Apr 9, 2013

የወያኔ ዘረኝነት (Apartheid ) በቂሊንጦ እስር ቤት




እንደሚታወቀው ከህወሐት/ኢህአዴግ ሥርዓት መገለጫ ባህሪያት አንዱና
ዋነኛው ዘረኝነት ነው፡፡ ይህ ዘረኛ ሥርዓት ዓላማውን ለማሳካት ሲል
በሀገሪቱ ባሉ ተቋማት በሙሉ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን በህወሐት ካድሬዎች
እንዲያዙ ያደርጋል፡፡ በብዙ ተቋማት ደግሞ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን ከላይ
እስከታች ያለውን ቦታ በእነዚህ የአንድ ብሔር ድርጅት ካድሬዎች
ተይዞ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ተቋም ሆኖ ሳለ የሚመስለው ግን የአንድ
ክልል ተቋም ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ሥር
ያሉት የቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ፣ ሸዋ ሮቢትና የድሬደዋ እስር ቤቶች
ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ እስር ቤቶች የሚፈፀመው ዘረኝነት ተመሳሳይነት
ቢኖረውም በቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች የሚፈፀመው ግን እጅግ የከፋ
ነው፡፡ በሌሎች ያለውን ለጊዜው እንተወውና ለዛሬ በቂሊንጦ እየተፈፀመ ያለውን ላውጋችሁ፡፡

 በቂሊንጦ ከባድ ጥበቃ ማ/ቤት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የክፍል ኃላፊዎች፣ የሦስቱም ዞኖች
ኃላፊዎች ሙሉ በሙሉ የህወሐት ካድሬዎች ሲሆኑ ጥበቃዎች፣ ቤተሰብ አገናኞችና ሌሎችም የሥራ ቦታዎች
ከሞላ ጎደል በእነርሱ የተያዙ ናቸው፡፡ ይህ የቂሊንጦ እስር ቤት በ3 ዞኖች የተከፈለ ነው፡፡
በእነዚህ ዞኖች እየተፈፀመ ያለው የዘረኝነት ተግባር ተመሳሳይ ቢሆንምበዞን ሁለት እየተፈፀመ ያለው ግን
ከሁሉ የከፋ ነው፡፡
በዚህ ዞን ከ15 ዓመት እስከ ሞት ድረስ ያሉ ፍርደኞች የሚታሰሩበትቦታ ነው፡፡
በዚህ ዞን ብዙ የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ፡፡ በግንቦት 7፣ በኦነግ፣
በኦብነግ፣ በአርበኞችና በሌሎች የተከሰሱ እስረኞች ይገኙበታል፡ ፡ ከእነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ጋር
ሰላምታ የተለዋወጠ፣ያወራ፣አብሮ የሄደና ማንኛውንም ማህበራዊ
ግንኙነት የፈጠረ እስረኛ ቢሮ እየተጠራ ዛቻ ፣ማስፈራራትና ድብደባ
ይፈፀምበታል፡፡ በተለይ በግንቦት 7 እና በኦነግ ከተከሰሱ እስረኞች
ጋር የሚቀራረቡ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ቁም ስቃያቸውን ነው
የሚያዩት፡፡ በዞኑ ብዛት ያላቸው ወሬ አቀባዮች ወይም በእስር ቤት ቋንቋ
አስጠጪዎች ያሉበት ቦታ ነው፡፡
እነዚህ ደግሞ የእነርሱ ብሄር አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ ከሌላው በተለየ መልኩ
የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
ክበቡን፣ህብረት ሱቁን እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ በእስር ቤቱ ያልተፈቀዱ
ነገሮች (ሲጋራ፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕፅ ወዘተ...) እንዲያስገቡና እንዲሸጡ
ይመቻችላቸዋል፡፡ የሚያገኙትንም ጥቅም ከኃላፊዎች ጋር ይጋራሉ፡፡
በነፃነት የፈለጉበት ቦታ ሄደው የመምጣት፣ ከተማ ሄደው የመዋልና
ጉዳያቸውን የማስፈፀምና የተለያዩ መብቶች ተሰጧቸዋል፡፡ እነዚህ
አስጠጪዎች የፖለቲካ እስረኞችን በመከታተል ከእነርሱ ጋር የተገናኘን
ማንኛውም እስረኛ እየመዘገቡ ወደ ቢሮ
ያስተላልፋሉ፡፡ባስተላለፉትም መሠረት እየተጠሩ ዘግናኝ ማስፈራሪያና ድብደባ
ይፈፀምባቸዋል፤ በካቴና እጃቸውና እግራቸው እየታሰሩ ለሳምንታትና
ለወራት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በየሳምንቱ በሚደረግ የቤት ውስጥ
ግምገማ ወይም የዞኑ አጠቃላይ ስብሰባ ላይ አሰራራቸውን የሚነቅፍ አስተያየት
የሰጠ እስረኛ “አንተ የግንቦት 7 ወይም ኦነግ ነህ” በማለት የሚያሰቃዩት እስረኛ
ብዙ ነው፡፡ በቅርቡ ያሬድ ሺፈራው የተባለውን እስረኛ ከግንቦት 7 ሰዎች
ጋር ቅርርብ አለህ በማለት በተደጋጋሚ እየጠሩ ሲዝቱበትና ሲያጨናንቁት ከቆዩ
በኋላ አንድ ቀን ጠርተው ነገ በሚኖረው ስብሰባ ላይ “የግንቦት 7 አባል ነኝ፡፡
ይህንን ያንን አድርግ ብለውኝ ነበር” ብለህ ተናገርና እንተውሃለን ሲሉት እሺ
ብሏቸው ወጣ፡፡ በኋላም በስብሰባው ላይ እንዲነሳና እንዲናገር ሲያደርጉት “እኔ
እናቴ ያሬድ ብላ ነው ስም ያወጣችልኝ አሁን ግን እናንተ ግንቦት 7 ብላችሁ
ስም አወጣችሁልኝ” ብሎ ሊቀጥል ሲል አስቆሙት፡፡ በኋላም ከዚያ ዞን
አንስተው እስካሁን የት እንዳደረሱት አይታወቅም፡፡ እንዲሁም አሸናፊ
የተባለ እስረኛ በማንነቱ ብቻ ከቆጠራ በኋላ አስወጥተው ከባድ ድብደባ
ፈጽመውበታል፡፡
በተመሳሳይም ዮናስ አስፋው በተባለው እስረኛ ላይም ከባድ ድብደባ ተፈጽሞበታል፡፡
 እንዲሁምብዛት ያላቸው የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ወከባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ
ከፈጸሙ በኋላ 13ቱን የካቲት 22 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ዝዋይ በመጫን እዚያ
በሚገኘው የጨለማ ቤት እያሰቃዩአቸው ይገኛል፡፡
እነዚህም፡-
1.ስሜነህ ምትኩ
2.አምባቸው ዘሪሁን
3.አንተነህ አምፖሎ
4.ሰይድ ሁሴን
5.ናደው ፍርዴ
6.ካሳሁን አብደላ
7.ዮርዳኖስ ግርማ
8.ደ/አዝማች በየነ
9.አለነ ብላታ
10.ገብሬ ሲሳይ
11.ዮናስ አስፋው ይገኙበታል፡፡
በህገ መንግሠቱ ላይ “ማንኛውም እስረኛ ለቤተሰቡ ቅርብ በሆነ እስር
ቤት እንዲታሰር ይደረጋል“ ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን እነዚህንና ሌሎች
ብዛት ያላቸውን እስረኞች ወደ ዝዋይ የሚጫኑበት ምክንያት ከዘረኝነት
የመነጨ ጥላቻቸው መገለጫ ነው፡፡ እነዚህን እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው
በማራቅ ለማጨናነቅና የሚደርሱባቸውን ተፅዕኖዎች እንዳይታወቁ
(ወደ ሕዝቡ እንዳይደርሱ) ከአዲስ አበባ ማራቁ እንደ መፍትሄ ስለሚወሰድ ነው፡፡
ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ተከሰው በእስር ቤት ከሚማቅቁት ውስጥ፡
1.ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ
2. አሳምነው ፅጌ
ቃሊቲ በሚገኘው የብቻ ማሰሪያ ክፍል ውስጥ 3 ዓመት ከ8 ወራት
ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ ለብዙ ቀናት እጅና እግራቸውን በካቴና አስረውና የቤተሰብ
ግንኙነት ከልክለው ወደ ዝዋይ እስር ቤት ጭነዋቸዋል፡፡
በተጨማሪም በተመሳሳይ ክስ ከተከሰሱት ውስጥ፡-
1.ሌ/ኮ ደምሰው አንተነህ
2. ሌ/ኮ ዓለሙ ጌትነት
3. ሌ/ኮ ሰለሞን አሻግሬ
4. ሻለቃ መኮንን ወርቁ
የተባሉትን የካቲት 22 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ዝዋይ ጭነዋቸዋል፡፡
እዚህ አ/አ በሚገኘው ቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤት ከአንድ ዞን ወደ
ሌላ ዞን እንዲሁም ወደ ጨለማ ቤት እያዘዋወሩ ሲያሰቃዩአቸው የነበረ
ሲሆን በተደጋጋሚ በተለያየ ጊዜ እየጠሩ “በጥይት እንደበድባችኋለን“፣
“የመጀመሪያው ጥይት እናንተ ላይ ነው የምናሳርፈው“ ወ.ዘ.ተ እያሉ
ይዝቱባቸው ነበር፡፡ ይህ ሳያንስ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው በማራቅ
ዝዋይ በሚገኘው ልዩ ቤት አጉረው እያሰቃዩአቸው ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይም
1.አቶ በቀለ ገርባ
2.አቶ ኦልባና ሌሊሳ
የተባሉ የኦፌኮ/መድረክ አመራሮችን ቃሊቲ በሚገኘው የጨለማና ልዩ እስር
ቤት ውስጥ ካሰቃዩ በኋላ ወደ ዝዋይ ጭነው እዚያ ባለው ልዩ እስር ቤት
ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፖለቲካ እስረኞችንና በበማንነታቸው ብቻ
የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን  ወደ ዝዋይ በመጫን ከቤተሰቦቻቸው
በማራቅና በዝዋይም የተለያዩ ጫናዎችን በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡ ከጊዜ ወደ
ጊዜም ይህን ድርጊታቸውን አጠናክረው እየቀጠሉበት ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን
ለነዚህ ተቋማት ማረሚያ ቤት የሚል ስም የሰጧቸው ቢሆንም እውነታው
ግን ከዚህ በፍፁም የተለየ ነው፡፡ አንዳችም የማረምና የማነፅ ተግባር
የሚካሄዱባቸው ተቋማት አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከተቆራኛቸው የዘረኝነት አባዜ
በመነጨ እስረኞችን በማንነታቸውና በፖለቲካ አቋማቸው በእስር ቆይታቸው
ማጨናነቅ፣ ማዋከብ፣ አየጠሩ ማስፈራራት፣ ቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና
መፍጠር፣ ከቤተሰቦቻቸው በማራቅ ግንኙነታቸውን ማዳከምና ከተቻለም
ማቆራረጥ እንደ ፖሊሲ ይዘው እየተገበሩት ይገኛል፡፡
ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ የታሰሩት እስረኞች ከቤተሰብ ጋር በሚገናኙበት
ወቅት የህወሓት አባላት የሆኑ ፖሊሶች ብቻ ተመርጠው ከጎናቸው ስለሚቆሙና
ለደቂቃም ያህል ስለማይለዩ ቤተሰባዊ ሚስጥሮችን(ጉዳዮችን) እንኳን
ለማውራት አስቸጋሪ ነው፡፡
በጭውውት ውስጥ መንግስትን ይነካል የሚሉት አረፍተ ነገር ከሰሙ
ዛቻውና ማስፈራሪያው ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በእስር ቤቱ
የሚሰጡ ማንኛውንም አገልግሎቶች (ዝውውር፣አመክሮ፣ይቅርታ፣የፍ/ቤት
ጉዳዮች፣ልዩ ልዩ ወ.ዘ.ተ) ለማግኘት ማንነትህ ወሳኝ ነው፡፡ ወይ የነሱ ሰው
መሆን አለብህ ካልሆነ ደግሞ ገንዘብ በደንብ ሊኖርህ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ እስር ቤት ውስጥ ዘግናኝ የሆነ የሰብዓዊ ጥሰት ያለበት፣
በማንነቱ ብቻ እስረኛው ቁም ሥቃዩን የሚያይበት ቦታ ነው፡፡ ሰውን ማሰር ብቻ
ሳይሆን አሥረውም ካላሰቃዩ ካላንገላቱ እርካታ የማይሰማቸው ዘረኞች የበዙበት
እስር ቤት ነው፡፡ ዓላማቸው ከእነርሱ ውጭ ያሉ ሕዝቦችን በእስር በማሰቃየት ቢቻል
መግደል ካልሆነም በቁሙ መግደል ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ የሚቆጣጠራቸው
አካል ያለመኖሩ ነው፡፡ ለስሙ ከፌ/ ማ/ቤ ኮሚሽን እና መንግስታዊ
ያልሆኑ ድርጅቶች ነን ባዮች ነገር ግን ከራሱ ከመንግስት በላይ ለመንግስት
የሚቆረቆሩ ካድሬዎች የሆኑ የእነ ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ አይነት
ድርጅቶች ለተለያየ ጊዜ እስር ቤቱን ቢጎበኙም ከተቆርቋሪነታቸው የተነሳ
እስር ቤቱን አድንቀውና አወድሰው ከመሄድ ባለፈ እውነታውን ማወቅም
ሆነ ማሳወቅ አይፈልጉም፡፡
ችግራችንን የሚያይልንና መፍትሄ የሚሰጠን አካል ባለማግኘታችን ይኸው
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስቃያችንን እንዲያውቅልን ስንል እውታውን
በጥቂቱም ቢሆን ልናሳውቅ ተገደናል፡፡
ፍኖተ ነጻነት

No comments:

Post a Comment