ሀኪሙ ‹‹ለማን ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ፣ ሕመምተኛው ‹‹ለራሴ›› ይላል፤ ሀኪሙ የሕመምተኛውን የውስጥ ስሜት ለማወቅ ጓጉቶ ‹‹ምን ይላል?›› ብሎ ይጠይቃል፤ ሕመምተኛው በመደነቅ ዓይኑን በልጠጥ አድርጎ ‹‹ዶክተር መቼ ተላከና፣ መቼ ደረሰኝና!›› አለው፤ እኔም…
በኢትዮጵያ ውስጥ እያሰቡ ለወደፊት ማቀድ አያዋጣም፤ ለሁሉም ሰው የወደፊቱን የሚወስኑት ወንበሩ ላይ ተቀምጠው ሰይፉን የጨበጡት ብቻ ናቸው፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይህንን አድርጌ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ከዚህ ደረጃ ደርሼ… እያለ በራሱ ሀብት፣ በራሱ ጉልበትና በራሱ እውቀት ሥራውን እያቀነባበረ ከዓመት ወደ ዓመት በእቅድ የሚሄድ የተፈቀደለት ብቻ ነው፤ ፈቃዱም ቢሆን ለአንድ ዓመት የተሰጠው በሌላው ዓመት ይሰረዝ ይሆናል፤ ለባል የተፈቀደው ለሚስት አይሠራም ይሆናል፤ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ አንድ ሰውም ሆነ አንድ ድርጅት እቅድ እያወጣ እየተሳካለት ከአደገ በራሱ የሚተማመንና በራሱ ኃይል እየተራመደ የሚያድግ ሲሆን ላልተደላደለው ሥልጣን አስፈሪ ይሆናል፤ በቋፍ እንዲኖር የሚገደደው ደካማ ሆኖ በልመናና በመለማመጥ እንዲጎብጥ ስለሚፈለግ ነው፤ አንድ ሰው ራሱን ችሎ ብቅ ሲል በኩርኩም አናቱን እያሉ ማኮማተር ባህል ነው፤ አልፎ አልፎ እንዲህ በኩርኩም ልኩን እንዲያውቅ ካላደረጉት ጎበዙ ጎበዝ እየሆነ ጎበዝ ያፈራል፤ ከርሞ ጥጃ ከመሆን ይወጣል! ከርሞ ጥጃነት በሚፈለግበት ሥርዓት እድገት እንዴት ይመጣል?
ሀሳብን በጋዜጣ ማውጣት አደባባይ መውጣት ነው፤ አደባባይ የሚወጡበት ጉዳይ የግል ሳይሆን የአገርና የሕዝብ ነው፤ መሆን አለበት፤ አደባባይ በወጣው ጉዳይ ላይ በአገርና በህዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ባለቤት ሊሆንበት ይችላል፤ በባለቤትነት ሊተችበት ይችላል፤ በጉዳዩ ላይ የሞቀ ክርክር ቢደረግበት ሁላችንም በብዙ መንገድ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን እስከዛሬ የሚታየው አዲሱ ልምድ ከላይ ባለስልጣኖች እንደልባቸው ይናገራሉ፤ በግድም ይሁን በውድ አብዛኛው ሰው ይሰማቸዋል፤ ባለሥልጣኖቹን በማስተጋባት ቴሌቪዥኑና ራዲዮው ደጋግመው እስቲሰለች ድረስ ያሰማሉ፤ በግድም ይሁን በውድ የባለሥልጣኖቹ ንግግር ለብዙ ሰዎች ጆሮ ይደርሳል፤ ግን ጆሮ የደረሰ ሁሉ ወደልብ መተላለፉን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ በአንጻሩ በግል ጋዜጦች ላይ የሚወጡት የተለዩና የተለያዩ ሀሳቦች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አመራሩን የሚተቹ ናቸው፤ እነዚህን ጋዜጦች የሚያነብቡ በጣም ጥቂቶች ናቸው፣ ጋዜጦቹን የሚያገኙዋቸው በገንዘባቸው እየገዙ በመሆኑ የሰዎችን ቀልብ መሳባቸው ይታወቃል፤ እነዚህን ትችቶች ባለሥልጣኖቹ ጉዳያቸው አድርገው የሚያነቡዋቸው አይመስለኝም፤ የእነሱ ንቀት ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት፣ ማንን ወንድ ብላ! እንዳለው ነው መሰለኝ፤ ባለሥልጣኖቹ ሁለት ጥቅሞችን ያጣሉ፤ አንደኛ የተቺዎቹን ሀሳብ መረዳትና ከራሳቸው ሀሳብ ጋር የማመዛዘን ዕድሉ ያመልጣቸዋል፤ ሁለተኛው ሕዝቡ በነፃነትና ያለምንም ግዴታ ትችቱን በማንበቡ ብቻ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሳያውቁት ይቀራሉ፤ የዚህ ውጤት የአገር ጉዳት ነው፤ እንግዲህ እነሱ የሚናገሩትን ይናገራሉ፤ ሌላውም የሚናገረውን ይናገራል፤ በሁለቱም ወገን የሚነገረው ስለአንድ አገርና ስለአንድ ሕዝብ ነው፤ በሁለቱም በኩል የተያዘው ፈሊጥ ሳያነጋገሩ መናገር ነው፤ ክፉ ሕመም ነው።
የሳያነጋገሩ መናገሩ ፈሊጥ የሚታየው በባለስልጣኖችና በተቺዎቻቸው መሀከል ብቻ አይደለም፤ በተቺዎቹም መሀከል ያው ነው፤ ተቺዎቹም መናገሩን እንጂ እርስበርሳቸው መነጋገሩን ገና የለመዱት አይመስልም፤ እንደታዘብሁት እስካሁን ድረስ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ የሚናገሩት ሁሉ እርስበርሳቸው እምብዛም አይነጋገሩም፤ ይህ ሊሆን የሚችለው እያንዳንዱ በሚናገረው ሁሉም ፍጹም ስምምነት ካላቸው ብቻ ነው፤ ወያኔ/ኢህአዴግም እንደዚህ ያለ ፍፁም ስምምነት ያለው አይመስለኝም፤ ወይም በጋዜጣው ላይ የሚናገሩት ሁሉ ይፈራራሉ ማለት ይሆናል፤ ለመፈራራታቸው ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ ነገር ግን አንዱም ምክንያት ለአገርም፣ ለወገንም፣ ለራስም ጠቃሚ አይመስለኝም፤ እንዲያውም የባለስልጣኖቹን ባሕርይ ወደመውረሱ የሚያስጠጋ ይመስለኛል፤ ይህ እውነት ከሆነ፣ ማለት በእኩልነት መነጋገር የማንችል ከሆነ መጀመሪያ ማድረግ ያለብን እያንዳንዳችን ለየራሳችን ተገንዝበን ካረጋገጥን ራሳችንን የምናስተካክልበትን መንገድ መከተል ግዴታ ይሆንብናል።
የፍትሕ ጋዜጣ የተሟላና የተዋጣለት ነው ባይባልም፣ በጣም ተፈላጊና ብዙ ሰውም የሚያነብበው ነው፤ ሆኖም በማስፈራራት የተካኑ ሎሌዎች አቤ ቶኪቾን ለስደት ከዳረጉት ወዲህ ፍትሕ ትንሽ ደረቅ ብሏል! በሀሳብ፣ በአስተያየትና እውቀትን በማስፋት የሚቀርቡት መጣጥፎች አብዛኛውን ጊዜ ፀሐፊው ከራሱ ጋር ብቻ የሚያወራባቸው መስለው ይታያሉ፤ የአንባቢን አእምሮ የመኮርኮር፣ ክርክር እንዲከፍት የማድረግ ኃይል ያላቸው አይመስሉም፤ ይህ የመጣጥፎቹ ጉድለት አይመስለኝም፤ ጠጥቶ ዝም፣ የጋን ወንድም! የሚባለው ዓይነት አንባቢና ፀሐፊ ነው፤ በጋዜጣው ላይ ብዙ ሰዎች መጣጥፎችን ቢያቀርቡም እርስበርሳቸው ሲነጋገሩ ወይም ሲከራከሩ አይታዩም፤ ይህ የሕመም ምልክት ይመስለኛል፤ አንድ ሰሞን ከአቶ ስብሐት ነጋ ጋር፣ አንድ ሰሞን ከፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ጋር ክርክር ቢጤ ተጀመረና ሁሉም እየሮጠ በየምሽጉ ገብቶ ተቋረጠ፤ በዚያን ጊዜም ቢሆን ክርክሩን ከመሩት ሰዎች ውጭ የገባ አንድ ወይም ሁለት ሰው ብቻ ይመስለኛል።
በተለያዩ መንገዶች ደጋግሜ እንደገለጥሁት በእኩልነት ደረጃ ሆነን ለመነጋገርና ለመከራከር ያቅተናል፤ በየፊናችን ስንናገር ራሳችንን ላይ አውጥተን ሰሚውን ከታች አድርገን መደመጥን እንጂ እኛ በተራችን ሌሎችን ማድመጥ እንዳለብን አናውቅም፤ እኛ ለመናገር የምንደፍረውን ያህል ለተናገርነው መልስ የሚሰጠው ድፍረት እንዲያገኝ አንፈልግም፤ እንዲያውም መልስ ከተሰጠን እናኮርፋለን፤ ከመሳፍንት አገዛዝ የወረስነው ባህል ነው፤ ለዚህ ነው ክርክር የማንጀምረው፣ ቢጀመርም የማይቀጣጠለው።
አሁን ደግሞ ስለኢትዮጵያና ጃፓን፣ ስለአጼ ቴዎድሮስና ስለአንድ የጃፓን ንጉሥ ክርክር እየተካሄደ ነው፤ አዝማሚያው የተለመደውን ባሕርያችንን የያዘ ይመስለኛል፤ አንዱ ስለሁነት ሲናገር አንዱ ስለዓላማ ሉዓላዊነት እየተናገረ፣ አንዱ ስለአጼ ቴዎድሮስ ተግባር ሲናገር፣ ሌላው ስለአጼ ቴዎድሮስ ዓላማ መልስ ቢሰጥ መግባባት አይኖርም፤ ክርክሩን እያሻከረው ነው፤ በበኩሌ ሁለቱ ሰዎች የከፈቱት ክርክር ብዙ ቁም-ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ብዙ ሰዎችን ይስባል የሚል እምነት ነበረኝ፤ አሁን እንደሚታየው ግን ሁለቱ ሰዎች እንደተለመደው እየተናገሩ ነው እንጂ እየተነጋገሩ አይደለም፤ ስለዚህም አንዳንዶቻችን ክርክር ውስጥ ገብተን የታሪክን አስተሳሰብና ታሪክን የማጥናትና የማጽዳት ኃላፊነታችንን ብንወጣ ጠቃሚ ይመስለኛል።
በክርክሩ ውስጥ ብዙ ሰዎች የሚያውቁትን እየያዙ ቢገቡበት ስለቴዎድሮስና ስለዚያ ዘመን ከፍተኛ ትምህርት እናገኝበት ነበር።
No comments:
Post a Comment