Apr 7, 2013
ትግል...ሽንፈት፤... ድል፤ ሽንፈት...
(ከተመስገን ደሳለኝ )
ከምሽቱ አንድ ሰአት አልፏል፤ የእጅ ስልኬ ደጋግሞ ቢጮኽም ትኩረት አልሰጠሁትም፡፡ ከጥቂት ሰከንዶች
ፋታ በኋላ የቢሮዬ ስልክ ጮኸ፤ አነሳሁት፡፡ ለካስ እንዲህ በአንዱ አልመልስ ስላት፣ በሌላው እያፈራረቀች
የምትደውለው ዕድሜዋ ወደ ሰባ እየተጠጋ ያለው አሮጊቷ እናቴ ኖራለች፡-
‹‹አቤት! እናቴ››
‹‹ለምንድነው የዚህን ያህል ስልኩ ሲጮኽ የማትመልሰው?›› ቆጣ ብላ ጠየቀችኝ፡፡
‹‹አስቸኳይ ስራ ላይ ስለነበርኩ ነው››
‹‹ኤዲያ! አንተ ደግሞ ሁል ጊዜ ጠብ ለማይል ነገር፣ ችክ ማለት ትወዳለህ››
…በእርግጥ እናቴ እውነቷን ነው! ችክ ያልኩ ቸካካ ነገር ሳልሆን አልቀርም ፡፡
‹‹ልዕልና›› ጋዜጣ ታግዳለች፤ እንደ‹‹ፍትህ›› እና ‹‹አዲስ ታይምስ›› ሁሉ የስርዓቱ የአፈና ሰለባ ሆናለች፤ የሚገርመው ግን መታገዷ
አይደለም፣ የታገደችበት መንገድ እንጂ፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደገለፅኩት አቶ መለስን የተኩት ሰዎች ከእረሱም የባሱ ጭፍን
አምባገነኖች ናቸው፡፡ ማንንም አይፈሩም፡፡ እግዚአብሄርንም ቢሆን ‹‹በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካልተጠመቅህ አምላክ ሆነ እንድትቀጥል
አንፈቅድልህም›› ከማለት አይመለሱም፡፡
የሆነ ሆኖ የስርዓቱ አይን አውጣነት የደረሰበትን ደረጃ ለመገንዘብ የሚከተለውን በጥሞና አንብቡ፡፡
የ‹‹ልዕልና›› አሳታሚ ድርጅት በሁለት ወዳጆቼ ስም ከተገዛ በኋላ፣ ስም ከመዞሩ በፊት ስርዓቱን ወጥመድ ውስጥ የሚከት ስልት
(አይን ያወጣ አምባገነን ባህሪውን ወዳጆቹ ሳይቀር ይኮንኑት ዘንድ ወደ አደባባይ የሚያወጣ) ተነደፈ፡፡ በስልቱ መሰረትም ከቀድሞ
የድርጅቱ ባለቤቶች ጋር አንድ ስምምነት ተደረገ፡፡ ይኸውም እኔ የሚጠበቅብኝን የአክሲዎን ሽያጭ ክፍያ አስቀድሜ ብከፍልም፤ ምንም
አይነት የስም ዝውውር ሳይደረግ ባለቤትነቱ በእነርሱ ስም ሆኖ እንዲቀጥል ተስማማን፡፡ በዚሁ መንገድ ስራው ተጀመረ፡፡ ለአፈና
ሲንደረደር ግራና ቀኝ ለማያጣራው መንግስት ደግሞ እንዲህ የሚል የ‹‹ተጋገረ›› መረጃ በጋዜጣችን ላይ አስተላለፍን ፡-
‹‹በህጋዊ መንገድ የስም ዝውውር አድርገን ነው ስራ የጀመርነው፡፡››
እነሆ ይህ በሆነ በአስራ ሶስተኛው ቀን (13/07/05) ብሮድካስት ውስጥ ያሉ ዞምቢዎች
‹‹ድርጅቱ ለሌላ ሶስተኛ ወገን በህገ-ወጥ መንገድ የስም ዝውውር አስተላልፏል›› ሲሉ ድምፃቸውን አሰሙ፡፡
መቼ ተላለፈ? የተላለፈላቸው ሰዎችስ ስም ማን ይባላል? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ብሮድካስትን አያሳስቡትም፤ ያውም አንድ
የሚዲያ ተቋምን ያህል ነገር ሲዘጋ (በነገራችን ላይ የስም ዝውውር የተደረገው ብሮድካስት ደብዳቤውን ከፃፈ ከአምስት ቀን በኋላ
/በ18/07/05/) ነው፡፡
ለብሮድካስት ህገ-ወጥ እግድ ጋዜጣዋ መገዛት እንደሌለባት አዘጋጆቹ ስምምነት ላይ ስለደርሰን በ20/07/05 ታተመች፡፡ ሆኖም ሌላው
ዞምቢ ድምፁን አሰማ-ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፡፡ ይህ መስሪያ ቤት ያለምንም ማጣራት ጋዜጣዋ በወጣችበት ዕለት (20/07/05)
ንግድ ፍቃዳችንን መሰረዙን የሚገልፅ ደብዳቤ ላከልን፡፡ በእጅጉ የሚገርመው ሁለቱም ‹‹ተቋምዎች›› ህገ-ወጥነታችንን የገለፁት
ተመሳሳይ የአዋጅ ቁጥር በመጥቀስ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ከመገናኛ እና ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/200 ከሚፈቅደው ውጪ…››
በማለት፡፡ …ይህ ምን ማለት ነው? በዚህ አዋጅ ውስጥ በርካታ አንቀፆች ተደንግገዋል፡፡ ስለአታሚ፣ አሳታሚ፣ ዋና አዘጋጅ፣ መረጃ
ተመስገን ደሳለኝየማግኘት መብት፣ የማሳተምና የመደራጀት ነፃነት፣ ስለአከፋፋዮች… አጅግ ብዙ ጉዳዮችን ያካትታል፡፡ ታዲያ እኛ የታገድነው ከእነዚህ
ሁሉ አንቀፆች የትኛውን ተላልፈን ነው? …ቢያንስ መንግስት የሚመስል ነገር ወይም ‹‹መንግስት ነኝ›› የሚል ካለ ጥፋታችንና
የተላለፍነውን የአዋጁን አንቀፅ ቢነግረን ሌላው ቢቀር ከስሜት መጎዳት እንድን ነበር፡፡ ነገር ግትን ዞምቢዎቹ እንደከዚህ ቀደሙ አንቀፅ
በመጥቀስ ማስመሰል እንኳን አልቻሉም፡፡ በደፈናው የአዋጅ ቁጥር ጠቀሱና አረፉት፡፡
…አሁን ሀገራችን አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በአደባባይ ህግ ለመጣስና የፈቀዳቸውን ለማድረግ ትንሽ እንኳ በማያመነቱ አደገኛ ሰዎች
መዳፍ ስር ወድቃለች፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ተናገሪዎች ለዓመታት ከሰፈሩበት ቀዬ በኃይል መፈናቀላቸው ቀጥሏል፡፡ በእርግጥ በመለስ
ዘመንም ቢሆን መፈናቀሉ ነበር፡፡ ኧረ እንዲያውም ‹‹ደን እየጨፈጨፉ ስላስቸገሩ ነው›› ብሎ ሁሉ አላግጦባቸዋል፡፡
የአማራው ‹‹ወኪል›› ነኝ የሚለው ብአዴንም ቢሆን ከታምራት ላይኔ ክፉ መንፈስ ገና ነፃ አልወጣም፡፡ ታምራት ላይኔ በስልጣን ዘመኑ
በርካታ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ተወላጆች በየአካባቢው ሞትና መፈናቀል እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲነገረው ‹‹እኛ ከክልል ሶስት ውጪ
ስለሚኖሩ አማሮች አያገባንም፡፡ ምክንያቱም በነፍጠኝነት ለወረራ የሄዱ ናቸው›› ብሎ ተሳለቆ ነበር፡፡ ዛሬ እነኦቦ አዲሱ ለገሰም ከዚህ
አቋማቸው አልተቀየሩም፡፡ ተወልደ ወ/ማርያም በክፍፍሉ ወቅት ብአዴኖች ከመለስ ጎን በመቆማቸው ተበሳጭቶ ‹‹የፖለቲካ ደሀ ናችሁ››
ሲል መተቸቱ በረከት ስምዖን ዛሬም የገባው አይመስለኝም፡፡
የማፈናቀሉ መሀንዲስ ህወሓትም ቢሆን ይህ መንገድ ብዙ ርቀት የማያስኬድ ስለመሆኑ ከሃያ ዓመት በኋላም አልተገለፀለትም፡፡ ለዚህም
ይመስለኛል ከፋፍሎ በመግዛት እና በማዳከም ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በመከተል ጉልበቱን እያዛለ ያለው፡፡ በነገራችን ላይ መረሳት
የሌለበት ቁም-ነገር የጥፋት ስራው ተጠያቂ ህወሓት እንጂ ‹‹እወክለዋለው›› የሚለው የትግራይ ህዝብ አለመሆኑ ነው፡፡ አማራ-
በብአዴን፣ ኦሮሞ-በኦህዴድ እንደማይገለፀው ሁሉ፣ የትግራይ ህዝብም በህወሓት ይገለፃል የሚል የጨዋታ ህግ የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች
ለስልጣናቸው እስከጠቀመ ድረስ የማይፈፅሙት ህገ-ወጥ ድርጊት አለመኖሩ ላይ መስማማት የሚኖርብን ይመስለኛል፤ የማይፈፅሙት
ጭካኔም የለም፡፡ ይህንን የሚያሳይ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ታሪኩ የቀድሞ የደህንነት ሹም የነበረው ክንፈ ገ/መድህንን በጥይት ደብድቦ
ስለገደለው ሻለቃ ፀሀዬን የሚመለከት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሟችም ገዳይም ትግርኛ ተናጋሪዎች ቢሆኑም፣ ሻለቃው ወንጀሉን ከፈፀመ
በኋላ ለብዙ ችግር ተዳርጎ ነበር፣ ያውም ከነቤተሰቡ፡፡ መጀመሪያ ባለቤቱን ከምትሰራበት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አባረሯት፡፡ እግር
በእግርም እየተከታተሉ በኪራይ ከምትኖርበት ቤት አፈናቀሏት (በጊዜው እስክንድር ነጋ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግላት ነበር) ሻለቃውም
ለስድስት ዓመት ያህል በጨለማ ቤት ውስጥ በመታሰሩ የአይን ብርሃኑ በከፍተኛ ደረጃ ተጎዳ፡፡ ፍርድ ቤት ሲቀርብ እንዴት ለመራመድ
ይቸገር እንደነበረ አስተውለናል፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ያጠፋ ሰው በህግ አይጠየቅ አይደለም፤ ከህግ ውጪ ስለምን የበቀል ሰለባ ይሆናል
ነው? ሰዎቹ ከየትኛውም ብሄር ተወለዱ በጠላትነት ከመዘገቧችሁ ለጭካኔያቸው ወደር የለውም፡፡
የሆነው ሆኖ ስርዓቱ ገደብ ላጣው ጭካኔው ‹‹ብሄር›› የተሰኘ አጥር የለውም ያስባለኝ በሻለቃው ህይወት መጨረሻ የተፈፀመው ድርጊት
ነውና እሱን ልንገራችሁ፡፡
ዕለቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ‹‹ፍልሰታ›› እያሉ የሚጠሩት የአስራ ስድስት ቀን ፆም ዋዜማ ነው-ሐምሌ 30ቀን፡፡
ሻለቃው ይህች ቀን የመጨረሻዋ መሆኗን ሊያውቅ የሚችልበት አገጣሚ አልነበረምና ጥብቅ ሀይማኖተኛ በመሆኑ ለፆሙ የመንፍስና የቁስ
ዝግጅቱን አጠናቆ በደስታ እየጠበቀ ነው፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡
በፃሃፊ ብዕር ልተርክላችሁ፡፡
…ወቅቱ ክረምት ቢሆንም ፀሀይ ህቡዕ የገባች እስኪመስል ድረስ ዝናብን አግደው የያዙ የሰማይ መስኮቶች ከንጋት ጀምረው ላንቃቸውን
ከፍተው ምድሪቱን እያረሰረሷት ነው፡፡ ቀኑ ተገባዶ አስር ሰዓት ላይ ደርሷል፡፡ አብዛኛው እስረኛ በየክፍሉ ከቷል፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ
ውሽንፍሩን ተከትሎ ያረበበውን ቅዝቃዜ ይከላከልልናል በሚል ካፍቴሪያ ውስጥ ቁጭ ብለው ሻይና ቡና ደጋግመው ያዛሉ፡፡
አንዲት የደህንነት መኪና ሾፌሩን ጨምሮ አራት ሰዎች አሳፍራ ወደማረሚያ ቤቱ አስተዳደር መግባቷን ማንም አላስተዋለም፡፡ መኪናዋ
የኃላፊውን ቢሮ ታካ ስትቆም የቡድኑ መሪ ቀልጠፍ ብሎ ወርዶ በቀጥታ ከፊቱ ወደአለው ቢሮ በመግባት፣ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ጋር
ለጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ ከአደረገ በኋላ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ያልተለመደ ትዕዛዝ ተላለፈ፤ ሁሉም እስረኛ ወደ ክፍሉ እንዲገባ የሚል፡፡እስረኞቹ በሙሉ ወደ ክፍላቸው መግባታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ቀኑን እየጠበቀ የነበረው ሻለቃ ፀሀዬ
ከክፍሉ ወጥቶ ከደህንነት ቢሮ ወደመጣችው መኪና ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፡፡ መኪናዋም በመጣችበት ፍጥነት የመልስ ጉዞ አደረገች፡፡
ይህ ሁሉ ነገር ተካሄዶ ያለቀው በአስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ነበር፡፡
...ጎዳናው ላይ አልፎ አልፎ እየተንገዳገደ ከሚያዘግም ሰካራም እና ከሚያላዝኑ የመንገድ ዳር ውሾች በቀር አንዳች እንቅስቃሴ አይታይም፤
ጭር ብሏል፡፡ የክረምቱ ቅዝቃዜ በድቅድቅ ጨለማ ቁጥጥር ስር ከዋለው ሌሊት ጋር ተቀላቅሎ በእጅጉ ያስፈራል፡፡ የሻለቃው ባለቤት
ወ/ሮ አምሳለ የመኖሪያ ቤቷ በር ሲንኳኳ ከሶስት ልጆቿ ጋር በእንቅልፍ ዓለም ውስጥ ነበረች፡፡ ማንኳኳቱ ሳይቋረጥ ለደቂቃዎች
በመቀጠሉ ድንገት ካሰጠማት እንቅልፍ አባነናት፡፡ እናም በሩን ከፈተች፡፡ ከዚህ ቀደም አይታቸው የማታውቃቸው ሁለት ሰዎች ቆመዋል፡
፡ ደነገጠች፡፡
‹‹ምንድን ነው? ምን ፈልጋችሁ ነው?›› አከታትላ ጠየቀች፡፡
‹‹ፖሊሶች ነን፣ ሻለቃ ፀሀዬ በጣም ስለታመመ አምሳለን ጥሩልኝ ስላለን ነው የመጣነው›› ሲል መለሰ አንደኛው ሰውዬ፡፡
‹‹ቀን ስንቅ ስወስድለት ደህና አልነበረ እንዴ? አሁን ምን ተፈጠረ?››
‹‹ድንገት ነው የታመመው፤ ልታዪው የምትፈልጊ ከሆነ ቶሎ እንሂድ?›› አለና አጣደፋት በሌሊት ከሰው ደጅ ቆሞ መመላለሱ
ያልተመቸው ሁለተኛው ሰው፡፡ ወ/ሮ አምሳለም ስጋት እንደሞላት ሰዎቹን አሳፍራ በመጣችው መኪና ውስጥ ገብች፡፡ ሆኖም መኪናዋ
ወደመጣችበት መመለሰ ስትጀምር መንገዱ ወደቃሊቲ የሚወስደው እንዳልሆነ ተረዳች፡፡ ከሃያ ደቂቃ ጉዞ በኋላም መኪናዋ አንድ ግቢ
ውስጥ ገብታ ቆመች፡፡ ሁሉም ወረዱ፡፡
‹‹የታለ ባለቤቴ?›› አምሳለ ጠየቀች፣
‹‹ያው! እዛ ክፍል ውስጥ ግቢ፣ እየጠበቀሽ ነው›› አላት አንደኛው ሰው፣ በሩ ወደተከፈተ ክፍል በእጁ እያመለከተ፡፡
እንደተባለችው ገርበብ የተደረገውን በር ሙሉ በሙሉ ከፍታ ገባች፡፡ …ክፍሉ ወለል መሀል ላይ ሻለቃው በጥይት ተበሳስቶ በጀርባው
ተዘርሯል፡፡ …ያልጠበቀችውን ክስተት የተመለከተችው የሻለቃው ባለቤት እንደሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆነች፡፡ …የዚህን ያህል ነው
የህወሓት ጭካኔ፡፡ ከመስመሩ ካፈነገጣችሁ ትግሬ ሆናችሁ አማራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ እናም ማቆሚያ ላጣው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች
መፈናቀልም ብቸኛው ተጠያቂ ህወሓት እንጂ ‹‹ወከልኩት›› የሚለው ህዝብ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ አመለካከት የተሳሳተ
ከመሆኑም በላይ የማይታረም አደጋ ያስከትላል፡፡
የሆነ ሆኖ እንዲህ አይነቱን አጓጉል ችግር ፈጣሪ ድርጊት ሁላችንም በጋራ ለማስቆም መሰለፍ አለብን፡፡ በይበልጥ ደግሞ ከሀገሪቱ የተለያዩ
አካባባዎች መጥታችሁ፣ የተለያየ አካባቢ ሰፍራችሁ ሀብት እያፈራችሁ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ይህ አይነቱ ማፈናቀል ባስቸኳይ
ይቆም ዘንድ ነግ በእኔ ብላችሁ ስርዓቱ ላይ ጫና ማሳደር አለባችሁ፡፡ ቀጣዩ ተረኛ እናንተ ላለመሆናችሁ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
የስርዓቱ ደጋፊዎችም ሆናችሁ ልሂቃኖች፣ በአሰልቺ ዜማ ጠዋትና ማታ ‹‹አባይ፣ አባይ…›› የምትሉ አርቲስቶች ከምንም በፊት ስለንፁሀን
እምባ መገደብ ልትናገሩ ይገባል፡፡ አገዛዙ የዱርዬ ባህሪውን ይገድብ ዘንድ ስትዘምሩ መስማት እንፈልጋለን፡፡ … እስቲ ዙሪያችንን
እንመልከት፤ ትላንት ከኋላችው ቆምን ነፃ ያወጣናቸው ሀገራት ዛሬ የብሄር ፖለቲካን ለእኛ ጥለውልን ርቀው ሄደዋል፡፡ በዘላቂነት አብሮን
ለማይቆይና ጠብ ለማይል ነገር እንማስናለን፡፡ እናቴም እንዲሁ ነበር ያለችኝ ‹‹ችክ አትበል! ጠብ ለማይል ነገር!›› ሆኖም ግሳጼዋን ችላ
ብዬ ለምን እንደደወለችልኝ ጠየኳት፡፡
‹‹ትላንት ለምን ወደ ቤት አልመጣህም?››
‹‹ምነው ፈልገሽኝ ነበር እንዴ?››
‹‹አዎ! የአባትህ 13ኛ ሙት ዓመት ነበር እኮ›› …ደነገጥኩ፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል? ግና በለሆሳስ ‹‹አባቴ ሆይ ነፍስህ በአፀደ ገነት
እንዳለች አምናለሁ!›› ስል እናቴ ማነብነቤን ሰምታኝ ኖሮ ምን እንዳልኩ ጠየቀችኝ፡፡‹‹አይ! ምንም አላልኩም››
‹‹ለማንኛውም ዛሬ ወደ ቤት እንድትመጣ?››
‹‹እናቴ! ቢሮ ስለማመሽ ልመጣ አልችልም፤ ራሴ ቤት ነው የማድረው››
‹‹እረስተከዋል እንዴ! ዛሬ እኮ መጋቢት ሀያ ሰባት ነው››
‹‹እና ታዲያ?››
‹‹የተወለድክበት ቀን ነዋ!›› …ሌላ የተረሳ ጉዳይ፡፡ ይህ ሳምንት ድብልቅልቅ ያለ ነው፡፡ የአባቴ 13ኛ ሙት ዓመት፣ የልደት ቀን፣ ሽልማት
(በነገራችን ላይ ‹‹ኢትዮቲዩብ›› ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስከበር አስተዋፆ አድርገሀል በማለት የሸለመው እኔን ብቻ ሳይሆን
ባልደረቦቼንና አንባብያንንም ጭምር በመሆኑ በሁሉም ስም እንዲህ ማመስገኑ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለው፡- ‹‹እንዳከበራችሁን
እግዚአብሄር ያክብርልን፤ መጪውም ከዚህ የበለጠ ስራ የምትሰሩበት የስኬት ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ እመኛለሁ››)
ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ከማሳረጌ በፊት መልዕክቴን ላስተላልፍ፡-
አሁንም ትግሉ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ልዕልና›› ብትዘጋም ሌላ ይከፈታል፡፡ ትግል… ሽንፈት፤ …ድል፤ እንደገና መሸነፍ… ተስፋ አንቆረጥም፤ ገና
ወደፊት እንቀጥላለን፤ በዘመናችን ብዙ ነገር አይተናል፤ ርዕዮተ-ዓለም ሲሸነፍ ተመልከተናል፤ ስርዓት ድል ሲመታ አይተናል፤ ህዝብ እንደ
ህዝብ ሲሸነፍ ግን ማንም ተመልክቶ አያውቅም፡፡ እናም እኔ ጋዜጠኛ ነኝ ‹‹ለዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ፀልዩ›› ብዬ ልመክር
አልችልም፡፡ ነገር ግን እልፍ ሆነን እንዘምር ዘንድ ድምፄን ከፍ አድርጌ እጠይቃለሁ፡-
አትነሳም ወይ? አትነሳም ወይ?
ይሄ ባንዲራ የአንተ አይደለም ወይ?
…ኢ-ፍታሀዊነትን እንዋጋለን፣ የከፋፍለህ ግዛን አስተዳደር እንቀይራለን፡፡ በሩንም በሰላም ይከፍቱልን ዘንድ ደጋግመን እናንኳኳለን፤
ካልከፈቱልንም ገንጥለን እንገባለን፡፡ ከዛ በኋላም ሀገራችንን የራሳችን እናደርጋለን! ያዘኑትም ይስቃሉ፤ የታሰሩትም ይፈታሉ፤
የተሰደዱትም ይመለሳሉ፤ የወጡትም ይወርዳሉ፡፡
(መጋቢት 27/2005 ዓ.ም እኩለ ሌሊት)
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
April 6, 2013
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment