Feb 3, 2013

”የመለስ ወራሾች አገሪቷን ወደ ድቅድቅ ጨለማ እየከተቷት ነው” ሲል ጋዜጠኛተመስገን ደሳለኝ ገለጸ


ኢሳት ዜና:-ጋዜጠኛ ተመስገን ይህን ያለው፤  <<የመለስ ራዕይ በ አዲስ ታይምስ መጽሔት ተተገበረ>>በሚል  ርዕስ የአዲስ ታይምስን መዘጋት አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ ነው።
“ምንም ጥርጥር የለውም መለስ ዜናዊ ፍፁም አምባገነን ነበር፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም ከአንድ ክፍለ ጦር በላይ የተለየ ሀሳብን እና ነፃ ሚዲያን  ይፈራ ነበር>> በማለት አስተያዬቱን መስጠት የጀመረው ተመስገን፤ << ወራሾቹም ሀሳቡን በነፃነት የሚገልፅን ከመለስ በባሰ መልኩ ይፈራሉ፡፡ ይህ ፍራቻቸው ወደ ጭፍን አምባገነንነት ስለቀየራቸው መላ ሀገሪቷን ወደ ድቅድቅ ጨለማ እየገፏት ነው፡፡>> ብላል።
አቶ መለስ ከአደባባይ ከተሰወሩ በኋላ በፍትህ ቤተሰቦች የሚመራ ትልቅ ሚዲያ ሲዘጋ ‹‹አዲስ ታይምስ›› ሁለተኛዋ  መሆኗን ያወሳው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ለ‹‹አዲስ ታይምስ›› መዘጋት መንግስት የሰጣቸው ሦስት ምክንያቶችም-የባለቤትነት ድርሻ ከአንዱ ወደ ሌላው ሲዞር በ15 ቀን ውስጥ አላሳወቃችሁም፣ ህትመቱ ሲወጣ ለቤተ-መዛግብት ሁለት ሁለት ኮፒ በነፃ አልሰጣችሁም እና  የገንዘብ ምንጫችሁ አይታወቅም የሚሉ  መሆናቸውን አመልክቷል።
እንደተመስገን ገለፃ የተሰጠው ምክንያት ፈጽሞ ውሸት ነው።
ምክንያቱም  እሱ እንዳለው  የባለቤትነት ድርሻ ሲዞር በጊዜው አሳውቀዋል፣ ህትመቱ ሲወጣም ለቤተ-መዛግብት ሁለት ሁለት ብቻ ሳይሆን  ሳይሆን አምስት አምስት ኮፒ በነፃ የሰጠንበትን ማስረጃ  አቅርበዋል፣ ምንጩ አይታወቅም ለሚለው ደግሞ የመፅሄቱ ኮፒ 35 ሺህ በመሆኑ ምንጩ ህዝባችን(አንባቢያን) መሆናቸውን ብሮድ ካስት አብጠርጥሮ ያውቃል።

ተመስገን አያይዞም፦<<አልተፈጸሙም እንጂ እነዚህ የተጠቀሱት ምክንያቶችስ ተፈፅመው ቢሆን እንኳ አዋጁ የሚለው አስራ አምስት ሺህ ብር ያስቀጣል ነው።ታዲያ መዝጋትን ከየት ያመጡት ህግ ነው? ማንአለብኝነት እና ጉልበተኝነት ካልሆነ በቀር፡፡>>ብሏል።
በነገራችን ላይ ‹‹ብሮድ ካስት›› በሚል ስያሜ የተመሰረተ ተቋም ከቴሌቪዥንና ራዲዮን ውጭ ያልተፈቀደለትን የ‹‹ህትመት ሚዲያ››ንም ጨምሮ መቆጣጠሩ ከበረከት ስምዖን ውጪ ለማንም ግልፅ አይደለም  ያለው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ለቤተ-መፅሀፍት መፅሄት ማስገባትን እና አለማስገባትንም እንዲሁ ከሙያ ብቃት ጋር ያላቸውን ግንኙነት  የሚያውቀው በረከት ብቻ ነው ፡፡>>ብላል።
አክሎም፦<<… አሁን የመለስ ራዕይ ግልፅ ነው፤ አፈናውን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው>> ብሏል ጋዜጠኛ ተመስገን።
“መቼም ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ በስልጣን ላይ ተቀምጦ ምንም ያልፈየደን መሪ፣ ልክ ስልጣን በያዘ ማግስት ህይወቱ እንዳለፈ ሰው ሁሉ፦ ‹‹ራዕይ ነበረው፣ እናስቀጥለዋለን… ጂኒ ቁልቋል ማለቱ በህዝብ ላይ ማላገጥ ነው>>ያለው ተመስገን፤ ለሀገር የሚጠቅም ራዕይ ቢኖረው ኖሮ፣ በስልጣን ላይ ያሳለፋቸው ሃያ አንድ ዓመታት ከበቂ በላይ ነበሩና፡፡>>ብላል።
ሀሳቡን ሲቋጭም፦<<ዋናው ጥያቄ ግን ‹‹ይህ የቀልድ ዘመን ዕድሜው ስንት ነው?›› የሚል ነው፡፡ ስድስት ወር? አንድ ዓመት? ወይስ ሁለት ዓመት? ….በጣም… በጣም በቅርቡ የምናየው ይሆናል….በዓለም አቀፍ መድረክ የተሸነፈበትንም ታላቅ ዜና ጊዜው ሲደርስ እንሰማለን፡፡>>ብላል።

No comments:

Post a Comment