በላሊበላ ተገኝቶ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘው የፓርላማው ቡድን ከተመለሰ በኋላ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳለቾና ሌሎች በሚኒስቴሩ ሥር የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችን ባለፈው ሰኞ በመጥራት ምልከታውን በማቅረብ ማሳሰቢያም ሰጥቷል፡፡
በንጉሥ ላሊበላ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ከአለት ተፈልፍለው የተሠሩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ የመሰንጠቅ አደጋ ላይ መሆናቸውንና አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኙም ሊፈርሱ እንደሚችሉ ቡድኑ ለኃላፊዎቹ ሪፖርት አድርጓል፡፡
በተለይም የቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ ጐለጐታ፣ ቤተ መርቆርዮስና ቤተ ደናግል አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱት መካከል እንደሚገኙበት በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ሚኒስቴሩ በአገሪቱ የሚገኙ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲያጠኑት ተደርጎ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ተቋማቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን፣ በመጪዎቹ ወራት ውስጥም መፍትሔ የመስጠት ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
አብያተ ቤተ ክርስቲያናቱ የተሠሩት ከአለት ተፈልፍለው በመሆኑ እንደሌሎቹ ዓይነቶች ቅርሶች በቀላሉ ጥገና በማድረግ የገጠማቸውን የመሰንጠቅ አደጋ ለማቆም በአገር ውስጥ ባለው የአቅም ደረጃ የሚቻል እንዳልሆነ፣ መሰንጠቁ የተፈጠረው በጂኦሎጂካል ምክንያት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ጂኦሎጂካል ምክንያቱ በየትኛው የአለቱ ክፍል ላይ እንደተፈጠረ ማወቅ በራሱ ከፍተኛ ጥናትን ይጠይቃል ብለው፣ መፍትሔም ሊያጣ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
ቢሆንም ባለሥልጣኑ በዚህ መሰል ቅርሶች ጥገና ላይ ልምድ ካለውና ከጣሊያን ወደ አገሩ ተቆራርጦ የገባውን የአክሱም ሐውልት በማያያዝ በአክሱም የተከለው ድርጅት፣ በላሊበላ ቅርሶች ላይ የተፈጠረውን ችግር በመመርመር መፍትሔ እንዲያመጣ ሥራው ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ኩባንያውም ሥራውን ለመጀመር በመጋቢት ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አብራርተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment