Jan 20, 2013

ህይወታቸው አልፏል ተብሎ ሊቀበሩ የነበሩ እናት፤ ድንገት ነፍስ ዘርተው መንቃታቸው አስደነገጠ፡፡


በመቀሌ ህይወታቸው አልፏል ተብሎ ሊቀበሩ የነበሩ አንዲት እናት፤ ድንገት ነፍስ ዘርተው መንቃታቸው ቤተሰቦቻቸውንና የአካባቢውን ነዋሪዎች አስደነገጠ፡፡ መግንዛቸው ተፈትቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት እኚህ እናት፤ በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ሃኪም ገልጿል።ምንልክሳልሳዊ
በመቀሌ ከተማ ቀበሌ 03 ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ወይኒ ፀጋዬ ከሐሞት ጠጠር እና ከኩላሊት ችግር ጋር በተያያዘ በገጠማቸው የጤና መቃወስ በመቀሌ ሆስፒታል ከአንድ ወር በላይ በመተኛት ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ የወ/ ሮዋ ሐኪም ዶ/ር ዘካሪያስ ገሰሰ እንደገለፁት፤ ሴትየዋ የሽንት ባንቧቸው ተዘግቶ ኩላሊታቸው ውሃ ቋጥሮ ለከፍተኛ ሥቃይ ዳርጓቸው ነበር። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘም አንደኛው ኩላሊታቸው መስራት ያቆማል፡፡ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ህክምና ግን የሴትየዋ ጤና መሻሻል ከማሳየቱም በላይ አገልግሎት መስጠት አቁሞ የነበረው ኩላሊታቸው ወደ ትክክለኛ ሥራው መመለስ ጀመረ፡፡ በመጨረሻም ጤናቸው በእጅጉ በመሻሻሉና የገና በዓልም እየተቃረበ በመምጣቱ ሴትየዋ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ጥያቄ ያቀርባሉ” በጥያቄያቸው መሰረትም ከሆስፒታሉ ወጥተው በዓልን በቤታቸው እንዲያሣልፉ መፈቀዱን ዶ/ር ዘካሪያስ ይገልፃሉ፡፡ የገናን በዓል ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሠላም እንዳሳለፉ የሚናገረው ልጃቸው ቴዎድሮስ ፍስሃ፤ የጤንነታቸው ሁኔታ መልካም በመሆኑና እምብዛም የሚያሣስባቸው ችግር ስለላጋጠማቸው ወደ ሆስፒታል እንዳልተመለሱ ገልጿል፡፡ ጥር 5 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ ላይ ግን ወ/ሮ ወይኒ ቀስ በቀስ እየደከሙ በመሄዳቸው ልጆቻቸው ተደናግጠው እየተጯጯሁ የአካባቢ አንጋፋ ሰዎችን ይጠራሉ፡፡ የወ/ሮ ወይኒን ሰውነት መቀዝቀዝና የልብ ምታቸው መቆሙን ያስተዋሉት የአካባቢው ሰዎች፤ ሴትየዋ መሞታቸውን ያረዳሉ፡ ፡ ይሄኔ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በመሪር ሃዘን ተውጠው ለቅሶአቸውን ያቀልጡታል፡፡ እንደ አካባቢው ወግና ሥርዓትም የወ/ሮ ወይኒ አስከሬን ታጥቦና ተገንዞ በሰሌን እየተጠመጠመ ጥብቅ ተደርጐ ይታሰራል፡፡ምንልክሳልሳዊ
በአካባቢው ባህል ሰው ከሞተ ማሣደርና ማቆየት ስለማይገባ የፍትሃት ፀሎት ተደርጐላቸው ቀብራቸው ከቀኑ 8 ሰዓት እንዲሆን ይወሰናል፡፡ ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ በሀዘን ተውጠው የእናታቸውን አስከሬን እያዩ ከነበሩት ልጆች መካከል አንዱ ድንገት ጩኸት ያሰማል፡፡ ሌሎቹ ተደናግጠው የሆነውን ሲጠይቁት “አስከሬኑ ይንቀጠቀጣል” በማለት ይናገራል - ወደ አስከሬኑ በፍርሃት እያየ፡፡ ነገሩ ያስደነገጣቸው ልጆችና የአካባቢው ሰዎች፣ አስከሬኑን ከበው ሁኔታውን መከታተል ይጀምራሉ፡፡ የሴትየዋ መንቀጥቀጥ እየጨመረ ሲመጣ አስከሬኑን በመፍታት ሐኪማቸውን ያስጠራሉ፡፡ በሰሌን ተጠቅልሎና በጥብቅ ታስሮ የነበረው በተፈታ ጊዜ ሴትየዋ በእፎይታ እንደተነፈሱ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ሃኪሙወዲያውኑ ሴትየዋን ወደ ሆስፒታል በማስወሰድ ጉሉኮስ እንዲሰጣቸዉ ያደረጉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ከጥቂት ቀናት በኋላም ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ሃኪማቸው ዶ/ር ዘካሪያስ ገሰሰ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዘካሪያስ በዚህ አጋጣሚ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አንድ ሰው ሞተ ተብሎ መሞቱ መረጋገጥ የሚቻለው በህክምና በመሆኑ የሞት ማረጋገጥ ህክምና ቢለመድ ከነህይወታቸው የሚቀበሩ ሰዎችን ነፍስ መታደግ ይቻላል፡፡ እናም የሞት ማረጋገጥ ህክምና መለመድ ይገባዋል” ብለዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment