ከጥቂት ቀናት በፊት ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ አንድ አነጋጋሪ፣ አከራካሪና አመራማሪ መጽሐፍ አውጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ሃሳባቸውን በአደባባይ፣ ሕዝብ በሚረዳው መንገድና ቋንቋ ከሚገልጡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ልሂቃን አንዱ ናቸው፡፡ በሦስት የመንግሥት ሥርዓት ፕሮፌሰር መስፍን ሃሳባቸውን ሲገልጡ፣ ሲጽፉ፣ ሲከራከሩና፣ መልካም የመሰላቸውን ሁሉ ለሕዝብ ሲያቀርቡና ሲሞግቱ የኖሩ የአደባባይ ምሁር ናቸው፡፡
አብዛኞቹ ልሂቃን በጆርናሎችና በዐውደ ጥናቶች ላይ ከሚያቀርቧቸው ጽሑፎች ባለፈ ለሀገር ሕዝብ ዕውቀታቸውን በሀገር ቋንቋ አያቀርቡም፡፡ በዚህ የተነሣም ታዋቂነታቸውም ሆነ ተሰሚነታቸው በዚያው አካዳሚያዊ በሆነው ክልል ብቻ የታጠረ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን በአማርኛችን ከጣት ቁጥር በላይ የሆኑ መጻሕፍትን አቅርበዋል፡፡ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በሀገራዊ መድረኮች እየተገኙ ያላቸውን ለግሰዋል፡፡
ይህንን መጽሐፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ከራሴም ጋር ሆነ ከሌሎች ጋር ተወያይቼበታለሁ፡፡ ተምሬበታለሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮችንም አንሥቼበታለሁ፡፡ ለመጻፍ ግን ጥቂት ቀናትን መውሰድ አስፈልጓል፡፡ ስለ ሦስት ምክንያት፡፡ ምናልባትም ከእኔ የተሻለ ሰው በጉዳዩ ላይ ይጽፍና ሃሳቤን፣ ያነሣው ይሆናል ብዬ፤ በሌላም በኩል ምናልባትም በሕይተወትና በጤና ያለው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አንድ ነገር ይል ይሆናል ብዬ፣ እንዲያም ባይሆን እነዚህ ሊቃውንትን ያፈራውና እነርሱም ያፈሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል ምልከታውን ያቀርብ ይሆናል ብዬ፡፡ ግን የሆነ አልመሰለኝም፡፡
ይህ አሁን የቀረበው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የኢትዮጵያን ታሪክ የሞገቱበት መጽሐፍ ነው፡፡ ጉዳዩ ገና ከርእሱ ይጀምራል፡፡ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ሲል፡፡ አነጋጋሪ፣ አመራማሪና አከራካሪነቱንም አሐዱ ይላል፡፡ ለመሆኑ ታሪክ ይከሽፋል? የክሽፈት ታሪክ ሊኖር ይችላል እንጂ የከሸፈ ታሪክ ሊኖር ይችላል? የስኬት ታሪክ ይኖራል እንጂ የተሳካ ታሪክ ይኖራል?
ፕሮፌሰር መስፍን ራሳቸው በመጽሐፋቸው ከገጽ 34 ጀምረው ስለ ታሪክ ምንነት ብያኔ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ብያኔያቸውም ታሪክን ‹ዘገባ› ‹መዝገብ› ‹ውለታ› ‹ሰንሰለት› እያሉ ነው የገለጡት፡፡ ይህ ገለጣቸው ደግሞ ታሪክ የማይቋረጠውን የሰው ልጆች ጉዞ የሚያሳይ ዘገባ፣ የትናንቱን የሰው ልጅ ሂደትና አስተዋጽዖ የምናነብበት መዝገብ፣ የትናንቱ ማኅበረሰብ ያቆየልን ውለታ ነው፡፡ የትናንቱንና የዛሬውንም የሚያስተሣሥር ሰንሰለት ነው፡፡
እንዲያ ከሆነ ደግሞ ታሪክ የአንድን ማኅበረሰብ የስኬትም ሆነ የክሽፈት፣ የድልም ሆነ የሽንፈት፣ የውጤትም ሆነ የኪሳራ፣ የልዕልናም ሆነ የተዋርዶ ጉዞ የሚያሳየንና የምናጠናበት፣ የምንመዘግብበትና የምናይበት ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ክሽፈቱ እናይበት ይሆናል እንጂ ራሱ የሚከሽፍ አይመስለኝም፤ ስለ ስኬቱ እናጠናበታለን እንጂ ራሱ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ ሰው የስኬት ታሪክ ይኖረዋል እንጂ ታሪኩ አይሳካለትም፡፡ የሽንፈት ታሪክም ይኖረዋል እንጂ ታሪኩ አይሸነፍበትም፡፡ ለዚህ ነው አከራካሪነቱ፣ አነጋጋሪነቱና አመራማሪነቱ ከርእሱ የሚጀምረው፡፡
ያንን ብንሻገረውና ታሪክ ይከሽፋል ብንል እንኳን መከራከራችንንና መመራመራችንን አናቆምም፡፡ ‹እውነት የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል? አንድን ታሪክ ከሽፏል ወይም ተሳክቷል የሚያሰኘው ምን ምን ሲሆን ነው? የሚሉትን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የምናጣው ታላቁ ነገር ይኼ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለታሪካችምን መክሸፍ ማሳያ ናቸው ያሏቸውን ነገሮች ከማንሣታቸው በቀር ይህንነ ነገር አላብራሩልንም፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ያጣሁት ታላቅ ነገር የሚመስለኝ ይኼ ነው፡፡ የታሪክን ‹ክሽፈትና› ስኬት› መበየኛ ነገሮችን አስቀድመው በማሳየት፤ አንድ ታሪክ ‹ከሸፈ. ወይም ‹ተሳካ› የሚያሰኙትን መመዘኛዎች በመተንተን፣ በዚያም መሠረት የኢትዮጵያን ታሪክ እየገመገሙ እዚህ እዚህ ላይ እንዲህ ስለሆንን፣ በዚህ መመዘኛ መሠረት ከሽፈናል ይሉናል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን ሌላ አካሄድ መርጠዋል፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ዋናውን ቦታ የያዙት ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ከእነርሱ በፊት ሌሎች የታሪክ ሰዎችም እየቀረቡ ሂሳቸውን ተቀብለዋል፡፡ እኔ እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍንን መጠየቅ የምፈልገው ሁለት ጥያቄ ነው፡፡
የመጀመርያው የታሪክ ክሽፈትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንዴት ነው የተገናኙት? የታሪክ ክሽፈትን ለማሳየት የታሪክን ሂደት ተከትሎ አንድን ሁነት ከየት ተነሥቶ የት እንደደረሰ በመተንተን፣ ያም ሁነት ከሽፎ ከሆነ የከሸፈበትን ምክንያት ማቅረብ ሲገባ ታሪካችን ከሽፏል ብንል እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?
ለእኔ ይህ አካሄድ አንድ ሰው ሌላ ሰውን የገደለበትን ዜና የሠራውን፣ ለዜናው ትንታኔ ዜና ያቀረበውን ጋዜጠኛና ተንታኝ የግድያው ወንጀል አባሪ ተባባሪ፣ ወይም ደግሞ ለግድያው ምክንያትና መነሻ አድርጎ እንደማቅረብ ነው፡፡ ዘጋቢውን ‹ወንጀለኛ› ማለትና ዘገባውን ‹የወንጀል ዘገባ› በማለት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ዘጋቢው ወንጀለኛ የሚባለው የሠራው ዘገባ ሕግን የተላለፈ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ዘገባውን የወንጀል ዘገባ የሚያደርገው ግን ስለ አንድ ስለተፈጠረ ወንጀል የቀረበ ዘገባ ከሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ጥናት ለብቻው ቢተነትኑትና ያም ትንተና የታሪክ አጻጻፋችንና አተናተናችን የተሳካ ነው ወይስ ያልተሳካ? አስመስጋኝ ነው ወይስ አስነቃፊ? ተመስጋኝ ነው ወይስ ተነቃፊ? የሚለውን ቢተነትኑት እስማማ ነበር፡፡
አንድ ኦዲተር የአንድን ድርጅት ሂደት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ያ ድርጅት ከስሮ ከሆነ የኪሳራውን መጠንና የኪሳራውንም ምክንያት ያቀርባል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ያ ኦዲተር የራሱ ሕፀፆች ይኖሩበታል፡፡ ሁለቱ ነገሮች ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ የድርጅቱ ኪሳራና የድርጅቱን የኪሳራ ሪፖርት የሠራው ባለሞያ ሕፀፅ፡፡ የዚህን ድርጅት ታሪክም አንድ የታሪክ ባለሞያ ሊዘግብ፣ ሊተነትንና የኪሳራውንም መነሻና ሂደት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ የታሪክ ባለሞያ ይህንን ታሪክ ሲዘግብና ሲተነትን ድክመቶች ሊኖሩበት ይችላል፡፡ የሁለቱ መገምገሚያ ግን ይለያያል፡፡ የድርጅቱ መክሰርና የታሪክ ባለሞያውም የከሰረ ድርጅትን ታሪክ መዘገቡና መተንተኑ ‹የከሰረ የታሪክ ባለሞያ› አያሰኘውም፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ላይ የተተቹት የታሪክ ባለሞያዎችም በፕሮፌሰር ሐሳብ ብንስማማ እንኳን ‹የከሸፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ በየአንጻራቸው ዘገቡ፣ ተነተኑ› እንጂ እነርሱ ራሳቸው የከሸፉ የታሪክ ባለሞያዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል ቢባል እንኳን ለዚያ ለከሸፈው ታሪክ ማጣቀሻ ይሆኑ ይሆናል እንጂ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ ሥር የእነርሱ ሥራ መተንተን አልነበረበትም፡፡ ምንልባት ፕሮፌሰር ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ› የሚል ርእሰ ጉዳይ ቢያነሡ ኖሮ የማርያም መንገድ ባገኙ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ በርግጥ ከሽፏል? በሚለው ከተስማማን ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብ ችግሮችና የአተያየይ ሳንካዎች ማንሳታቸውና በዚያ ላይ ትችት ማቅረባቸው አልነበረም ችግሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱን አስችለውና ደረጃውን ጠብቀው ደግመው ደጋግመው ቢሄዱበት ለሁላችንም የዕውቀት በረከት የሚሆን ነው፡፡ ነገር ግን ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ ታሪክ ጸሐፊዎቹን ከታሪኩ ጋር አብሮ መውቀጥ ‹ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ› ዓይነት ይሆናል፡፡ ‹ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ይዘንባል› ያለውን የሜትሮሎጂ ባለሞያ ‹ለምን ዘነበ› ብሎ እንደመውቀስ ነው፡፡
ሌላው ሁለተኛው ጥያቄዬ የተነሡትን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የሚመለከት ነው፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ላይ በዋናነት ተነሥተው የተተቹ አምስት ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሊቃውንት አሉ፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይና ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፡፡ ከእነዚህ ሊቃውንት መካከል ከፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴና ከፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በቀር ሌሎቹ ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ በሕይወት ከሚገኙት ከሁለቱ ሊቃውንት መካከልም ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ታምመው በድካም ላይ ነው የሚገኙት፡፡
ምንም እንኳን በአንድ መጽሐፍ ላይ የሚደረግ ክርክርና ሂስ ሰዎቹ መልስ ሊሰጡበት፣ ሂሱንም ሊቀበሉበት ዘመን ብቻ መሆን አለበት ባይባልም፣ ይህ ዕድል ካለና ከነበረ ግን ይመረጣል፡፡ ቢያንስ ስለ ሦስት ነገር፡፡ አንደኛ እነዚህ ሊቃውንት ሂሱን ተመልክተው እንዲሻሻሉ፤ ሁለተኛም እነዚህ ሊቃውንት የእነርሱንም አተያይ የማቅረብ ዕድል እንዲያገኙ፤ ሦስተኛ ደግሞ ነገሩ ፍትሐዊ እንዲሆን፡፡ አንድን አካል መልስ ለመስጠት በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ ማሄስና መውቀስ ከሞራል አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ የሀገሬ ሰው ‹ሙት ወቃሽ አትሁን› የሚለው ሙት መወቀስ ስለሌለበት ሳይሆን ‹መልስ ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ› ማለቱ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የነ ፕሮፌሰር ታደሰ፣ የነ ዶክተር ሥርግውና የነ ፕሮፌሰር መርዕድ ዘመነኛ ናቸው፡፡ ይህ ዛሬ የሰጡት ትችት በዚያ በዘመነኛነታቸው ወቅት ቢሆን ኖሮ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚኖር ክርክር ታላቅ ዕውቀት በተገበየ ነበር፡፡ በርግጥ ልዩ ልዩ መዛግብትን ስናገላብጥ አንዳንድ ክርክሮች እንደነበሩ ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ኅትመቶች ሲወጡም ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ የፕሮፌሰር መስፍን ሐሳብ ቀርቦ ክርክር አልተደረገበትም፡፡
የፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት church and state in Ethiopia የሚለው መጽሐፍ የታተመው በ1964 ዓም ነው፡፡ የዛሬ 41 ዓመት፤ የዶክተር ሥርግው Ancient and medieval Ethiopian History to 1270 የታተመው በ1964 ዓም የዛሬ 41 ዓመት ነው፡፡ የፕሮፌሰር መርዕድ ጽሑፍ political geography of Ethiopia at the beginning of 16thc.የታተመው በ1966 ዓም ነው፡፡
አንግዲህ ይህንን ሁሉ ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ትችቱ መቅረቡ ነው ለእኔ የሞራል ጥያቄ እንዳነሣ ያደረገኝ፡፡ እነዚህን ሰዎች በዘመን ያላገኘናቸው፤ ‹ጥንት› በምንለው ዘመን የነበሩ ቢሆኑ ኖሮ የሞራል ጥያቄው ሊነሣ ባልቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእኛው ጋር የነበሩ፤ መልስ ሊሰጡበትና ትችቱን ሊቀበሉበት በሚችሉት ዘመንም ሊጻፍላቸውም፣ ሊጻፍባቸውም የሚቻል፣ ነበርና ምነው? ያሰኛል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያን ጥንታዊና የመካከለኛው ዘመን በማጥናትና በመተንተን እንደ ሥርግው፣ እንደ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና እንደ ፕሮፌሰር መርዕድ ያለ ሰው ዛሬ አላገኘንም፡፡ በየመድረኩም ሆነ በየመዛግብቱ እንደ ብሉይና ሐዲስ የሚጠቀሰው የእነዚሁ ቀደምት አበው ሥራ ነው፡፡ የእነዚህን ቀደምት አበው ሥራዎች በማይመለከታቸው ርእስና ጉዳይ ላይ ማንሣትም ሆነ ማሄስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለቡድኑ መሸነፍ ተጨዋቾቹንና አሠልጣኙን፣ ፌዴሬሽኑንና ኮሚሽኑን መጠየቅ ሲገባ የጨዋታውን ዘጋቢና ተንታኝ ጋዜጠኛ መውቀስ ይመስላል፡፡
ከቀድሞ ጀምሮ በልሂቃኑ ዘንድ ከዕውቀት ክርክር የዘለለ ሌላ የጎንዮሽ መጎሻሸምና መነካካት እንደነበረ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ምሁራን ታሪክ የሚያጠና ሁሉ የሚደርስበት ነው፡፡ አንድ ማሳያ ብቻ ላንሣ፡፡ አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህራንና በሌሎች መካከል ‹ጠብ› ተፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም ለአብዮቱ እንቀርባለን የሚሉ ምሁራን እነዚህን የታሪክ ክፍል መምህራን ‹ደብተራዎች› እያሉ መውቀስና እንደ አድኅሮት ኃይላት መመልከት ያዘወትሩ ነበር፡፡
ይህ ነገር እየከረረ መጣና አንድ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ምሁር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ ሄደው እነዚህን የታሪክ መምህራን በፀረ አብዮትነት ከሰሱ፡፡ በወቅቱም ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ቤተ መንግሥት እንዲመጡ ተጠሩ፡፡ እኒህ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዶክተር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ በማን በኩል እንደ ሄዱ ፕሮፌሰር መስፍን ያውቃሉ፡፡
ፕሮፌሰር ታደሰ ከሌሎቹ ምሁራን ጋር በጉዳዩ መክረው ወደ ቤተ መንግሥት ተጓዙ፡፡ አንዳች ክፉ ነገር እየጠበቁ ነበር የገቡት፡፡ መንግሥቱ በክብር ተቀበላቸውና የአብዮቱን ታሪክ እንዲጻፍ መፈለጉን ነገራቸው፡፡ ፕሮፌሰርም ልባቸው መለስ አለች፡፡ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ሞያዊ ሥራ ለመሥራት እንደሚቻል ገለጡ፡፡ መንግሥቱም ፕሮፖዛል እንዲያዘጋጁ ነግሮ በክብረ ሸኛቸው፡፡ ከመሸኘቱ በፊት ግን ‹ከዶክተር እገሌ ጋር ቅሬታ አላችሁ መሰል፣ አንዳንድ ነገር ነግሮኝ ነበር፤ እዚያው ተነጋግራችሁ ፍቱት› አላቸው፡፡ እርሳቸውም እንፈታዋለን ብለው ከቤተ መንግሥት ወጡ፡፡
አሁን እዚህ መጽሐፍ ላይ ቤተ መንግሥቱን አየሁት፡፡
No comments:
Post a Comment