Jan 31, 2013

አብዛኞቹ የተፈናቀሉ የጉራፈርዳ ነዋሪዎች የደረሰቡት እንደማይታወቅ መኢአድ ገለጠ


ኢሳት ዜና:-ድርጅቱ ” በጭቆናና በአፈና ስልጣንን ለማራዘም የሚካሄደው ዘመቻ ቀጥሏል” በሚል ርእስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፣ በጉራፈርዳ ወረዳ የሚፈናቀለው አርሶአደር ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑንና የተወሰኑትም በሚዛን ተፈሪ፣ በጅማ፣ በአንቦ እና በአዲስ አበባ ያለመጠለያ ለልመና መዳረጋቸውን ገልጿል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶአደሮች መሬታቸውን ተነጥቀው የአካባቢው ታጣቂዎች በጨረታ ስም እየተቀራመቱት መሆኑን የገለጠው መግለጫው፣ ወ/ሮ ስንዴ ስጦታው የተባሉ የስምንት ልጆች እናት በጥይት ተደብድበው በመሞታቸው ልጆቻቸው ያለአሳዳጊ መቅረታቸውን አብራርቷል።
ጥር 21 ከሌሊቱ 8 ሰአት ከወረዳው መስተዳደር የተላኩ አራት ወታደሮች ወደ አቶ ኢበሉ ማሞ ጊቢ በመግባት ሁለት በሬዎችና ሶስት በጎችን መውሰዳቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ መግለጫ፣ 32 ሰዎችም እንዲሁ በእስር ቤት ያለምንም ፍርድ እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጿል።
መኢአድ ” በጉራፈርዳ ህዝብ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው ወከባ እስራትና እና ግድያ በአገራችን ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ረገጣና የአንድን ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብን የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ” በማለት ገልጾ፣ ነዋሪዎቹ ከአካባቢው መልቀቅ እንዳለባቸው አለበለዚያ ግን ሁሉንም እንደሚገድሏቸው የወረዳው አስተዳዳሪዎች እና የፖሊስ ሀላፊዎች መግለጻቸውንም ይፋ አድርጓል።
በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ የተካሄደውን የሌሎች አገራት የዘር ማጥፋት ወደ አገራችን መግባቱን፣ በጉራ ፈርዳ የተፈጸመው ድርጊት እንደሚያመላክት የገለጸው መኢአድ፣ ድርጊቱን  ኢትዮጵያውያን ተረባርበው እንዲያስቆሙት ጥሪ አቅርቧል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ መምጣታቸው ይነገራል።

    No comments:

    Post a Comment