Apr 23, 2013

በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ኦሮሞ ዞን ከተፈጠረለት ለምን የራያና አዘቦ ዞን በትግራይ ውስጥ አልተፈጠረም


ቡልቻ ደመቅሣ 22 /04/2013
የኦሮሞ የፖለቲካ ጉዳይ በየዘመኑ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ ሲመሏ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነው ከአፄ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት፣ የኢትዮጵያ ነገስታት ኦሮሞን ለማሸነፍ ስላልቻሉ በየጊዜው እየተጋጩ እንደምንም አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ፋዘር አልሜዳ የሚባለው የፖርቱጋል ቄስ በዚህ ጉዳይ በሰፊው ጽፏል፡፡ ነገር ግን አብሮነታቸው እንደ ገዥና ተገዥ አልነበረም፡፡ ከአጼ ልብነድንግል ጀምረው እስከ ንጉስ ሳህለ ስላሤ የነበሩት አፄዎች ሁሉ ኦሮሞን ለማሸነፍ እና ለመግዛት ያላደሩጉት ጥረት አልነበረም፡፡
ኦሮሞንና ሀገሩን አሸንፈው ለማስገበር የቻሉት አፄ ሚኒሊክ ብቻ ነበሩ፡፡ እሳቸውም ኦሮሞን ለማሸነፍ የቻሉት ከኦሮሞዎች ቀደም ብለው ከፈረንጆች የጦር መሳሪያ ስላገኙ ነበር፡፡ መሣሪያ ያገኙበትም ምክንያት ከእሳቸው ቀድሞ የነበሩት አንዳንድ አፄዎች ለአውሮፓ መንግስታት “ኢትዮጵያ ብቻዋን ክርስቲያን ሆና በአፍሪካ ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች” ብለው የአውሮፓውያን መንግሥታትን ስለለመኑና ስላስረዱ የጦር መሣሪያ ማግኘት ቻሉ፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ሚኒሊክ ሸዋን በሙሉ ለመቆጣጠር ሲነቃነቁ ደብረብርሃን አጠገብ በምትገኘው አብደላ በምትባል መንደር ውስጥ ከጎበና ዳጬ ጋር ተገናኙ፡፡ ጎበና ዳጬም በዚያን ጊዜ በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የሉባና የነበዙ አባ ደክር ወዳጅ የነበሩ፡፡ ከአፄ ሚኒሊክ ለጎበና ዳጬ አንድ ነገር ተናገሩ፡፡ “ወደታች ወደደቡብ እንሂድ፡፡ ወደአቢቹ፣ ገላን፣ ጉለሌ፣ አርሲ አብረን እንዝመት፡፡ አንተ የጋላ ንጉስ ትሆናለህ፣ እኔ የኢትዮጵያ ንጉስ እሆናለሁ ተከተለኝ” አሏቸው፡፡ እንደተባባሉትም ወደታች ወደደቡብ መጥተው የኦሮሞን ጎሣዎች መውጋት ጀምሩ፡፡ ጎበናም ራስ ተባሉ፡፡ ነገር ግን አፄ ሚኒሊክ ለጎበና የገቡትን ቃል ሳይጠብቁ ቀሩ፡፡ ጎበናም ብዙ ጊዜ ከተዋጉ በኋላ እየተዳከሙ ሄዱ፡፡ ነገር ግን የሸዋን፣ የወለጋን (በሰላም የገቡ) እና የከፋን (ከፋም በሰላም ገባ) ኦሮሞዎች ካሸነፉ በኋላ አፄ ሚኒሊክ እራሳቸው ጦርነቱን መምራት ጀመሩ፡፡ ራስ ጎበና በቀየሱት መንገድ ሄደው ሌሎች ያልተያዙትን ሀገሮች ያዙ፡፡ ለምሳሌ ሀረርን፣ ውጋዴንን፣ ሱማሌን፣ ቦረናን ያቀኑት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ (እኔ አቀኑ እላለሁ አንዳንድ ሰዎች ግን “ኮሎናይዝ” አደረጉ ነው የሚሉት፡፡ እውነቱን ለታሪክ ተንታኞች እንተዋለን፡፡) ይህ ታሪክ አፈታሪክ ነው፡፡ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት አፈታሪክ የተፃፈ ታሪክ ያህል ዋጋ አለው፡፡ አሁን ልክ አይደለም ብሎ መከራከር ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ሁሉ ይህን ያምናሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የታሪኩን እርግጠኛነት የሚያረጋግጠው የራስ ጎበና ሕመም ነው፡፡ (በብስጭት እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚናገሩ የእሳቸው ተወላጆች አሉ፡፡)
እኔ እንደብዙ ወገኖቼ ጎበናን አላብጠለጥልም ሰው ስራ መስራት አለበት፡፡ ቤተሰቡን የሚደግፈው የሰራ እንደሆነ ነው፡፡ አለስራ መኖር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ራስ ጎበና ስራ አግኝተው ቢሰሩም የፈለጉት ሳይሆን ቀርቶ ታመው ሞቱ፡፡ ይሄ ማንኛቸውም መሪ የሚያረገው ነገር ነው፡፡ አንዳንዱ አላደርግም ብሎ ይሞታል፡፡ ግን ብዙ ሰው ሞትን አይመርጥም፡፡ አፄ ሚኒሊክ ጎበናንም ባያገኙ ማሸነፋቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ከአውሮፓውያን ብዙ የጦር መሣሪያ አግኝተዋል፡፡
ራስ ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ያደረጉት ስምምነት ለጊዜው ለኦሮሞ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚሄድ መስሎ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አፄ ሚኒሊክ ኦሮሞን የገዙበት የባሪያ አገዛዝ ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንዲሄዱ አደረጋቸው፡፡ ኦሮሞ ደርግ ላይ ምንም ተስፋ ስላልነበረው የጀነራል ተፈሪ ባንቴ ፕሬዝዳንት መሆን ምንም አልመሰለውም፡፡ ዶክተር ነጋሶ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ለኦሮሞ የተሻለ መስሎ አልታየውም፡፡ ዶክተር ነጋሶም እራሳቸው በስርዓቱ ባለማመን ረግጠው ወጡ፡፡
ከዚያ በኋላ የአፄ ሚኒሊክን የጦር ኃይል መመከት ያልቻለው ኦሮሞ፣ ገባርነትን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ሆኖም ግን አፄ ሚኒሊክ ከዚያ በፊት ኦሮሞ ይዞት የነበረውን መሬት ማስለቀቅ ስላልቻሉ ኦሮሞ በአፄ ልብነድንግል ጊዜ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይዞት የነበረውን መሬት እንደያዘ ቀረ፡፡ እዚህ ላይ እናስታውስ፡፡ የወሎ አሮሞና ትግራይ ውስጥ ያሉት ራያና አዘቦ ኦሮምኛ ቋንቋቸውን እየረሱ አማርኛ ወይም ትግሪኛ መናገር ጀምረዋል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ኦሮሞ ዞን ከተፈጠረለት ለምን የራያና አዘቦ ዞን በትግራይ ውስጥ አልተፈጠረም፡፡ ይኼ የሚያሳየው ሕገ መንግስቱ በተፃፈበት ጊዜ (በ1986 ዓ.ም) ህወሓት የነበረውን ፍጹም የበላይነት ነው፡፡
ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ 35 በመቶ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ሕዝቡም ወደ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ይገመታል፡፡ የኦሮሞ መሬት ስፋቱ 387,000 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ማለትም ጀርመንን ያክላል ማለት ነው፡፡
Read more at  http://www.fetehe.com

No comments:

Post a Comment